Get Mystery Box with random crypto!

የአቶሚክ ልማድ አስደናቂ ሀይል ውጤቶችህ የልማዶችህ ቀሪ መለኪያዎች ናቸው፡፡ ያለህ ገንዘብ የፋይ | የስብዕና ልህቀት

የአቶሚክ ልማድ አስደናቂ ሀይል

ውጤቶችህ የልማዶችህ ቀሪ መለኪያዎች ናቸው፡፡ ያለህ ገንዘብ የፋይናንስ አጠቃቀምህ ውጤት ነው፤ እውቀትህም የመማር ልማድህ ቀሪ መለኪያ ነው።
በሕይወትህ ውስጥ ያሉት ምስቅልቅሎችም ነገሮችን የማጽዳት ልማዶችህ  ድምር ውጤቶች ነው።የምታገኘው የምትደጋግመውን ነው፡፡


የሕይወትህን መዳረሻ ለመገመት ከፈለግህ ማድረግ ያለብህ ነገር ቢኖር የምታገኛቸውንና የምታጣቸውን ጥቃቅን ለውጦች ተከትለህ ማየትና ይህ የለውጥ መስመር በሃያ - በሰላሳ ዓመታት የት እንደሚያደርስህ መረዳት ነው፡፡ የወር ወጪህ ከገቢህ ያነሰ ነው? በየሳምንቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትሰራለህ? በየቀኑ አዳዲስ ነገሮችን ታውቃለህ? መጽሐፍ
በጥቂቱም ቢሆን ታነባለህ? የወደፊት ሕይወትህን ሙሉ የሚወስኑት እንደነዚህ ያሉ ጥቃቅን የጦር ግንባሮች ናቸው፡፡

በሙሉ ጊዜ በውድቀትና በስኬት መካከል ያለውን ልዩነት ያሰላል፡፡ ጊዜ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የምትሰጠውን ነገር ማባዛት ነው፡፡ ጥሩ ልማዶች ጊዜን አጋርህ ሲያደርጉት፣ መጥፎ ልማዶች ግን ጠላትህ ያደርጉታል፡፡

ልማዶች በሁለቱም በኩል የተሳሉ ሰይፎች ናቸው፡፡ መልካም ልማዶች ሊስሉህና ሊያሳድጉህ የሚችሉትን ያህል መጥፎ ልማዶች ደግሞ ቆራርጠው ሊጥሉህ የሚችሉበት እድል በዚያው መጠን ነው፡፡
ለዚህም ነው ዝርዝሩን መረዳት ጠቃሚ የሚሆነው፡፡ ልማዶች እንዴት እንደሚሰሩና እንዴት ወደ ውጤት እንዲወስዱህ ማድረግ እንደምትችል መማር አለብህ፡፡ በዚህ መንገድ የሰይፉን ቆራጭ ስለት የማስወገድ እድል ታገኛለህ፡፡

ብዙውን ጊዜ ሁኔታ ቀያሪ ቅጽበቶች ቀደም ብለው የተሰሩ የብዙ ተግባራት ድምር ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ተደራራቢ ቅድመ ተግባራት ዋናውን ለውጥ ለማምጣት የሚያስፈልገውን አቅም ይገነባሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በሁሉም ቦታዎች የሚታይ ነገር ነው፡፡ ካንሰር የሕይወት ዘመኑን 80 በመቶ የሚያሳልፈው የማይታይ ሆኖ ነው፡፡ ከዚያ የሰውነትን አካል የሚቆጣጠረው ግን በወራት ውስጥ ነው፡፡ ሸምበቆም መሬት ለመሬት ስሮቹን በሚዘረጋባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ብዙም አይታይም፡፡ ከዚያ ነው በስድስት ሳምንታት ውስጥ በአየር ላይ እስከ 90 ጫማ ድረስ ማደግ የሚችለው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ልማዶችም የሆነ ወሳኝ ምዕራፍን አልፈን አዲስ ሁኔታ ውስጥ ገብተን እስክንገኝ ድረስ ምንም ለውጥ የሚፈጥሩ አይመስሉንም፡፡ በየትኛውም ሁኔታ መጀመሪያ እና መካከለኛ ዘመን ውስጥ ብዙውን ጊዜ የመከፋት ሸለቆ ይኖራል፡፡ ለውጥ ለማምጣት ስትነሳ የእድገት ደረጃዎችህን በማይቆራረጥ እና ወጥ በሆነ መልኩ ማየት እንደምትችል
ታስባለህ፡፡ ግን አታይም፡፡ በመጀመሪያዎቹ ቀናት፣ ሳምንታትና ምናልባትም ወራት አካባቢ ለውጥ የማይመጣ መስሎ መታየቱ በጣም የሚያበሳጭ ነው፡፡ የትም የምትሄድ መስሎ አይሰማህም፡፡ ይህ የየትኛውም የድርርቦሽ ድል መገለጫ ባህሪ ነው - ሁልጊዜም ትላልቅ ውጤቶች የሚመጡት ዘግይተው ነው፡፡

ዘላቂነት ያላቸውን ልማዶች መገንባትን ከባድ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ምክንያቶች መካከል አንደኛው ይህ ነው፡፡ ሰዎች ትናንሽ ለውጦችን ለማምጣት ይሞክሩና ውጤቱ ግን አልታይ ይላቸዋል፡፡ ከዚያም ለማቆም ይወስናሉ። “ለአንድ ወር ያህል በየቀኑ እሮጥኩ፤ እና ለምንድነው ሰውነቴ ላይ ለውጥ ያላየሁት?” ብለህ ልታስብ ትችላለህ፡፡ እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ አንድ ጊዜ ከተቆጣጠረህ ጥሩ ልማዶችን እየተውክ ለመሄድ ትመቻቻለህ። ትርጉም ያለው ለውጥ ለማሳየት ግን ልማዶችን ለረዥም ጊዜ ማቆየትና ጉብታውን ለማለፍ የሚያስችላቸው አቅም ማጠራቀም አለባቸው፡፡ እኔም የተዳፈነ ችሎታ ጉብታ (The plateau of atent potential) የምለው ይሄንን ነው፡፡

ጥሩ ልማድ ለመገንባት ወይም መጥፎ ልማድ ለመተው ስትታገል ራስህን ብታገኘው የመሻሻል አቅም አጥተህ እንዳይመስልህ፡፡ ይልቁንም እንደዚህ የሚሆነው ገና የተዳፈነው ችሎታህን ጉብታ ስላለፍክ ብቻ ነው፡፡ “ጠንክሬ ብሰራም ውጤት አላመጣሁም አይነት አቤቱታ “በረዶው ለምን በ26፣ በ27 ወይ በ28 ዲግሪ አልቀለጠም?” ብሎ ቅሬታ እንደማቅረብ ያለ ነው፡፡ ድካምህ አልባከነም፣ እየተጠራቀመ ነው እንጂ፡፡ ሁሉም ድካሞችህ ተደማምረው 32 ዲግሪ ላይ ውጤት ማሳየት ይጀምራሉና፡፡

በስተመጨረሻ የእምቅ ችሎታ ጉብታህን ስታልፍ ሰዎች ስኬትህን የአንድ ቀን ስኬት ብለው ይጠሩታል፡፡ የውጪው ዓለም ሁሉንም የለውጥ ደረጃዎችህን አያይም፡፡ ሰዎች ማየት የሚችሉት ድራማዊ የሆነውን የለውጡን ፍሬ መገለጫ ብቻ ነው፡፡ አንተ ግን ለዚህ ያበቁህ ምንም ለውጥ እያሳየህ በማይመስል ሰዓት ሁሉ የሰራሀቸው ጠንካራ ስራዎች መሆናቸውን ታውቃለህ፡፡

ሁሉም ትላልቅ ነገሮች የሚነሱት ከትናንሽ ጅማሮዎች ነው፡፡ የእያንዳንዷ ልማድ ዘር አንዲት ትንሽ ውሳኔ ነች፡፡ ይህች ውሳኔ ስትደጋገም ግን ልማድ እያደገና እየጠነከረ ይሄዳል፡ ስሮቿ እየተስፋፉ ይሄዱና ቅርንጫፍ ማውጣትም ትጀምራለች፡፡
የእምቅ ችሎታ ጉብታን አልፎ ለመሄድና በሌላው ጎን ለመገኘት የሚያስችለንን የጥንካሬ ትግል ቆይታ የሚወስነው ምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች የመልካም ልማድን ድርርቦሽ ትርፍ ሲያጣጥሙ አንዳንዶች ግን የመጥፎ ልማዶቻቸው ምርኮኛ ሆነው የሚቀሩትስ ለምንድን ነው?

ይቀጥላል

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence