Get Mystery Box with random crypto!

በዕውቀት ዘመን በህዝብ ፈቃድ መተዳደር እንጂ መገዛት የለም! ድሮ ድሮ አብዛኛውን የዓለም ሐገራት | የስብዕና ልህቀት

በዕውቀት ዘመን በህዝብ ፈቃድ መተዳደር እንጂ መገዛት የለም!

ድሮ ድሮ አብዛኛውን የዓለም ሐገራት ይመሩ የነበሩት በጎበዝ አለቆች ነበር፡፡ ያኔ መሪ ማለት ባለመሣሪያና በስልጣኑ ላይ የሚቀናቀነውንና የሚጠላውን የሚገድል ነበር፡፡ በዛ ዘመን ጊዜ ያጀገናቸውና ዕድልና አጋጣሚ የፈጠረላቸው ጉልበታቸው ሃይላቸው የሆኑ ሠዎች ሐገርና ሕዝብን ከጉልበታቸው ስር አንበርክከው ለዘመናት በክርናቸው ገዝተዋል፡፡

ተገዢው የዓለም ህዝብ ለብዙ ዘመናት ከእንደዚህ ዓይነት አንባገነን ጭቆና ለመላቀቅና ነፃነቱን ለመጎናፀፍ በተለያየ የጭቆና አገዛዝ ቀንበር ውስጥ ሆኖ ትግሉን አላቋረጠም ነበር፡፡ በትግሉም ስንቱ አጥንት ከስክሷል፣ ደሙንም አፍሷል፣ ስንቱ ሕይወቱን፣ ልጁን፣ አባቱን፣ እናቱን፣ ዘመዱን፣ ንብረቱን፣ ጥሪቱን ወዘተ ገብሯል፡፡

ያ ቅስም ሠባሪ፣ ተስፋ አስቆራጭ፣ አድካሚና ስቃይ የተሞላው ትግል የስንቱን ህይወት ቀጥፎ ዛሬ ፍሬ አፍርቷል፡፡ ብዙዎቹ የዓለማችን ሐገራት ከጉልበት ብዝበዛ፣ ከአንባገነን አገዛዝ ተላቀዋል፤ እየተላቀቁም ይገኛሉ፡፡

ዛሬ መሪ ማለት በእውቀት ከፊት የሚቀድም እንጂ ከኋላ ሆኖ በጭቃ ጅራፍ የሚገርፍ አይደለም፡፡ መሪነት በእውቀት መሻል፣ በሐገር ፍቅርና በቅንነት መርቀቅ፣ ለፍትህና እና ለነፃነት ዘብ መቆም እንጂ ለራስ ጥቅም ብቻ አርበኛ መሆን አይደለም፡፡ ይሄ ዘመን ህዝብን በእውቀት አሳምኖ እንጂ በማስፈራራት ለሚገዛው መሪ ቦታ የለውም፡፡ የአሁኑ ትውልድ በፍትህና በነፃነት፤ በእኩልነትና በክብር፤ በምክንያትና በዕውቀት እንድታስተዳድረው እንጂ ቀጥቅጠህ #በአድሎና #በነሲብ እንድትገዛው አይፈልግም፡፡

አሁን በመሪህ መገዛት የለም መተዳደር እንጂ፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ የሐገር መሪዎች ህዝብን ሊያገለግሉ እንጂ ሊገለገሉበት እንዳልሆነ የተረዱበት ዘመን ቢኖር አሁን ብቻ ነው፡፡ ማንም መጥቶ የሕዝብ አናት ላይ ወጥቶ እንዳሻው ሊዘውረው የማይችልበት ዘመን ላይ ደርሠናል፡፡ ጊዜ ዳኛ! አጃኢብ ጊዜ!

ለዚህም ነው ማሕተመ ጋንዲ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ላይ ሆኖ ለሐገሩ ሕንድ ዘመኑን የቀደመ ንግግር የተናገረው፡፡ አባባሉም እንዲህ የሚል ነበር፡-

.......‹‹ከዕለታት አንድ ቀን ሕዝብን መምራት ማለት በጡንቻ መጠቀም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሕዝብን መምራት ማለት ከሕዝብ ጋር አብሮ ለመሄድ መቻል መሆኑ ታይቶኛል፡፡››....... ነው ያለው፡፡ ድንቅ ንግግር!

በዕውቀት ዘመን በህዝብ ፈቃድ መተዳደር እንጂ መገዛት የለም!

እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)

የስብዕና ልህቀት
@Human_Intelligence
@Human_Intelligence