Get Mystery Box with random crypto!

ማንነት-ፍሮይድ በተለያዩ ቀናት፣ በተለያዩ ሳምንታት ወይም በተለያዩ አመታት ውስጥ የተለያዩ ማንነ | የስብዕና ልህቀት

ማንነት-ፍሮይድ

በተለያዩ ቀናት፣ በተለያዩ ሳምንታት ወይም በተለያዩ አመታት ውስጥ የተለያዩ ማንነቶች እንዳሉህ ተሰምቶህ አያውቅም? በአንደኛው ቀን ጨዋታ ወዳድ ተጫዋች ትሆንና በሌላኛው ቀን ቁጥጥርን የሚያበዛ ቁጡ ሰው ትሆናለህ፡፡ ሲግመንድ ፍሮይድ ስለ ባህሪ መለዋወጥ የሚለን ነገር አለ፡፡
ከእርሱ በፊት ስለ ሰው ልጆች ስነ-ልቦና ያጠና የለም ባንልም ፍሮይድ ግን በእጅጉ በተለየ ሁኔታ ተመራምሯል እና ዛሬም ድረስ የምንከተላቸውን የሳይኮሎጂ አስተምህሮዎችን ፈልስፏል።
ፍሮይድ የእኛ ማንነት በሶስት ይከፈላል ይለናል፡፡

#ኢጎ; ይህ አሳቢውና ምክንያታዊው ማንነታችን ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ የሚያነበውና በአእምሮህ ውስጥ የሚተርክልህም ይህ የማንነት ክፍልህ ነው፡፡ ከሶስቱ ማንነቶችህም በመሃል ላይ ይገኛል።


#ኢድ; ይሄኛው የእንስሳነት ባህሪህን ያጎላዋል፡፡ ወሲባዊ ፍላጎቶችህ፣ በስሜትህ የምትመራባቸው ውሳኔዎችህ እና ሌሎችም ግልፍተኛ ድርጊቶችህ በዚህ የማንነት ክፍልህ ይመራሉ። ልክም እንደ ሰይጣን ሆኖ ውሳኔዎችን እንድትወስን ያጣድፍሃል። የሰደበህን ሰው እንድትደበድብ ወይም ድንጋይ እንድትወረውርበት ያበረታታሃል። ልክ ህጻን ልጅ ሲርበው እንደሚያለቅሰው ይህ ማንነትህ ድርጊቶችህ ስለሚያስከትሉት ውጤት
ሳይጨነቅ ምሱን እንድታመጣለት
ያለቅሳል።

#ሱፐር_ኢጎ; ይህ በአእምሮህ የተቀመጠ ዳኛ ነው፡፡ እንዲህ አታድርግ ነውር ነው፤ ይህን ማድረግህ አንተን እንድትዋረድ ያደርግሃል እያለ ሃሳቦችህ እና ድርጊቶችህ ላይ ሂስ ይሰጣል፡፡ ስለ ማህበረሰቡ ህግ እና ከድርጊትህ በኋላ ስለሚከሰት መጥፎ ነገር አበክሮ ይጨነቃል። ይህ ልክ ነው፤ ይህ ልክ አይደለም እያለ ይመክርሃል።

ለምሳሌ ለፈተና ልታጠና ተቀመጥክ፡፡ ኢድ መጨናነቅ አይወድም፤ እናም በቀስታ ፈታ በል አትጨናነቅ ይልሃል። ወይ ስልክህን አንድታነሳና ፌስቡክ እንድትጠቀም አልያም ከጓደኞችህ ጋር ሄደህ እንድትዝናና ይመክርሃል።

ሱፐር ኢጎ፤ ከኢድ በተቃራኒ፣ ነገሮችን አጋኖ እና መጥፎ አድርጎ ያቀርብልሃል። ዛሬ ካላጠናህ ፈተና ትወድቃለህ፤ ፈተናንም ከወደቅክ ይህን አመት ትደግማለህ... እያለ ያስፈራራሃል።

በመሃል ወይም ምክንያታዊ ማንነትህ ለማስታረቅ ይመጣል፡፡ ራሴን እስክጥል ድረስ መጨናነቅ የለብኝም፤ ሆኖም ግን ለአንድ ሰዓት ያህል አጥንቼ ወደ ጫወታ እሄዳለሁ ይላል፡፡

ፍሮይድ የማንነት ቀውስ የሚመጣው ሶስቱን አጣጥመን ሳንሄድ ስንቀር ነው ይለናል። ሰካራም፣ ሴሰኛ ሰው አይተህ ታውቃለህ ይሄ ሰው የኢድ (የእንስሳነት) ማንነቱ በርትቶበታል፡፡ በተቃራኒው ስለ ሁሉም ነገር የሚጨነቅ እና ፍጹም ለመሆን የሚጥር ሰው ያውቃል? ቋጣሪ፣ ጥንቁቅ አልያም አብዝቶ የሚጨነቅ ይሆናል ... ይህ ሰው የሱፐር ኢጎ (የዳኛው) ማንነት በርትቶበታል፡፡

ሁሌም ቢሆን በሁለቱ ማንነቶቻችን ውስጥ እንዳንዋጥ ራሳችንን ልንቆጣጠረው ይገባል፡፡ ነገር ሁሉ በጊዜው እና በአግባቡ ሲሆን ያማረ ይሆናል። ጠቢቡ ሰለሞን እንዳለው፡-
“ለማልቀስ ጊዜ አለው፥
ለመሳቅም ጊዜ አለው፤
ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥
ለመዝፈንም ጊዜ አለው።“

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence