Get Mystery Box with random crypto!

#ቃል #ዳንኤላ_ስቴል ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ ምዕራፍ ስምንት (8) ናንሲን አምቡላንስ ላይ | ✍ ልብ ወለድ በፅዮን ✍ fiction ❤️😘

#ቃል
#ዳንኤላ_ስቴል
ትርጉም፣ ባሴ ሐብቴ

ምዕራፍ ስምንት (8)


ናንሲን አምቡላንስ ላይ ሲያሳፍሯት ፤ ማረዮን ሂልያርድ ጥቁር የሱፍ ቀሚስና መደረቢያውን ለብሳ ሆስፒታሉ ሕንፃ በር ላይ ቆማ ትመለከት ነበር። ጊዜው ከጥዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ፤ ቀኑ ከናንሲ ጋር ከላይ የተገለጸውን ስምምነት ባደረጉ ማግሥት ነው ። ከናንሲ ጋር እዚያ ስምምነት ከደረሱ በኋላ ማሪዮን ዳግም ወደ ናንሲ ክፍል ዞር አላለችም ። ዳግም አላነጋገረቻትም ። ብቻ እስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ጉዳዩን ለዶክተር ሮበርት ዊክፊልድ አነሳችለትና በፍጥነት ከዶክተር ፒተር ግሬግሰን ጋር እንዲዋዋል ጠየቀችው ። ዶክተር ዊክፊልድ ይህን ሲሰማ በደስታ ሰክሮ ማሪዮንን ጉንጩን ሳማት ። ግሬግሰንን አንጋገረው ። ግሬግሰንም ተሰማማ በቃ ። ፒተር ግሬግሰን ናንሲን ሳይውል ሳያድር ወደ ሳንፍራንሲስኮ እንድትልክለት ስለጠየቀ ማሪዮን ደስ ተሰኘች ። ሁለት ነርሶች ቀጥራ በአንደኛ ማዕረግ የጄት ጉዞ ነርሶቹ ይዘዋት ወደ ሳንፍራንሲስኮ እንዲንዙ ሁሉን ነገር ባንድ ቀን አዘጋጀች። ማሪዮን ስለወጪው ቅር አልተሰኘችም።

« መቼም የታደለች ልጅ ናት ማሪዮን » አለ ዶክተር ዊክፊልድ ማሪዮንን በአድናቆት እየተመለከተ ።
«ይመስለኛል » አለች ማሪዮን ። «አንድ ነገር . . . ይህን ጉዳይ ማይክል እንዲሰማ አልፈልግም ። ሰምተኸኛል ዊክ ?»
«አልገባኝም » አለ ዶክተር ዊክፊልድ ግራ እየተጋባ ።
«ለምን አይሰማም ? ለሚወዳት ልጅ እናቱ ያደረገችላትን ችሮታ የመስማት መብቱን መነፈግ አለበት እንዴ ?››
‹‹የለም የለም የለም ፣ መስማት የስበትም ። እንዲያውም ከሰማ ውሉን እሰርዛለሁ… የማሳከሙን ውል»
« አልገባኝም. . .»
«ይህ ጉዳይ ሚስጥር ሆኖ እንዲጠበቅ እፈልጋለሁ ። ከሁለታችን ማለፍ የለበትም። ማለትም ካራታችን ፣ ካንተ ፣ ከኔ ከሷና ከግሬግሰን ። ማይክል ይህን ነገር መስማት አይኖርበትም ። አያስፈልገውም ። ነፍሱን እንዳወቀ ፈጽሞ ስለናንሲ ማንሳት የለብህም እንዲረበሽ አልፈልግም ። »

በሀሳቧ፣ ቢሻለውና ነፍሱ መለስ ብትል ነው ያውም…አለች ሌሊቱን ሙሉ አጠገቡ ቁጭ ብላ ነው ያደረችው ። ከናንሲ ጋር ከተደራደረች በኋላ ነፍሷ በጣም ስለተደሰተች እንቅልፏም አልመጣባት ። ድካምም አልተሰማት ። ያደረገችው ነገር ትክክል እንደሆነ አምና ነበርና ። ደጋግማ አስባበት ፤ አምናበት ነበር። ለሁለቱም ሕይወታቸው የደስታ እንዲሆን ነው ያደረግሁት ። እሱም ነፃ ወጣ ። እሷም ትድናለች ። እያለች ደጋግማ ስታስብ አደረች ። « እንግዲህ አንዲት ቃል ላንናገር ተስማምተናል ። አይደለም እንዴ ሮበርት ? » አለች ማሪዮን ። ሮበርት ብላ ጠርታው አታውቅም ነበር ።
«መነገር የለበትም ካልሽ እኔ የምናገርበት ምንም ምክን ያት የለም »
«ደግ እንደሱ ነው»

የአምቡላንሱ በር ተዘጋ ፤ ሁለቱ ነርሶችና ናንሲ ከገቡ በኋላ ። ናንሲ ሕክምናዋን በምታካሂድበት ጊዜ ነርሶቹ ቋሚ አስታማሚ ሆነው ስድስት ወር ሙሉ አብረዋት ሊቆዩ ተቀጥረዋል ። ከስድስት ወር በኋላ ግን ነርሶቹ እንደማያስፈልጉ ግሬግሰን ገልፆላቸዋል ። ከስድስት ወር ፤ ጨመርም ቢል እስከ ሰባት ወር ድረስ… የፊት አጥንቷን ሽፋሽፍቶቿንና ሽፋሎቿን እንዲሁም አፍንጫዋን ማስተካከልና መትከል ስላለበት አይኖቿ በፋሻ መታሰራቸው አይቀርም ። በዚያ ጊዜ ሰው ያስፈልጋታል" ነርሶች ማለት ነው ። ግሬግሰን እንዳለዉ ፊቷ እንደገና እንደ አዲስ ነው የሚታነጸው ። ስለዚህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ወጭው ብዙ ነው። ለምሳሌ አንድ የአእምሮ ሀኪምም ያስፈልጋታል ። በየጊዜው ሊያነጋግራትና በአዲሱ ሰብእናዋ እንድታምን ሊያደርጋት ይገባል ። ለዚያም መክፈል ያለ ነው ። ግሬግሰን ይህን ሲያስረዳ…
«አዲስ ሰው መሆኗ አይቀርም ። ምክንያቱም ያጣችውን ነገር ሁሉ ፤ማለት በመንፈስ ያጣችውን… ለመመለስ አዳጋች ነው። አዲስ ሰብእናዋን እንድትቀበል ማድረግ ይኖርብናል » ብሏ.ል ። ይህ ደሞ ማሪዮንን በጣም ነበር ያስደሰታት ። ምክንያቱም ይህ ከሆነ ናንሲ ከማይክል ጋር ያላትን ግንኙነት ልትቀጥል አትደፍርም ማለት ነው ብላ ስለገመተች ነበር ። ማን ያውቃል ? ድንገት ሊገናኙ ይችላሉ ። አውሮፕላን ማረፈያ ላይ ሰው ይገናኛል ። ወይም ሆቴል ውስጥ ወይም ድንገት እመንገድ ላይ . . . ድንገት ። ይህ ደግሞ ለማሪዮን ደግ ነገር ሆኖ ሊታያት አይችልም ።

