Get Mystery Box with random crypto!

ልጅነት ሲመክር (በያስ ሁዳ) . . በሚኮላተፍ አንደበቱ እየተነጫነጨበት። ገና 5 አመ | 🍂ISLAMIC TEAM🍂

ልጅነት ሲመክር
(በያስ ሁዳ)
.
.
<<ሂድ ጥራት>>
<<ከዛስ>>
<<እወድሻለሁ በላት>>
<<አጎቴ ሀሚድ ይወድሻል ነው የምላት?>>
<<አይደለም። ነቢል ይወድሻል በላት>>
<<እህህ... ነቢልማ እኔ እኮ ነኝ>>
<<እኮ አንተ እኮ ነህ የምትወዳት። ታዲያ እኔ ነኝ እንዴ መታረቅ ያማረኝ?>>
<<እኔ አዎዳትማ... እኔ እንድታጫውተኝ ብቻ ነው የፈለኩት። አንተ ላስህ ሂድና <ነቢልን አጫውቺው> በላት። እኔ ስላት አትሰማም... እኔን አቶደኝም>> በሚኮላተፍ አንደበቱ እየተነጫነጨበት። ገና 5 አመቱ ነው፤ ትምህርት ቤት ምን ያህል ከጨዋታ እንደሚያቦዝን አልተረዳም። ለሱ ቤትም ሆነ ትምህርት ቤት ያው ነው፤ ጨዋታ...ምግብ... መኝታ። ለ9 አመቷ ሀናን ግን ህይወት ሌላ መስመር ይዛለች። ከትምህርት ቤት መልስ ወደ መድረሳ፤ ከደርስ ስትመጣ ወደ ጥናት... ለጨዋታ ያላት ቦታ እየደበዘዘ መጥቷል። ከማናችንም በላይ ግን ነቢል የእህቱ ጨዋታ መቀነስ ውስጡን ሰርስሮት ገብቷል፤ ሌላው ታሪክ አይመለከተውም ለእሱ ቀላሉ አማርኛ ስለማትወደው መሆኑ ብቻ ነው።

<<አሁንማ አስኮርፈሀታል እኮ። መጀመሪያ ሂድና ይቅርታ በላት። እሷ እኮ ሚሷ የቤት ስራ ስለሰጠቻት ነው። ካልሰራች ደግሞ ግርፍ ታደርጋታለች... እንጂ እኮ ትወድሀለች። ቶሎ በል ሮጥ በልና ከጀርባዋ እቅፍ አድርጋት ጎሽ... እሷ እኮ ሌላ ወንድም የላትም አታሳዝንም?>> አንጀቱን ለመብላት እየሞከርኩ። ትንሽ ካመነታ ቡኋላ እየሮጠ ሄዶ ከጀርባዋ አይኗን ያዛት።
<<እኔ ማነኝ?>> ሊሸውዳት ድምፁን ለማጎርነን እየታገለ።
<<እምም... ሀሚ ነህ?>> አውቃ ተታለለችለት፤ ሀናን። ነቢል ሙከራው የተሳካለት መስሎት ደስ አለው... ሳቁ ብፍ ብፍ ብሎ እያመለጠው <<አይደለሁም>> ጎርናናውን ቅላፄ ላለማጥፋት እየሰጋ። ትንሽ እንዲ ከተሸወደችለት ቡኋላ የራሱ ብልጠት ለራሱ አስገርሞት አይኗን ገለጠላት፤ እቅፍ አድርጋ ለደቂቃዎች እየኮረኮረች ስታስቀው ቆየች። በእህቱ ናፍቆት ተከፍተው ጠውልገው የነበሩት ጉንጮቹ የበሰለ ቲማቲም መስለው እስኪቀሉ ድረስ ሳቀ።

