Get Mystery Box with random crypto!

ሃይማኖቱን እንኳ ተዉለት !! ዮናስ ዘውዴ በዓለም ከድካም በቀር ምንም ላልተረፈው፤የዕለት ተዕለት | የስብዕና ልህቀት

ሃይማኖቱን እንኳ ተዉለት !!
ዮናስ ዘውዴ

በዓለም ከድካም በቀር ምንም ላልተረፈው፤የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ለማሸነፍ ብርቱ ትግል ለሚያደርገው መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮችን ለሟሟላት ብቻ ሲለፋ ዘመኑን ለሚፈጀው፤ ቢከፋው ቢያዝን፣ቢመረው በምድር ምንም መጽናኛ ለሌለው፣ ለዚህ ምስኪን ሕዝብ ልቡ ሲበርደው አንጀቱ አልችል ሲለው የሚጽናናበትን ሃይማኖት እንኳ ተዉለት እንጂ።

በብዙ መከራ ውስጥ ለሚያልፍ ከፀሐይ በታች ሁሉም ዓይነት የመከራ ዶፍ ለዘነበበት፤ አለኝ ብሎ የሚማጸንበትን፤ ይኽን ዓለም የሚንቅበትን የተጓደለበትን ምድራዊ ፍትሕ በትዕግሥት እንዲያሳልፍ እንዲያሳልፍ ምክንያት የሆነውን እምነቱን እንዴት አይተዉለትም?

እንደ ሕዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል፣ በቋንቋው ተሰዷል፣በሰውነቱ ተጎሳቁሏል በቅድመ አያቶቹ ታሪክ ምንም የማያውቀው ሰው፤ ላልነበረበት ጊዜ በመካካሻነት በጠላትነት እየተፈራረጀ እንዲኖር ተፈርዶበታል ይኽ በሕዝቦች መካከል የተዘራ እንክርዳድ ነው። በፓለቲካው ዓለም በጸብ ለሚነግዱ አካላት ይኽ እንክርዳድ እንደትልቅ የኃይል መሣርያ በማገልገል ዘልቋል።

ሃይማኖት ግን መነካት የሌለበት እሳት ነው። ሃይማኖት የምትጫወትበት ምድራዊ እሳት አይደለም።ለሚያምኑት የመለኮት እሳት ነው፡፡ ከቅጽሩ ወዳልተቀደሰ የፖለቲካ ሜዳ ልታወጣው ብትሞክር ቅድሚያ የሚፈጅህ አንተኑ ነው። ሃይማኖት ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ሕዝብን ከሕዝብ አንድ አድርጎ አያይዞ በኅብረት አቆይቷል።

ፈርሀ እግዜርም ከትውልዱ ላይ እንዳይጠፋ ግብረገብን በማሥረጽ moral compass ሆኖ ያገለገለውም ሃይማኖት ነው። ኅሊናውን በጥላቻ የታወረ ሰው ሊገድልህ ቢመጣ ቢያንስ በእግዜር በጌታ በማርያም በአሏህ በዋቃ ብቻ በፈጠረህ ትለዋለህ፡፡ እንደ ሕዝብ ተከባብረን የኖርነው የሠለጠነ ሕግና ሥርዓት ስላለን አልነበረም። ይልቁንም በፈጠረን አምላክ በኩል አንድ እንደሆንን ስለሚሰማን ነበር፡፡ እንደ ሕዝብ የሥልጣኔ ታሪክ ቢኖረንም ቅርብ ጊዜ ያስተናገድናቸው ቀውሶችና የሰማናቸው ዜናዎች ባለአእምሮዎች ለመሆን ብዙ እንደሚቀረን ሥልጡን ነን ብለን የምንመጻደቀውን ያህል ሥልጡን እንዳልሆንንይናገራሉ።

