Get Mystery Box with random crypto!

በምንም ነገር አልገደብም !!! ገና በ19 ወሯ በደረሰባት የትኩሳት በሽታ ራሷን የሳተችው ሄለን | የስብዕና ልህቀት

በምንም ነገር አልገደብም !!!

ገና በ19 ወሯ በደረሰባት የትኩሳት በሽታ ራሷን የሳተችው ሄለን ኬለር፣ ወዲያውኑ የማየቷንና የመስማቷን ብቃት ተነጠቀች፡፡ ስለሄለን ስናስብ የሚያስገርመን ማየትና መስማት የተሳናት ሴት መሆኗ አይደለም፡፡ በሁኔታዋ ሳትበገር የመጀመሪያዋ ማየትም መስማትም የማትችል የዲግሪ ተመራቂ፣ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ፣ ጸሃፊ . . . ለመሆን መብቃቷ ያስገርመናል!!! ለዚህ ያበቃትን አመለካከቷ በአጭር ቃል ስታስቀምጠው፣ “ውስንነቴ ላይ አተኩሬ አላውቅም፣ ልቤንም በኃዘን አይሞሉትም፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ ናፍቆቶች ቢመጡብኝም . . . እጅግ በጣም ስስ ስሜቶች ናቸው”፡፡

ሄለን ኬለር በውስንነታቸውና በገደባቸው ላይ ለሚያተኩሩ ሰዎች ካስተላለፈችው ብዙ መልእክቶች መካከል . . .  

“የራስን ሁኔታ እያዩ ሲያዝኑና ከንፈር ሲመጥጡ መኖር ክፉ የተባለው ጠላታችን ነው፡፡ ለዚህ ጠላት ራሳችንን አሳልፈን ከሰጠነው በዚህ ዓለም ውስጥ ምንም ጥበብ የሞላው ነገር ማድረግ አንችልም” – Hellen Keller
አንተ “ጎዶሎዬ ይህ ነው” ብለህ ከምታስበው ሁኔታህ እጅግ የባሰ ሁኔታ ውስጥ እያለ የተሟላ ሕይወት የሚኖር ሰው እንዳለ ላስታውስህ፡፡ በአንጻሩም፣ ሙሉ፣ ስኬታማና ደስተኛ ሆኜ ለመኖር ይህኛውና ያኛው ያስፈልኛል ብለህ የምታስባቸውን ነገሮችና ከዚያም በላይ እያላቸው በጣም አሳዛኝና ያልተሟላ ሕይወት የሚኖሩም ሰዎች እንዳሉም ላስታውስህ፡፡

“አንገትህን በፍጹም አታቀርቅር፡፡ ሁል ጊዜ ቀና በል፡፡ ይህችን አለም አይን አይኗን ተመልክተሃት በድፍረት ኑር”
– Hellen Keller

ያለህ ነገር ወይም ሁኔታህ ሌላው ሰው ካለው ነገርና ሁኔታ ቢያንስም እንኳ፣ ሰው መሆንህ ግን ከማንም አያንስም፡፡ ክብርህ ያለው ሰው የመሆንህ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የገጠሙህን ሁኔታዎች ተጋፈጣቸው፣ ቀና ብለህ ለመኖርም ወስን፡፡ በዚህች ምድር ላይ ያለ ጀግና እስካሁን ምንም ክፉ ያልገጠመው ወይም ጎዶሎ ነገር የሌለው ሰው አይደለም፣ ጀግናው ከገጠመኞቹ አልፎ የሚሄደው ሰው ነው፡፡

“የእኛን ሁኔታ ከእኛ የተሻለ ነገር አላቸው ከምንላቸው ሰዎች ጋር ከማወዳደር ይልቅ፣ በተግዳሮት ውስጥ ካሉት ከብዙሃኑ ጋር ብናወዳድረው ምን ያህል ከታደሉት መካከል እንዳለን ይገለጥልናል”– Hellen Keller


የስብዕና ልህቀት
@Human_Intelligence