አይኖቼን ከነሱ ሳነሳ የኔዋ ከቅድሙ በተለየ መልኩ ታየችኝ። ፀጉሯ በሁለት ተጎንጉኖ ደረቷ ላይ አርፏል፤ ራሷንም በነጭ ጨርቅ ቢጤ ጠበቅ እድርጋ አስይዛዋለች። ፀጉሯን ለመሸፈን አልነበረም... ራሷን ስላመማት ነው። እድሜ ለኔ፤ ለትዕግስተ ቢሱ! በሰባሪ ቃላት ወርጄባት ስታለቅስ ነው የቆየችው። አይቼ የማልጠግባቸው ኮከብ መሳይ አይኖቿ ዛሬ በኔ ምክኒያት በእምባ ተሞልተዋል። እንደ አልቃሻ ህፃን ደጋግማ ጉንጮቿን በመዳፏ እያበሰች ሳያት እኔንም ሆድ ባሰኝ። አሁንም ግን እየሰራች ነው፤ በጎን እንግዶቹ የተመገቡበትን ሰሃን ታጥባለች። ዘወር ብላ ደግሞ ለልጆቹ መክሰስ የሚሆን እንቁላል ትጠብሳለች። ግን ምን ሆኜ ነው?

እለቱ እናቴና ሁለት እህቶቼን ምሳ የጠራሁበት ልዩ ቀን ነበር። እኔ ልጆቹን ትምህርት ቤት አድርሼ እስክመለስ እሷ ቤቱን ስታሰናዳና ስታበሳስል ቆየች። ለመውጣት ተዘጋጅቼ ስጠይቃት <<በ ግማሽ ሰዐት ውስጥ እጨርሳለሁ፤ አንተ ይዘሀቸው ስትመጣ ሁሉም ተዘጋጅቶ ይጠብቅሃል>> ነበር ያለችኝ፤ ዩስራ። እግረ መንገዴንም ወረገይነቦቹን ጠረጴዛው ላይ እንዳስቀምጥላት ጠይቃኝ አድርጌአለሁ። <ከዚህስ በላይ የሚያግዝ ባል ከወዴት ሊገኝ?> እያለ የሚፎክረውን ልቤን ገትቼ፤ በችኮላ... ያስለመድኳትን የፍቅር ስንብቴን እንኳን ሳልሰጣት ወጣሁ። ይሁን እንጂ ኡሚን፤ ዘይነብን አና ሩቀያን ይዤም ስመለስ እዛው ናት። ራሷን አትጠብቅም ብዬ ተናደድኩ፤ ግን ምናልባት ስለቸኮልንባት ይሆናል ብዬ ኡዝር ሰጠኋት።

ምሳው ደርሶ እስኪቀራርብ ድረስ ማዕድ ቤት ውስጥ መንጎዳጎዷን አላቆመችም። ኡሚ ማጉተምተም እና መከፋት ስትጀምር አየሁ... እነ ዚዚም ቢሆኑ ወጥታ እንድታጫውታቸው ከጅለዋል። በስተመጨረሻም ምሳው ቀረበ፤ እሷም ተጣጥባ እንደ ነገሩ ልብሷን ቀይራ መጣች። ምግቡ ሁሉ ማሻአላህ የሚጣፍጥ ሆኖ ሳለ ኡሚ የምትወደው ወርገይነብ ብቻ የተቸኮለበትና ያልበሰለ ነገር ሆነ። ኡሚ ካለሱ ምግብ ንክች እንደማታደርግ ታውቃለች... ከዚህ በፊት ሰርታልኝ ስቀምሰው እንዲህ ሆኖባት አያውቅም። ታዲያ የኔ ቤተሰቦች ሰለመጡ ነው ሙያው የሚጠፋት? ኡሚ ሰሀኗን ገፋ አድርጋ ተነሳች።
<<ምነው ማማ.. አልጣፈጠሽም? ወይ ሌላ ልስራልሽ በአላህ... እስከዛ ሌላውን ቀማምሺ>> ዩስሪ ነበረች።
<<አዪዪ... ፊቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ። ተይው አንቺም አትድከሚ፤ ከእናት ቤት ያልተማሩት ሙያ በአንድ ቀን ከየትም አይመጣም። ሩቂ ትሰራልኛለች።>> አኮረፈች።

ዩስሪ ንግግሩን ወደ ውስጧ ላለማስገባት ብላ ተነስታ ቡናውን ማቀራረብ ጀመረች፤ እነ ኡሚ ግን ካልሄድን ብለው ወጠሩን። ብንለምናቸው እምቢ አሉን፤ ሳምንታት የጠበቅነው ቀን ተበላሸ። ከሁሉም ግን ኡሚ ልትሄድ እየለባበሰች የተናገረቻት አንድ ቃል ጭንቅላቴን በጠበጠችው።
<<የአብራኬን ክፋይ ከሃዋው ጋር ሲደሰት ላየው እንጂ የተዘፈዘፈ ፊት ሊገርፈኝ አልመጣሁም። አንዴ እንኳን ተቀምጣ ልታጫውተኝ አላሰበች፤ አትምጡብኝ ማንን ገደለ ልጄ..>> አለችና አፉታዋን ሳትሰጠን ሄደች።

