Get Mystery Box with random crypto!

ትናንሽ ልማዶች ትልቅ ልዩነት ይፈጥራሉ። Atomic Habit ደራሲ- ጄምስ ክሊር ትርጉም-ድረስ ጋ | የስብዕና ልህቀት

ትናንሽ ልማዶች ትልቅ ልዩነት ይፈጥራሉ።
Atomic Habit
ደራሲ- ጄምስ ክሊር
ትርጉም-ድረስ ጋሻነህ

የአንድን ወሳኝ ቅጽበት ሚና ከፍ አድርጎ ማየትና በየቀኑ የሚደረጉ የጥቃቅን መሻሻሎችን ሚና ዝቅ አድርጎ ማየት ይቀለናል ፡፡ ብዙውን ጊዜ ትልቅ ስኬት ትልቅ አድርገን ራሳችንን ተግባርን እንደሚፈልግ እናሳምነዋለን፡፡ ክብደት መቀነስም ይሁን ትልቅ ቢዝነስን መገንባት፣ መጽሐፍ መፃፍም ይሁን ውድድርን ማሸነፍ ወይም የትኛውንም ሌላ ግብ ለማሳካት ሁሉም ሰው የሚያወራለት አይነት መሬት የሚያንቀጠቅጥ ትልቅ ነገርን መስራት እንዳለብን በማመን ራሳችንን እናጨናንቃለን፡፡


ጥቃቅን ነገሮችን በአንድ በመቶ ማሻሻል ግን የማንመኘው ለእይታም የማይገባ ነገር ነው፡፡ ይሄኛው አይነት የመሻሻል መንገድ ግን ከፍተኛ ውጤት የማምጣት አቅም አለው - በተለይ በረዥም ጊዜ፡፡ ትንሽ ለውጥ በጊዜ ሂደት የምታመጣው ልዩነት አስደናቂ ነው፡፡ ሂሳባዊ ስሌቱ ይሄን ይመስላል፡፡ ለአንድ ዓመት ሙሉ በቀን 1 በመቶ እያሻሻልን ብንሄድ በአመቱ መጨረሻ መጀመሪያ ከነበርንበት በ37 በመቶ እንሻሻላለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በቀን በአንድ በመቶ ወደታች እየሄድን ለአንድ ዓመት ከቆየን ወደ ዜሮ አካባቢ እንደርሳለን፡፡ በጥቂት ጅማሮ የተጀመረች ቀጣይነት ያላት ትንሽ መሻሻል ተጠራቅማ ታሪክ ትሰራለች፡፡

ልማዶች ራስን የማሻሻል ድርብርብ ድርብርብ ወለዶች (compound interests) ናቸው፡፡ በድርብርብ ወለድ ራሱን በሚያበዛበት ልክ ገንዘብ መጠን የልማዶች ውጤትም በደጋገምናቸው መጠን ይባዛል። በየቀኑ ተነጥለው ሲታዩ የሚፈጥሩት ለውጥ በጣም ጥቂት መስሎ ቢታይም በወራት ወይም በዓመታት ቆይታ የሚያመጡት ለውጥ ግን አስደናቂ ነው፡፡ የመልካም ልማዶች ጠቀሜታዎች እና የመጥፎ ልማዶች ጉዳቶች ግልጽ ብለው የሚታዩት ከአምስት ወይም ከአስር ዓመታት በኋላ ወደኋላ ዞር ብለን ስንመለከታቸው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ይህንን ነገር በየቀኑ ሕይወታችን አንጥረን ለማየት ከባድ ነገር ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ እነዚህን አይነት ለውጦች መተውና መናቅ ይቀናናል፡፡ ዛሬ ላይ ጥቂት ገንዘብ መቆጠብ ብትችል አሁኑኑም ሚሊየነር አትሆንም፡፡ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ጂም ብትሰራ በአካል ቅርፅህ ላይ ምንም ለውጥ አታይም፡፡ ዛሬ ምሽት ፈረንሳይኛ ቋንቋን ለሶስት ሰዓታት ብታጠና የቋንቋው ተናጋሪ አትሆንም፡፡ ጥቃቅን ለውጦችን ለማምጣት እንሞክራለን፡፡ የለውጡን ውጤት ቶሎ ማየት ስለማንችል ግን ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለሳለን፡፡

መጥፎው ነገር ደግሞ ይህ የለውጡ ውጤት የሚታይበት ፍጥነት እጅግ ዘገምተኛ መሆን ለመጥፎ ልማዶች እንድንመቻች የሚያደርገን መሆኑ ነው፡፡ ዛሬ ምሽት ቤተሰቦችህን ተወት አድርገህ ስራ ላይ ብታሳልፍ ይረዱሃል፡፡ ሥራህን የምትጨርስበት ሰዓት ለነገ ብለህ ብታሳድረው ለዚህ የሚሆን ጊዜ “ነገ ላይ አይጠፋም፡፡ በዚህ መንገድ አንዲትን ውሳኔ መተው ብዙም ከባድ ነገር አይደለም፡፡

መጥፎ ውሳኔዎችን በየቀኑ ችግሮቻችንን በ1% እያባባስን፣ እየደጋገምን፣ ትንንሽ ስህተቶችን እየሰራን እና ጥቃቅን ምክንያቶችን እያበጀን ከሄድን ግን ድምር ውጤታቸው እጅግ የገዘፈ እና የከፋ ይሆናል፡፡ ችግር የሚዳርጉንም እዚህም  እዚያም የምንስራቸው ችግሮቻችንን በ1% የማባባስ ስራዎቻችን ድምር ውጤቶች ናቸው

በልማዶቻችን ላይ በምናመጣቸው ጥቃቅን ለውጦች የምናመጣው ጠቅላላ . ውጤት የአውሮፕላንን የበረራ መስመር በጣም በትንሽ ዲግሪ በመቀየር እንደሚመጣው ለውጥ ያለ ለውጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሎስ አንጀለስ ወደ ኒው ዮርክ እየበረርክ ነው እንበል፡፡ ከላክስ አየር ማረፊያ የተነሳውን
አውሮፕላን ፓይለቱ በ 3.5 ዲግሪ ወደ ደቡብ ቢቀይረው መዳረሻህ የሚሆነው ኒው ዮርክ ሳይሆን ዋሽንግተን ዲሲ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ትንሽ ለውጥ ስትነሳ አካባቢ አይታወቅህም፡፡ የአውሮፕላኑ አፍንጫም አቅጣጫውን የሚቀይረው በጣም በትንሽ ጫማዎች ናቸው፡፡ ጉዞው መላው አሜሪካን ሲያካልል ግን መዳረሻህ መጀመሪያ ካሰብከው ቦታ በመቶዎች በሚቆጠሩ ማይሎች ርቀት ላይ ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በየቀኑ በልማዳችን ላይ የምናሳያቸው ጥቃቅን ለውጦች ሕይወታችንን ፍፁም የተለየ መዳረሻ ይስጡታል። በ1% የተሻለ ወይም በ1% የወረደ ውሳኔን መስጠት ትርጉም ሊኖረው የሚችል ለውጥ አይመስለንም፡፡ በጊዜ ሂደት ግን አሁን አንተ በሆንከው እና አንተ ትሆን በነበረው ማንነት መካከል ያለውን ልዩነት የሚፈጥሩት እነዚህ ጥቃቅን ልዩነቶች ናቸው፡፡ ስኬት የ በየቀኑ ልማዶች ድምር ውጤት ነው፡፡ ወሳኙ ነገር ልማዶችህ ወደ ስኬት የሚወስዱህ ናቸው ወይስ አይደሉም? የሚለው ነው፡፡

ስለሆነም አብዝተህ መጨነቅ ያለብህ ዛሬ ላይ ስላመጣኸው ውጤት ሳይሆን የዛሬው ጉዞህ አቅጣጫ ላይ ነው፡፡ የወጪ አወጣጥ ልማድህ ካልተቀየረ ጥሩ ነገር አትጠብቅ፡፡ በተቃራኒው ዛሬ ላይ ደሃ ብትሆንም ሽርፍራፊ ሳንቲሞችን የምትቆጥብ ከሆነ ግን ወደ የፋይናንስ ነፃነት የሚወስደው መንገድ ላይ ነህ - ከምታስበው በላይ በዝግታ ብትጓዝም፡፡

ይቀጥላል

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence