Get Mystery Box with random crypto!

ለጊዜ ተዋቸው! (Samuel Geda) በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ነበር። ታ | የስብዕና ልህቀት

ለጊዜ ተዋቸው!

(Samuel Geda)

በአንድ ትንሽ መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ነበር። ታዲያ ይህ ሰው፣ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በኑሮው ከሚገጥመው ችግር የተነሳ፣ ሁልጊዜም በህይወቱ ደስተኛ አልነበረም። አንድ ቀን ግን ከሚኖርበት ሥፍራ በቅርብ ርቀት የምትገኝ ከተማ ዘንድ፣ አንድ ታላቅ የኃይማኖት አባት ከአጃቢዎቻቸው ጋር እንደመጡ ይሰማል። ይህን ጊዜም እኚህን አባት ማግኘት አለብኝ ብሎ ይወስናል።

በመሸም ጊዜ እኚህ አባት ያሉበት ሥፍራ ይደርስና፡ እሳቸውን ለማግኘት ቁጭ ብሎ መጠባበቁን ይይዛል። ከረጅም ቆይታ በኋላም እኒያን አባት ያገኝና ጥያቄውን ይጀምራል። "አባቴ ሆይ፥ በህይወቴ ፍፁም ደስተኛ አይደለሁም፤ በቃ ሁሌም በችግር የተከበብኩኝ ሰው ነኝ... በዚህ በኩል የሥራ ጭንቀት፣ በዚህ ደግሞ የጤና ቀውስ፣ በዛላይ የቤቴ ውስጥ ችግር... ብቻ ተደማምሮ እረፍት ነስቶኛል፣ ደስታም ርቆኛል፤ እባክዎትን አንዳች የመፍትሄ ሀሳብ ይስጡኝና፡ ደስተኛና የሰላም ኑሮ እንድኖር ይርዱኝ!"

ሽማግሌውም ፈገግ ብለው፤ "ልጄ፥ ለችግርህ ነገ ጠዋት ላይ መፍትሄ እሰጥሃለሁ፤ ነገር ግን አሁን ባዝህ፣ ጥቂት የኔን ሥራ ልትሠራልኝ ትችላለህን?፤ ሰውዬውም በዚህ ይስማማል። እሳቸውም ቀጥለው፦ "በጉዞአችን የያዝናቸው መቶ ግመሎች በዚህ ይገኛሉ፤ እናም ዛሬ ምሽት የነርሱን ነገር፡ አደራውን ላንተ ሰጥቻለሁ፤ ሁሉንም ግመሎች እመሬት ላይ ካስቀመጥክ በኋላ ወደ መኝታ መሄድ ትችላለህ"። ይህንንም ብለው ወደ ድንኳናቸው ሲያቀኑ፣ ሰውዬውም የታዘዘውን ሊያደርግ ምሽቱን ግመሎቹ ዘንድ አመራ።

በቀጣይ ቀንም ሽማግሌው ማልደው ወደ ሰውዬው በማቅናት "ልጄ፥ ሌሊቱን ጥሩ ተኝተህ አደርክ?" ብለው ይጠይቁታል። ሰውዬው ግን ኅዘን በተሞላበት ስሜት ሆኖ "አባቴ፥ ለዐፍታ እንኳን እንቅልፍ ሳይወስደኝ ነው ሌሊቱ የነጋው። ብዙ ለፋሁ፣ ብዙም ጣርኩኝ፡ ይሁንና በአንድ ጊዜ ሁሉንም ግመሎች እንዲቀመጡ ማድረግ አልቻልኩም። አንዳንዶቹ ራሳቸው ይቀመጣሉ፤ አንዳንዶቹ ግን ላስቀምጣቸው ብሞክርም እንኳን አይቀመጡም፤ አንዱ በዚህ በኩል ሲቀመጥ፡ በሌላ በኩል ያሉት ይነሣሉ"።

ይህን ጊዜ ሽማግሌው ፈገግ እያሉ እንዲህ አሉ፦ "ካልተሳሳትኩኝ፡ ይህ የሆነው ትላንት ማታ ነው አይደል?"

- ራሳቸውን በራሳቸው ያስቀመጡ ብዙ ግመሎች ነበሩ!?

- ብዙዎቹ ደግሞ በአንተ ጥረት ሊቀመጡ ችለዋል!?

- ቀሪዎቹ ልታስቀምጣቸው ሞክረህ እንኳን አልተቀመጡም፤ ከቆይታ በኋላ ግን በጊዜ ውስጥ ራሳቸውን አስቀምጠው አግኝተሃቸዋል!?

ሰውዬውም፦ "አዎ! አዎ!...ትክክል!" ብሎ መለሰ።

ሽማግሌውም ቀጠሉና፦ "ስለዚህ አሁን አንድ ነገር ተረዳህን?፤ በህይወት ያሉም ችግሮች እንዲሁ ናቸው...

- አንዳንዶቹ በራሳቸው መፍትሄ ያገኛሉ።

- አንዳንዶቹ በአንተ ጥረት መፍትሄ ያገኛሉ።

- አንዳንዶቹ ደግሞ በአንተ ጥረት እንኳን አይፈቱም፤ እነዚህን ችግሮች ለጊዜ ተዋቸው። ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ በራሳቸው ይፈታሉና/መፍትሄ ያገኛሉና/።

ትላንት ማታ፣ ምን ያህል ብትሞክር በአንድ ጊዜ ሁሉንም ግመሎች ማስቀመጥ እንዳልቻልክ ትምህርት ወስደሃል። አንዱን ግመል በዚህ ጋር ስታስቀምጥ በሌላ በኩል ያሉት ይነሣሉ። ልክ እንዲሁ፤ እዚህ ጋር አንዱን ችግር ፈታሁ/ተፈታ ስትል እዛ ደግሞ ሌላ ችግር ተነስቶ ይጠብቅሃል። ህይወት እንዲህ ነውና!። ችግሮች የህይወት አካል ናቸው፤ አንዳንድ ጊዜ ጥቂት፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ በርካታ ችግሮች ይኖራሉ። ይሄ ማለት ግን ስለነሱ ሁሌ ማሰብ አለብህ ማለት አይደለም። እነሱን ለጊዜ እየተወክ ወደፊት ተጓዝ። በእያንዳንዱ እርምጃም ወደ ዓላማ-ህይወት (Purpose of life/self- realization/) ማደግን ተማር።

ልብ በል፤

• አንዳንድ ጊዜ፤ ደስታን ለማወቅ በኅዘን፣ ዝምታን ለማድነቅ በጩኸት፣ የመኖርን ዋጋ ለማወቅ ባለመኖር መንገድ ልታልፍ ግድ ነው።

ይኸውልህ፤ ህይወት በተቃርኖ የተሞላች ነች። እያንዳንዱ ስኬት ከሸክም ጋር ነው የሚመጣው። ትልቅ ቤት ማግኘት ስኬት ሲሆን፣ ብዙ የሚጸዳ መኖሩ ሸክም ነው። ልጅ መውለድ ስኬት ሲሆን፣ በእኩለ ሌሊት መነሳቱ ሸክም ነው። ባለስልጣን መሆን ስኬት ሲሆን፣ የህዝብን ጩኸት ማስተናገዱ ሸክም ነው።

ብዙ ጊዜ የምንሠራው ስህተት- ስኬቱን ያለ ሸክም ከመፈለግ የሚመጣ ነው። ይህ ግን እውነታው አይደለም። የሚመጡት በጥቅል (package) ነው። ዋናው ነገር፣ ሸክሙም እያለ በስኬቱ/በበረከቱ መደሰትን መማሩ ላይ ነው!!

ሰናይ ምሽት

የስብዕና ልህቀት
@Human_Intelligence