Get Mystery Box with random crypto!

#ቃል #ዳንኤላ_ስቴል ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ ምዕራፍ ዘጠኝ (9) የአውሮፕላኑ መስገሪያ ጎማ | ✍ ልብ ወለድ በፅዮን ✍ fiction ❤️😘

#ቃል
#ዳንኤላ_ስቴል
ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ

ምዕራፍ ዘጠኝ (9)

የአውሮፕላኑ መስገሪያ ጎማ ከሆዱ ውስጥ ጉጉ ግርር ብሎ ሲወጣ ለናንሲ በደንብ ተሰማት ። እጅዋን ስትዘረጋ ከቦስተን ወደ ሳንፍራንሲስኮ ባደረገችው በዚህ ጉዞ ላይ ያዝ እያደረጉ መቶ ጊዜ ያህል ካፅናኗት ሁለት የተለያዩ እጆች አንዱ ያዝ አደረጋት ። ከሁለቱ ነርሶች አንደኛዋ ነበረች እጅዋን ያዝ አድርጋ ያጽናናቻት ። የነርሷ እጅ እጅዋን ሲቀበል መንፈሷ ተረጋጋ። የትኛዋ ነርስ እንደሆነች ስታውቅ ደስ አላት ። በአያያዛቸው መለየት ጀምራ ነበር ። የአንደኛዋ ነርስ እጅ ቀጭን ሲሆን ልስልስ ያለ ነበር ። የዚች ነርስ እጅ ቀዝቃዛ ቢሆንም አጨባባጧ ግን ጠንካራ በመሆኑ ይህችኛዋ ሴት ስትጨብጣት ፍርሃት ፤ ፍርሃት የሚላት ይተዋትና ልቧ መድፈር ይጀምራል። የሁለተኛዋ ነርስ እጅ ወፍራምና ቡትቡት ያለ ሲሆን ገና ያዝ ስታደርጋት ክብካቤና ፍቅር ያልተለያት እንደሆነ ይሰማታል ። የዚች ነርስ ሞቃት እጅ ፍቅርን ይገልጽላታል ። ያዝ አድርጋ እትከሻዋ አካባቢ እጅዋ መባቀያ ላይ መታ መታ ስታደርጋት የፍቅሯን ጥልቀት ይገልጽላታል ፤ ለናንሲ ። ህመሙ ጠንከር ሲልባት ሁለት ጊዜ መርፌ የወጋቻት ይህችው ነርስ ነበረች ።

ድምጿም የሚያረጋጋ ሀይል አለው። ልስልስ ያለ ነው። ቀጭን እጅ ያላት ሴትዮ ስትናገር ትንሽ ያዝ ያደርጋታል ። ናንሲ ሁለቱንም ሴቶች እየወደደቻቸው ስትሄድ ተሰማት ።

«አሁን ደርሰናል የኔመቤት ። ማረፊያው እየታየኝ ነው» አለች ጠንከር ያለ አያያዝ ያላት ነርስ እጅዋን እንደያዘች ።

ነገሩ እንደተባለው ነበር ። የቀራቸው ሃያ ደቂቃ ያህል ሲሆን፤ ፒተር ግሬግሰን ሰዓቱን በማየት አረጋገጠ ። ፒተር ግሬግሰን በቀጠሮው መሠረት በጥቁሩ አውቶሞቢል ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ሲነጉድ ይህን ተገንዝቧል። አምቡላንሱ እዚያው ይጠብቀዋል ። ፒተር ሕክምናውን ከሚያደርግላት ልጅና ከነርሶቹ ጋር በአምቡላንሱ ሊመለስ ወስኗል።ምክንያቱም የልጅቷ ሁኔታና የሚያደርግላት ሕክምና አጓጉቶታል ። አዲስ ፊት መስራት ! አዲስ ውበት መፍጠር ! ይህ 'ቀላል ነገር አይደለም ። በዚያ ላይ ምን አይነት ፊት እንደሚፈጥር ያውቃል ። ፒተር በዚህ ሁኔታ ሀሳቡን ሊቀጥል አልፈለገም ። ስለዚሀም ስለናንሲ ማንነት ማሰብ ቀጠለ ። አራት መቶ ሺህ ዶላር እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ ነው። ልጅቷ ይህን የሚከፍልላት ሰው ማግኘቷ መታደል ነው። ለማሪዮን ሂልያርድ ምኗ ትሆን! ማሪዮን በጣም የምትወዳት ወይም የምታስብላት ሰው መሆን አለባት-። ያለዚያ ይህን ያህል ገንዘብ አታወጣም ነበር። ይህን ያህል አትጨነቅላትም ነበር ።። አራት መቶ ሺህ ዶላር ! ከዚህ ውስጥ ሦስት መቶ ሺህ ዶላር የሱ የአገልግሎት ዋጋ ነው ። ወጭውንና የመሳሰለውን ችሎ ። መቶው ሺህ ዶላር ግን የተከፈለው ለታካሚዋ ነው ። ሕክምናዋን እስክትጨርስ ለመኖር የሚያስፈልጋትን ነገር ለማሟላት የምትጠቀምበት ። በዚህ ገንዘብ የፈለገችውን ሁሉ ለማሟላት ወደ ኋላ አልልም አለ ፒተር ግሬግሰን በሀሳቡ ።