የትምህርት የጤና የፍትሕ ሥርዓቶቻችን በስብራት የተሞሉ ናቸው። ምንን ተማምነን ምንን እንደምናፈርስ አናውቅም። በርሀብ ብዛት ከአንጀቱ የተጣበቀ ሆዱ እስኪቀደድ ድረስ እያከከ የፒያሳን ወርቅ ቤቶች ያለስርቆት ውልብታ ደክሞት የሚደገፍ የኔቢጤና ምንዱባን ያላጣነው በእንተ ስማ ለማርያም ብሎ የሚላስ የሚቀመስ በማምሻ እንደማያጣ ተስፋ ስለሚያደርግ ነው። እንጂማ የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውንም እስከ መብላት ይደርሳል።

የሃይማኖትን አንድነትን የነጠቅከውን ሕዝብ በምን አንድ ታደርገዋለህ? ነገ ከነገ ወዲያ የእንትን ክልል እግዜር ከእንትን ክልል እግዜር ጋር ኅብረት እንደሌለው በግልጽ የሚሰበክበት ጊዜ ይመጣል። የሃይማኖት አንድነትን ማዳከም (ሲዳከምም በዝምታ ማየት እያደር ቅጥ ላጣ ዓለማዊነት፣ ግብረሰዶማዊነት አውሮፓ እየተሰቃየ ላለበት ስመሥልጣኔ በሽታና ውጥንቅጥ ሁሉ በር እንደመክፈት ነው። በቀሪው ዓለም ሲቀደስባቸው የነበሩ ትላልቅ ካቴድራሎች መጠጥ ቤትና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ሆነዋል።


በክርስትና ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ወንድም ሴትም የለም ሁላችንም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ነን። በላ 8:27:28) ክርስቶስ በሞቱ ያላስታረቀው የለም። አንድ በየቀኑ አባታችን ሆይ ጸሎቱ ይቅር በለን:: እኛም የበደሉንንይቅር እንደምንል እያለ የሚጸልይ ሰው እንዴት እና ከመቼው? የሀጢአት ማወራረድ ውስጥ ይገባል? በክርስቶስ ስም የተመሠረተች ቤተክርስቲያንን ለመከራ አዲስ አይደለችም። የመከራ ዘመናቶች አሏት።ነገርግን ክርስትና ሥር የሚሰደው ደግሞ በመከራ ውስጥ ነው ሊቁ ጠርጡለስ The blood of the Martyrs is the seed of the church? ይላል። ሰማዕታት የቤተክርስቲያን ምርጥ ዘርናቸው። በዚህ ሁሉ መሃል ግን ቤተክርስቲያንን የነኳት ኔሮን እና ማርከስ ኦሬሊየስ የት ናቸው?

ቤተክርስቲያን ግን ይኸው አለች ትኖራለችም ይኽች ቤተ ክርስቲያን በየሆስፒታሉ ለወደቁ ሕሙማን በየወኅኒው ለታሰሩ አርሰው ዝናብን ለሚጠብቁ በስደት በሰው ሀገር ላሉ ለአእዋፋትና አራዊት ይልቁንም ደግሞ ስለአገር ሰላም ሌሊት ተቀን የምትጸልይና የምትማልድ እመቤት ናት። በደመራ ዕለት እና በጥምቀት ዕለት ብቻ ሳይሆን በመከራዋ ቀን የሚመጡላት እልፍ ልጆች አሏት። ኖረው ብቻ ሳይሆን ሞተው የሚያከብሯት አዕላፍ ልጆች አሏት። የድረሱልኝ ጥሪዋን ሰምተው ልጅ የእናቱን ድምፅ ሰምቶ እንደሚገሰግስ በጓቿ ድምፃን ሰምተው በቅጥር ግቢዋ ይሰበሰባሉ በክንፎቿ ይጋረዳሉ ይጋርዱማል።

ቤተክርስቲያን ሆይ እንደ አንድ ዜጋ በአንቺ ወቅታዊ ጉዳይ ከመጨነቅ የሚይዘኝ ነገር የለም፡፡ እናም ስለ ሰላምሽ እጸልያለሁ።

አገሬ ሆይ እንደ አንድ ከምድርሽ እንደ በቀለ ዜጋ በአንቺ ወቅታዊ ጉዳይ ከመተከዝ የሚይዘኝ ነገር የለም። እናም ስለሰላምሽ አጥብቄ አነባለሁ

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence