Get Mystery Box with random crypto!

ብቃትን ፍለጋ! አንድ ጊዜ ፈጣሪ ሰውን ያላካተተ ስብሰባን ጠራና ፍጥረትን ሁሉ ሰብስቦ አንድን ጥ | የስብዕና ልህቀት

ብቃትን ፍለጋ!

አንድ ጊዜ ፈጣሪ ሰውን ያላካተተ ስብሰባን ጠራና ፍጥረትን ሁሉ ሰብስቦ አንድን ጥያቄ ጠየቃቸው፣ ይላል አንድ ምንጩ ያልታወቀ አፈ-ታሪክ፡፡

ጥያቄው እንዲህ የሚል ነበር፡-

“ለነገሩ ዝግጁ እስኪሆኑ ድረስ አንድን ነገር ከሰው ልጆች ልሰውርባቸው እፈልጋለሁ፡፡ ስለሆነም ያንን ከሰዎች ለመሰወር የምፈልገውን ነገር የት ባስቀምጠው ሰዎች ላያገኙት የሚችሉ ይመስላችኋል?” አላቸው፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ብዙም የደፈረ እንስሳ ማግኘት ከባድ የነበረ ቢሆንም አራት እንስሶች የየግል ሃሳባቸውን ሰነዘሩ፡፡

ንስር እንዲህ አለ፡-

“ከሰዎች ለመሰወር የፈለከውን ነገር ለእኔ ስጠኝና ከፍ ብዬ መብረር ስለምችል ጨረቃ ድረስ ይዤው እወጣና እዚያ አስቀምጠዋለሁ”፡፡ ፈጣሪም መልሶ፣ “አንድ ቀን የሰው ዘር ጨረቃ ላይ የመውጣት ብቃት ስለሚኖረው ማግኘታቸው አይቀርም” አለው፡፡

አሳ እንዲህ አለ፡-

“እንደ ውቂያኖስ ጥልቅ ነገር እንደሌለለና ሰዎች እዚያ ጥልቀት ድረስ እንደማይሄዱ አውቃለሁና እኔ በዋና እዚያ ድረስ መጥለቅ ስለምችል ይዤው ልግባና እዚያ አስቀምጠዋለሁ”፡፡ ፈጣሪም መልሶ፣ የሰው ልጅ ወደጠለቀው ባህር የመግባት አቅም ለማዳበር ብዙ ጊዜ ስከማይፈጅበት ማግኘቱ አይቀርም” ብሎ መለሰ፡፡

አንበሳ በተራው እንዲህ አለ፡-

“እንኳን ሰው አብዛኛዎቹ የዱር እንስሶች እንኳ የሚፈሩት ጥቅጥቅ ያለውን ጫካ የምደፍር እኔ ነኝ፡፡ እዚያ ወስጄ ባስቀምጠው ስለማያገኙት ለእኔ ስጠኝ”፡፡ ፈጣሪም፣ “ሰዎች ጫካን መመንጠር ብዙም ስለማይከብዳቸው ቀስ በቀስ ይደርሱበታል” አለ፡፡

ጦጣ በመጨረሻ እንዲህ አለች፡-

“ፈጣሪ ሆይ፣ ከእነዚህ ሁሉ ሃሳብ ሰጪዎች በበለጠ ሁኔታ ከሰው ጋር ቀረብ ብዬ የምኖረው እኔ ስለሆንኩኝ ባህሪያቸው በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ ሰዎች አብዛኛውን ነገር ፍለጋ ውጪ ውጪውን ነው የሚሉት፡፡ ውስጣቸው ያለው ነገር ትዝም አይላቸው፡፡ ስለዚህ ውስጣቸው ብታስቀምጠው በቀላሉ አያገኙትም” አለችው፡፡

የጦጣ መልስ ተቀባይነት ስላገኘ ፈጣሪ ለመደበቅ ያሰበውን ነገር በሰው ውስጥ አስቀመጠው ይባላል፡፡ ይህ የተደበቀው ነገር የራሳቸው የሰዎቹ እምቅ ብቃት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በውስጣቸው ፈጣሪ ያስቀመጠው አስገራሚና የታመቀ ብቃት እያላቸው ምንም እንደሌላቸው በከንቱ ጊዜያቸውን ያባክናሉ፡፡

በውስጣችሁ ተዝቆ የማያልቅ እምቅ ብቃት እንዳለ ታውቃላችሁ? ፈልጋችሁ አግኙት! አውጡት! አዳብሩት! ተጠቀሙበት!


ዶ/ር እዮብ ማሞ
የስብዕና ልህቀት
@Human_Intelligence
@Human_Intelligence