Get Mystery Box with random crypto!

ከ400 ዓመት በፊት የተነገሩ አምስት ጠቃሚ የሕይወት ምክሮች ራስን ለመለወጥ የሚረዱ ምክሮችን | የስብዕና ልህቀት

ከ400 ዓመት በፊት የተነገሩ አምስት ጠቃሚ የሕይወት ምክሮች


ራስን ለመለወጥ የሚረዱ ምክሮችን ስናስብ ምናልባት ገበያውን የሞሉት አዳዲሶቹ መጽሐፍት ጠቃሚ ሊመስሉን ይችላሉ። ሁሌም ቢሆን ማንም ሰው ዘመናዊና አዲስ የሆኑ ነገሮችን በመጠቀም ራሱን መቀየር ይፈልጋል።

ነገር ግን ከብዙ ዘመናት በፊት የተጻፉ መጻሕፍት አሁን ላለንበት ዓለም ተግባራዊ መሆን ይችላሉ። 'ዘ አናቶሚ ኦፈ ሜላንኮሊ' የተባለው መጽሐፍ በአውሮፓውያኑ 1621 እንደተጻፈ ይነገራል። የዘመናዊውን ሰው አኗኗርና አስተሳሰብ ከዚህ መጽሀፍ በላይ የሚገልጽ ግን አልተገኝም።

በርተን እንግሊዛዊ ቄስና ምሁር ሲሆን ከ2 ሺ ዓመታት በላይ ግሪክ ውስጥ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ሕክምናዎችና እና ፍልስፍናዎችን አጠናቅሯል።

ይህ እንግሊዛዊ ምሁርና ቄስ ከፍተኛ ድብርትን ያውቀዋል። በዚህ ጉዳይ ዙሪያም በርካታ ሃሳቦችን አስቀምጧል። ነገር ግን የበርተን የሕይወት ስራዎች በዘመናዊው ሰው ሕይወት ውስጥ ድብርትና ሀዘንን እንዴት ይረዱታል?

ስኮትላንዳዊቷ ጋዜጠኛ ኤሚ ሎፕትሮት የበርተንን ስራዎች አጠናቅራ በድጋሚ በማዘጋጀት ለ21ኛው ክፍለዘመን ሰው በሚመች መልኩ አቅርባዋለች።

እሷ እንደምትለው በ1620ዎቹ ሰዎች ከድብርትና ሀዘን ለመላቀቅ ይወስዷቸው የነበሩ የመፍትሄ እርምጃዎች አሁንም ድረስ ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉ ናቸው።

1. የራሳችንን የስሜት መለዋወጥ በአንክሮ መከታተል

በድብርት አልያም በሀዘን ለሚሰቃይ ሰው የሚሰሙት ስሜቶች ምናልባት ያለምንም ምክንያት የሚሆኑ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ነገር ግን የሚሰሙን ስሜቶች የራሳቸው አካሄድ አላቸው።

ድብርት ተላላፊ በሽታ እንደሆነና ምልክቶቹም ሆነ የሚያሳርፉት ጫና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተወረስ እንደሚሄድ በርተን ያስብ ነበር።

ምናልባት ነገሮችን የተመለከተበት መንገድ የተለየ ሊመስል ቢችልም በዘመናዊው ህክምናም ብቸኛው ምክንያት ባይሆንም ድብርት ከቤተሰብ የሚተላለፍ እንደሆነ ተረጋግጧል።

"አንድ የቤተሰብ አባል በከባድ የድብርት በሽታ የሚሰቃይ ከሆነ መላው ቤተሰብ አብሮት ህክምናውን አብረውት እንዲከታተሉና ለራሳቸውም ነገሮችን እንዲያስተውሉ እፈልጋለሁ'' ይላሉ በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩት ዶክተር ፍራንሲስ ራይስ።

ነገር ግን ድብርት ከቤተሰብ ብቻ የሚመጣ ጉዳይ አይደለም። የተለያዩ ውጪያዊ ምክንያቶችም የራሳቸው አስተወዋጽኦ አላቸው። በርተን መጽሐፉን በሚያዘጋጅበት ወቅት ራሱ ላይ ያስተዋላቸውን ነገሮች ከግምት ውስጥ አስገብቷል።

በየጊዜው የሚቀያየር የደስታና ሀዘን ስሜቶች በዘመናዊው የህክምና ዓለም 'ባይፖላር ዲስኦርደር' የሚባል ሲሆን በርካቶችን የሚያጠቃ ነው።

በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሚሰሟቸውን ስሜቶች በአግባቡ መከታተልና ለምን እንደሚለዋወጡ ማወቅ ለድብርት ፍቱን መድሀኒት ተደርጎ ይወሰዳል። ምን ሲገጥመን የስሜት መለዋወጥ ውስጥ እንደምንገባ ማወቅ ከቻልን እነዚያን ነገሮች ማስወገድ ቀላል ነው።


2. የቀዝቃዛ ውሃ ጥቅም

በርተን በመጽሐፉ ላይ ከብዙ ዓመታት በፊት በሌሎች ሰዎች የተጻፉ የተለያዩ ሀሳቦችን አስፍሯል።

ንጹህ በሆነ ቀዝቃዛ ወንዝ ውስጥ ገላችንን መታጠብ ደግሞ በርተን ካስቀመጣቸው መፍትሄዎች መካከል አንደኛው ነው። ማንኛውም ሰው ረጅም ህይወት መኖር ከፈለገ በጣም በሚያምር ተፈጥሮአዊ ቦታ ላይ ገላን መታጠብ አንደኛው መንገድ ነው ይላል።

'' በቀዝቃዛ ውሀ ምክንያት ሰውነታችን የሚሰማውን ጭንቀት መቋቋም ካስለመድነው ሌሎች አስጨናቂ ነገሮችንም መቋቋም ይማራል'' ይላሉ በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ፖርትስማውዝ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ማይክ ቲፕተን።

3. ከተፈጥሮ አለመራቅ

ተፈጥሮ ለበርተን ከፍተኛ ድብርትን ለማባረር ቁልፍ ሚና የሚጫወት ነገር ነበር።

በተለይ ደግሞ በተፈጥሮአዊ ጫካ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አይነት እጽዋት ጭንቅላታችን ዘና እንዲል እና የሚያስጨንቁትን ነገሮች እንዲረሳ የማድረግ ከፍተኛ አቅም አላቸው።

በኦክስፎርድ ቦታኒክ ጋርደን ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሳይመን ሂሰኮክ እንደሚሉ አንዳንድ ተክሎች ድብርትን ለማከም ጭምር ጥቅም ላይ ይውላሉ።

በርተን ደግሞ አንዳንድ ተክሎች ስንመገባቸው ጭምር ድብርትና የማባረር አቅም ያላቸው ቢሆንም ተክሎቹን መመልከት በራሱ ድብርትን እና ጭንቀትን የማባረር አቅም አለው ይላል።

እንግሊዛዊው የእጽዋት ተንከባካቢ ሞንቲ ዶን እንደሚለው በከፍተኛ ሁኔታ በድብርትና ጭንቀት ተሰቃይቶ ነበር። ነገር ግን እጽዋትን መትከልና መንከባከብ ከጀመረ በኋላ ግን ነገሮች እየቀለሉ መምጣታቸውን ያስታውሳል።

''አንድ ተክል ከተተከለበት ጊዜ ጀምሮ እድገቱን መመልከትና መንከባከብ ለጭንቅላት የሚሰጠው ትልቅ እረፍት አለ'' ይላል።

4. ችግራችንን ለሌሎች ማጋራት

''በውስጣችን የሚሰማንን ጭንቀትና ድብርት ለራሳችን ብቻ ይዘነውና ተሸክመነው ከመቆየት ይልቅ ለሌሎች ማጋራትና አብሮ መፍትሄ መፈለግን የመሰለ ነገር የለም'' ብሎ ነበር በርተን ከ400 ዓመታት በፊት።

ጭንቀትና ድብርት የሚያጋጥማቸው ሰዎች ሁሌም ቢሆን ራሳቸውን ከሰዎች ለይተው መቀመጥ ይመርጣሉ። ነገር ግን መሰል ነገሮች እንደውም ጭራሽ ስቃዩን ያበዙታል።

በቤተሰብ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩት ዶክተር ፍራንሲስ ራይስ እንደሚሉት ጭንቀት ሲገባን ከምንወዳቸውና ከሚወዱን ሰዎች ጋር ዘና የሚያደርግ ነገር ማድረግና ችግራችን በዚያው ለእነርሱ ማጋራት በጣም ወሳኝ ነው።

''ምናልባት ከሰዎች ጋር ብዙም ማውራት የማንወድ እንኳን ቢሆን ከሰዎች ጋር ለየት ያለ ነገር ማድረግ ጭንቅላታችን ትኩረቱን ወደ ሌሎች ነገሮች እንዲያደርግ ያግዘዋል''

ጭንቀትና ድብርት አሰቃየኝ ብሎ አንድ ሰው ሐኪም ጋር ቢሄድ ምናልባት ድብርትን የሚያስወግዱ በርካታ አይነት መድሀኒቶች ሊታዘዙ ይችል ይሆናል። ነገር ግን በአሁኑ ሰአት እንደ ዴንማርክ፣ ካናዳ እና ዩኬ ባሉ አገራት መሰል ችግር የሚያጋጥማቸው ሰዎች ከመድሀኒት ይልቅ ከሰዎች ጋር እንዲገናኙ፣ አዲስ ክህሎቶችን እንዲማሩ አልያም ተፈጥሮአዊ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ነው የሚታዘዝላቸው።

5. ስራችንን እና ሕይወታችንን ማጣጣም

ምናልባት በርተን ቃል በቃል ስራችንን እና ሕይወታችንን ማጣጣም ብሎ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን አዲስ ነገር የመማር ፍቅር በሚል ገልጾታል። እንደውም ይህ የመማር ፍቅር በራሱ ከበዛ ችግር ሊሆን እንደሚችልም አስቀምጧል።

በርተን እንደሚለው ሕይወታችንን የምንመራበት ስራን ለማሳካት አልያም ምርምር ለማድረግ ይሁን ሙሉ ትኩረታችንን እና ጭንቅላታችንን በሙሉ እዛ ላይ ባደረግን ቁጥር ራሳችን ላይ ተጨማሪ ጭንቀትና ድብርት እንጨምራለን።

ሰዎች ስለስራቸው አብዝተው ሲጨነቁ እና ነገሮችን ለማስተካከል ሙሉ ጊዜያቸውን እዚያ ጉዳይ ላይ ባዋሉ ቁጥር ከሰዎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እየቀነሰ ይመጣል። የሚያስደስታቸውን ነገር ማድረግም ቢሆን ያቆማሉ።

ምናልባት በርተን የሰዎችን አስተሳሰብ የተመለከተበትና ያጠናበት መንገድ ያረጀ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እርሱ ተውሶ ያመጣቸው የግሪክ ፈላስፋዎች አስተሳሰብና ህክምናዎች አሁንም ድረስ ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉ ናቸው።

ራስን ማወቅ፣ መዋኘት፣ ተፈጥሮ፣ ማህበረሰብ እና ማንበብ ከዛሬ 400 ዓመት በፊት ከሰሩ አሁን ላይ ለእኛስ የማይሰሩበት ምክንያት አለ?

source -BBC News

የስብዕና ልህቀት
Join: @Human_Intelligence