Get Mystery Box with random crypto!

ጀልባዎቻችሁን አቃጥሉ! እ.ኤ.አ. በ 1519 #Hernan Cortes  የሚባል አንድ አሳሽ  (e | የስብዕና ልህቀት

ጀልባዎቻችሁን አቃጥሉ!

እ.ኤ.አ. በ 1519 #Hernan Cortes  የሚባል አንድ አሳሽ  (explorer) ስድስት መቶ ከሚጠጉ ሰዎቹ ጋር አስራ አንድ መርከቦችን በመምራት በዚያን ጊዜ የታወቀና እጅግ የበለፀጉ ሀብቶች በብዛት የሚገኙበት መሬት ለመቆጣጠር ወደ ሜክሲኮ አቀና።  

ምኞቱ ከሠራዊቱ ቁጥር እጅግ የላቀ ነበር።  85,000 ስኩዌር ማይል የሚሸፍነውን ከ5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያለውን የአዝቴክ ኢምፓየር ግዛት በሙሉ ለመቆጣጠር ነበር። 

ነገር ግን አንድ ችግር ነበር -  ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ብዙ ቢሞክሩም ማንም ሊያሸንፈው ያልቻለ አንድ ጠንካራ ሰራዊት ይህን ሀብት ይጠብቅ ነበር።

ነገር ግን ይህ ሰራዊት በሜክሲኮ ድንበር ላይ ሲያርፍ ኮርቴስ ለሰዎቹ አንድ ነገር አዘዘ - “ጀልባዎቻችሁን አቃጥሉ!”  የሚል ቆፍጠን ያለ ትእዛዝ። 

ሰራዊቱም ትእዛዙን ተቀበለ።  

የእሱ ሰዎች ሁለት ምርጫዎች ብቻ ነበራቸው:-  ‘ጦርነቱን ማሸነፍ’ - ወይም ‘መሞት’!

ለማፈግፈግ ወይም ለማምለጥ ምንም እድል ስላልነበራቸው በሕይወታቸው ውስጥ በጣም ትልቅ ድፍረት የሚጠይቀውን ውጊያ ተዋጉ - እናም አሸነፉ።   

ድል አድራጊዎቹ ኮርቴስና የእሱ ሰዎች ነበሩ። በህይወት ዘመናቸው ተጠቅመው ሊጨርሱት የማይችሉትን ሀብትም ማግኘት ቻሉ። 


ይህ ታሪክ መመለስ የማትችልበትን ነጥብ፣ ወደ ኋላ የማትሻገርበትን መስመር እንዳቋረጥክ የምታውቅበት የስነ-ልቦና ቁርጠኝነትን ይወክላል። በዚህ መስመር ምንም አጥር የለም፣ ትከሻህን ማየት የሚባል ነገር የለም።  አሁን ሁሉም ነገር በዚህ አዲስ እውነታ ውስጥ ስኬታማ መሆን ላይ ብቻ ማተኮር ነው። 

በህይወት ውስጥ ወደኋላ ማፈግፈግ አማራጭ ባይሆን ኖሮ በየቀኑ ምን ያህል ማደግና ወደህልምህ መቅረብ ትችል ነበር? 

‘ጀልባዎችህ እየተቃጠሉ መሆናቸውን’ ብታውቅ፤ ምን ያህል ከፍታ ላይ ትደርሳለህ፣ ምን ያህል ትደፍራለህ፣ ምን ያህል በታታሪነት ትሰራ ነበር፣ ምን ያህል ህልምህን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ ትሆን ነበር?

ብዙ ጊዜ፣ አዲስ እና አስፈሪ ነገርን ለመሞከር ስናስብ በ"ህይወት አድኖቻችን" ላይ የሙጥኝ እንላለን። ለምሳሌ:- የራሳችንን የግል ንግድ ለመገንባት እየፈለግን ነገር ግን በቅጥረኝነት ህይወት ላይ ልንቆይ እንችላለን ወይም የዕለት ተዕለት ተግባራችንን ሁልጊዜ በህይወታችን ለማድረግ የምንፈልጋቸውን ታላላቅ ነገሮች ላለመሞከር እንደ ሰበብ ልንጠቀም እንችላለን።  

ከፊታችን ያለው መንገድ ግልጽ ባይሆንም እንኳ በሕይወታችን ውስጥ ወሳኝ የሆነውን ውሳኔ መወሰን የሚያስፈልገን ጊዜ አለ።  የምትችለውን  ያህል መረጃዎችን  ሰብስቡ፣ ስጋቶችህን  ለያቸው/ለካቸው። ከዚያም ራስህን ወደፊት ለማራመድ የራስህን ምርጥ ውሳኔ ወስን።   ለአንድ ነገር ቃል ከገባህ በኋላ ከእሱ ጋር ለመጣበቅ ፍቃደኛ ሁን። 

ፍርሃትህ ማሳካት የምትፈልገውን ትልቁን የህይወትህን ህልም እንዲያሳጣህ አትፍቀድ። ‘እንዲህ ቢፈጠረስ? እንዲህ ቢሆንስ፣ እንዲህ ባይሆንስ.....?’’ ... እያልክ ራስህን ሽባ አታድርግ።  በትልቁ የሕይወት ግብህና ስኬታማ ለመሆን በሚያስፈልጉህ እርምጃዎች ላይ ብቻ አተኩር። 

እርግጥ ነው! የደህንነት መረቦች እና የማምለጫ መንገዶች ከህመም እና ጉዳት ይጠብቁናል። ነገር ግን ወደ ትልቁ የህይወት ግባችን ለመድረስ የምናደርገውን ጥረት፣ ትኩረት እና ቁርጠኝነት ይቀንሱታል ወይም ያጠፉታል። 

ለማድረግ ያሰብከው ወይም ‘አንድ ቀን አደርገዋለሁ’ እያልክ ማሳካት የምትፈልገው፤ ነገር ግን ረጅም ጊዜ በውስጥህ ተዳፍኖ የተቀመጠ ህልም  አለ?  ውስጣዊ ድምጽህን እመነው!  ህልምህን ተከታተል! 
ጀልባዎችህን አቃጥል! 
ወደኋላ አትመልከት!
ወደፊት ብቻ!!!

የስብዕና ልህቀት
@Human_Intelligence