እንደገናም አመት ከመንፈቅ ሙሉ በአይኑ ላይ ውል ሲለው የኖረ ፊት ትዝ አለው ። ያ ፊት ናንሲን አዲስ ሴት ያደርጋታል ። ለአስራ ስምንት ወራት ያረገዘውን ፊት ናንሲ አድርጎ ይወልደዋል ። የናንሲና የእሱን የወደፊት ግንኙነት ሲያስበወ ሲቃ ያዘው። ናንሲ የሙያውን ረቂቅነት የሚያይባት ብቻ አትሆንም ። የእሷና የሱ ግንኙነት ከሐኪምና ታካሚ ግንኙነት ያልፋል ። ከመዋደድም ያልፋል ። ደፋርና በራሷ የምትተማመን ሴት የምትሆንበትን መንገድ ሁሉ ያደርጋል ። ደግሞም ትሆናለች። ይህን ነገር ሲያስብ የሆነ ያህል ሆኖ ተሰማው። በደስታ ሰክረ። ሙያውን ይወደዋል ። አንድ ነገር ሰርቶ ውጤቱ ሲያምር ሁልጊዜም ይደሰታል ። ስለዚህም ምንም እንኳ ነገሩ ግራ ቢመስል ፤ገና ካሁኑ ከናንሲ ጋር ፍቅር ያዘው። ገና ወደፊት ከሚፈጥራት ናንሲ ጋር፤ ካላያት ናንሲ ጋር።

ሰዓቱን እንደገና አየት አደረገ ጊዜው እየታቀረበ ነው። ቤንዚን መስጫውን ተጫነው። መኪናው ተፈተለከ ። የቀጠሮው ሰዓት በመድረሱ ብቻ ሳይሆን ፒተር ግሬግሰን በፍጥነት መንዳት በጣም ከሚያስደስታቸው ሰዎች አንዱ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። ፒተር የግል አውሮፕላንም አለው። ያን አውሮፕላን አስነስቶ በጣም ከፍ ብሎ ማብረር ወይም አውሮፕላኑን በፍጥነት ሽቅብ ነድቶ አቅጣጫ ለውጦ ዘቅዝቆ ቁልቁል ማብረር በጣም ያስደስተዋል። ጉራ ወይም ሌላ ነገር አይደለም፣ፒተር አስቸጋሪ ነው የሚባለውን ነገር ሁሉ ማድረግ ይወዳል። አደገኛ ነው ሲሉት ተራራ መውጣት... የመሳሰሉትን ሁሉ በሚገባ እስኪካናቸው ድረስ ያደርጋቸዋል። ፒተር አናቱ ድረስ ያልወጣበት የአውሮፓ ተራራ አይገኝም። ይህ ሁሉ ታዲያ እላይ እንደተገለፀው ካስቸጋሪው ጋር መጋፈጥን በመውደዱ ነው። በዚህ ጠባዩ ነው ይህን የቆዳና የአካል ቅርፅ መፍጠር ቀዶ ሕክምና ሙያው ያደረገው። አስቸጋሪና ብዙ ጥንቃቄ ያሻዋል። ያ ስለሆነ እንዲያውም ሰዎች አንዳንድ ጊዜ እግዜር ልትሆን ትሻለህ? በሚል ተረብ ገረፍ ያዶርጉታል። እሱ ግን ይህ እንዳልሆነ ያውቃል። ይህን አይነት ሕክምና እንዲያደርግ እሱን የሚገፋፋው እልህ ነው ፤አይቻልም ያሉትን ነገር እንዲቻል የማድረግ እልህ። እና አድርጎ ማሳየት ። ፒተር ይኸው ነው። እስከዛሬ ድረስ ያከማቸውን ሰዎች አስታወሰ ። ተሳክቶለታል ። ፒተር ሁልጊዜም ይሳካለታል ። የፈለጋት ሴት እምቢ አትለውም ። ተራሮች ተረትተውለታል። ሰማይን ተጫውቶበታል። ምን ጊዜም አሁንም ይሳካለታል። ናንሲና እሱ ተረዳድተው ሕክምናው ባሰበው መንገድ ይፈጸማል። ዛሬ የአርባ ሰባት አመት እድሜ ያለው ሰው ነው። በዚህ ባሳለፈው እድሜ ሁሉ ተሸንፎ አያውቅም ። ዛሬም አይሸነፍም

«ሄሎ ናንሲ ፤እንኳን ደህና መጣሽ ጉዞው እንዴት ነበር! አለ ፒተር ግሬግሰን ካውሮፕላኑ እንደወረደች ። ሁለቱን ነርሶች እንዳያቸው ተስማሚ እንደሆኑ ገምቷል ። ለነሱ በጥቅሻ ሰላምታ ሰጠ። ፤ድምጹን ስትሰማ ደስ አላት ።
«ጥሩ ነበር፤ ዶክተር ግሬግሰን » አለች ናንሲ ።ድምጺ እንደደከማት በ.ያመለክትም ስልቸታ ግን አልነበረበትም ።
«ዶክተሬ ነህ-»
«ነኝ። ግን ካሁን ጀምሮ አብረን መሥራታችን እይደለም? ስለዚህ ሚስ ማክኦሊስተር ፤ዶክተር ግሬግሰን ከመባባል ፤ እኔም ናንሲ ብል አንችም ፒተር ብትይ ይበልጥ የሚያቀራርበን ይመስለኛል» አለ ፒተር ። አቀራረቡ ደስ አላት ።
«ልትቀበለኝ ነው እዚህ ድረስ የመጣኸው » አለች።
«አንቺ ብትሆኝ እዚህ ድረስ መጥተሽ አትቀበይኝም ነበር ማለት ነው?» ሲል ጠየቃት ።
«እቀበልህ ነበር እንጂ» አለች ይህን ስትል በሚገርም ሀኔታ ነገሩ እውነት መሰላት። ይህን ያህል ከሰው ጋር ባጭር ጊዜ መግባባት መቻሏ ገረማት «አመሰግናለሁ» አለች ።
«እኔ የመጣሁት ለራሴ ደስ ስለሚለኝ ነበር ። ሆኖም አንችንም ደስ ሲልሽ አየሁ ። ይህ ደሞ ደስታዬን እጥፍ አደረገው እንኳን መጣሁ አሰኘኝ» አለ ።« በማከታተልም «ናንሲ» አለ
«አቤት »
«ናንሲ ከዚህ በፊት ሳንፍራንሲስኮ መጥተሽ ታውቂያለሽ?»
«አላውቅም»
‹‹ደስ እምትል ከተማ ናት ። ፍሬስኮን እንደምትወጃት እተማመናለሁ። ምርጥ የሆነ አፓርታማ እንፈልግልሻለን ። አለቀ ። ብዙ ሰዎች ሳንፍራሲስኮን ከረገጡ በኋላ የተወለዱበትን ፤ የኖሩብትን ቦታ ይረሳሉ። እዚሁ ቅልጥ ብለው ነው የሚቀሩት ። ለምሳሌ የእኔን ነገር ማንሳት እንችላለን ። የዛሬ አሥራ እምስት አመት አካባቢ ከሺካጐ መጣሁ። መጣሁ ቀረሁ። ዛሬ የፈለገው ነገር ቢመጣ ከዚች ከተማ ንቅንቅ አልልም ። አንች የት ነው የነበርሽው?››
‹‹ቦስተን »