እነሱን ሸኝቼ ስመለስ ዩስሪ የቀራረበውን ቡና ስታነሳሳ አገኘኋት። አንድ ሁለት እያልን ብዙ ተናገርኳት፤ <<በእናትሽ ላይ የማታደርጊውን በኔ እናት ለምን?>> ብዬ ብዙ ወቀስኳት። ቤተሰቦቼን ስለማትወዳቸው ያመጣቸው ቸልተኝነት መስሎ ታየኝ። ዩስሪ ግን አሁንም ለቸልተኝነቷ ማብራሪያ መከራከሪያ ለማቅረብ አልፈቀደችም። እኔም እንደተበሳጨሁ ልጆቹን ከ ትምህርት ቤት ይዣቸው ተመለስኩ። ነቢልና ሀያት አላህ ይማረውና የወንድሜ ሰፍዋን ማስታወሻዎቼ ናቸው። ዩስሪን ሳገባ ጀምሮ አብረውን እየኖሩ 2 አመታትን አስቆጥረናል። እነሱን አሳታርቄ በተረጋጋ መንፈስ ሳያት ነበር ቀን የለበሰችውን አውልቃ ሀዘን ቤት መስላ መቀመጧን የተገነዘብኩት።

ቆይ ግን ምን ሆኜ ነው? ለምን የሷ ብቻ ጥፋት ታየኝ? አስር የምግብ አይነት ቀርቦ አንዱ መበላሸቱን አይታ የምትወቅሰውን እናቴን ብቻ ማዳመጤስ ለምን? እሷ እንደ እናቷ አላየቻትም የምለው... ኡሚስ በእርግጥ እንደ ልጇ አይታታለች? ለነገር ፍለጋ እንጂ ሩቂ ከሁቢ የተሻለ በተአምር እንደማታበስል አውቃለሁ፤ በሷ እጆች ለአመታት በልቻለኋ! ዩስሪ ሀናንን ሆና ሁላችንም ትንሹን ነቢል የሆንባት መሰለኝ። እኛ ያየነው ቀርባ አለማጫወቷን... ከኛ ጋር ሳቅ አለማድመቋን ብቻ ነው። ግን የተሰጣት የቤት ስራስ? የሚስትነት ሀቁንስ የት ጣልነው? ዱንያ ትምህርት ቤት ናት፤ ነገ ዓዲሉ ይፋረደናል... እሷንም ባጎደለችው ሀቅ እንዳይቀጣት መልፋቷ ጥፋቱ ምን ላይ ነው?

እንደ እናት አክብራ ቡናውን እያቀራረበችላት፤ ተራምዳ ለስድብ እመር ስትል ለምን እናቴን <ተይ> ማለት ተሳነኝ? ለምን ለነቢሎ እንዳልኩት <ስራ በዝቶባት ነው እንጂ ትወድሻለች> ብዬ አልተከላከልኩላትም? ዩስሪ ከኔ ውጪ ባል አላት እንዴ? ያኔ ከጋሼ አንገቴን አጎንብሼ ከወላጆቿ እቅፍ ሳወጣት እንደ አባት መከታ፤ እንደ ወንድም ጋሻ ልሆንላት አልነበረም? በወላጆቿ ቤት... እሷም እኮ እናት ነበራት - ስታለቅስ የምታባብላት። እሷም እኮ አባት ነበራት - ዝምቧን እሽ እንኳን ለማለት የማያስደፍር። እሷም እኮ ወንድም ነበራት- እንኳን ስድብ ሊወርድባት ፥ ቀልዳችን እንኳን ካልተመቻት አብሮ የሚከፋ። ታዲያ ላግባ ብዬ ስወስዳት እነሱን ሆኜ ልሞላላት አልነበረም? እኔ ግን አምጥቼ ለቤተሰቦቼ አጫዋችና ገረድ አደረግኳት። እንደ ህፃን...