ግሬግሰን በጣም ግልፅና ሥራውን አጠናቆ የሚያውቅ ባለሙያ ሲሆን እድሜውም በአርባና በሃምሳ ዓመት መካከል ነው። ዝናው በመላው ዓለም ታውቋል ። እንዲህ ያለ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ( የአካል መልሶ መተካት ቀዶ ህክምና ) ሙያ ያለው ሰው ነበር ናንሲን ያጋጠማት ። የታደለች ልጅ ነች አለች ማሪዮን በሀሳቧ ። በውሉ ላይ የናንሲ ምቾት የሚጠበቅበት ሁኔታ ሁሉ አብሮ ገብቷል ። የሚመች መኖሪያ መከራየት አለባት ። ከላይ ያልናቸውን ወጪዎች ጨምሮ ጠቅላላ የተከፈለው አራት መቶ ሺ ዶላር ነበር ። ውሉ ሲታተም ማሪዮን አላንገራገረችም ። ገንዘቧን ለምታ ስቀምጥበት ባንክ ደውላ የተባለውን ያህል ገንዘብ ወደሚፈልገው ባንክ በስሙ እንዲዛወርለት የምታደርግ መሆኑን ወዲያውኑ ገለፀች ።
«ነገ ጠዋት በሶስት ሰእት ሄደህ ብትጠይቅ ገንዘቡን በስ ምህ ገቢ ሆኖ ታገኘዋለህ» አለች ማሪዮን ፒተር ግሬግሰን አልተጠራጠረም። ማሪዮን ሂልያርድ ማን እንደሆነች አሳምሮ ያውቃል ። ለመሆኑ ማሪዮንን የማያውቅ ማን አለ!

«ለምን አትመጪና ቁርስ አትቀምሽም ማሪዮን» አለ ዶክተር ዊክፊልድ ከሀሳቧ እየቀሰቀሳት ። ግራ ተጋብቷል ። ጆርጅ ኮሎዌይን ነበር የተማመነው ። እሱም እስከ ነገ ጠዋት ከኒውዮርክ መውጣት እንደማይችል ገልጾለታል ። ዶክተር ዊክፊልድ አላወቀም እንጂ እንዳይመጣ የከለከለችው ማሪዮን ነበረች።
«የምፈጽመው ጉዳይ ስላለ ብቻየን መሆን እፈልጋለሁ ። ስለዚህ መምጣት አያስፈልግህም » ብላ ። ሁሉም ነገር እንዳሰበችው ተሳካላት ። አሁን ደስ ብሏታል ።
« ማሪዮን »
‹‹እህ»
«ቁርስ እንዴት ነው ?»
«በኋላ ይሻለኛል ፤ ዊክ በኋላ ። አሁን ልግባና ማይክልን ልየው »
«እኔ አይቸው እመጣለሁ »
ዶክተር ዊክፊልድ ወደ ፎቅ ሲወጣ እሷ ወደ መጸዳጃ ቤት ጎራ አለች ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማይክል ወደተኛበት ክፍል ስትገባ ሁሉም ነገር ፀጥ ብሎ ነበር፡፡ ዶክተር ዊክፊልድ ዝም ብሎ አልጋ አልጋዉን ይመለከታል፡፡ ነርሷም የለች….
የጥዋት ጸሐይ በመስኮት ገብታ አልጋው ላይ አርፋለአች ከየት እንደሆነ እንጃ የተበላሸ ቧንቧ ይመስላል ውሀ ያለማቋረፍ ጠብ ጠብ ሲል ይሰማል ። ጸጥታው ታይቶ ፤ ተሰምቶ የማይታወቀውን ያህል ነበር ። ድንገት ልቧ ዘለለ ። ልቧ ዘልሎ ባፏ ሊወጣ ደረሰ… ልክ እንደያኔው ፤ ልክ ፍሬዲሪክ ሲሞት እንደሆነው ምነው አምላኬ!ምነው!እጅዋን ወደ ደረቷ ላከችው፣ልቧን ለመያገ ልቧን ይዛ እበሩ ላይ እንደቆመች የጨው አምድ መስላ ቀረች አይኗን ከዶክተር ዊክፊልድ ወደ አልጋው ፤ካልጋው ወደ ዶክተር ዊክፊልድ እያንከራተተች ባለችበት ድርቅ ብላ ቀረች እና አየችው ልጅዋን ማይክን። የለም እንደያኔው አይደለም።እንደ ፍሬዴሪክ አደለም ። እንባ ተናነቃት ።