Get Mystery Box with random crypto!

እውነታን የመቀበል ምርጫ አንደኛው ምርጫህ በየጊዜው በመንገድህ ላይ የሚደነቀሩ በፍጹም ልታስወግ | የስብዕና ልህቀት

እውነታን የመቀበል ምርጫ

አንደኛው ምርጫህ በየጊዜው በመንገድህ ላይ የሚደነቀሩ በፍጹም ልታስወግዳቸው የማትችላቸውን እንቅፋቶች ሲታገሉ መኖር ነው፡፡ ሌላኛው ምርጫህ ግን እውነታን ተቀብለህ፣ ዝንባሌህንና መንገድህን በመቀየር መገስገስ ነው፡፡

ታሪኩ ከተከሰተ ትንሽ ሰንበት ብሏል፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1989 ዓ/ም በጸሐፊነቱና በቀስቃሽ ተናጋሪነቱ የታወቀው ዴኒስ (Dennis Waitley) ከሺካጎ ከተማ ወደ ሎስ አንጀለስ የሚሄደውን የበረራ መስመር ቁጥር 191 ለመያዝ በመንገድ ላይ እንዳለ ትንሽ በመዘግየቱ ምክንያት በረራው ለጥቂት ያመልጠዋል፡፡ በአየር ማረፊያው ደርሶ ለመግባት ሲጣደፍ አይኑ እያየ የመቀበያውን ደጆች ሲዘጉት ተመለከተ፡፡ የዘገየው ለጥቂት በመሆኑ ምክንያት ወደ በረራው ለመግባት እንዲፈቀድለት ቢማጸንም እንኳን ስላልተፈቀደለት በጣም ይበሳጫል፡፡ በዚያው ቀን ከምሳ በኋላ ዋና ተናጋሪ ሆኖ ሊቀርብበት የሚገባው ስብሰባ ቀጠሮ በዚህ ምክንያት ተበላሸበት፡፡

ከአካባቢው ዘወር በማለት በመነጫነጭ ላይ እያለ፣ ከሃያ ደቂቃዎች በኋላ አንድ ሰበር ዜና ቀልቡን ይስበዋል፡፡ ለጥቂት ያመለጠው በረራ ገና በመነሳት ላይ አያለ በመከስከሱ በውስጡ ያሉት ሰዎች በሙሉ መሞታቸውን ተመለከተ፡፡ ንዴቱና ቅሬታው ወደ ድንጋጤ፣ ወደ ኃዘንና በኋላም “በረራው እንኳን አመለጠኝ” ወደሚል ሃሳብ ተለወጠ፡፡

ከአየር ማረፊያው ወትቶ ሆቴል በመያዝ ወደ ክፍሉ ገብቶ አረፍ ለማለት ሞከረ፡፡ በእጁ ላይ ያለውን የበረራ ትኬት በመመለስ ገንዘቡን ከመቀበል ይልቅ ትኬቱን ለማስታወሻነት ለማስቀመጥ ወሰነ፡፡ ይህ ትኬት የዘወትር አስታዋሹ ሆነለት፡፡ በአንድ ነገር በሚበሳጭበት ጊዜ ሁሉ ባለቤቱ እጁት ትይዘውና ወደዚያ ለማስታወሻነት ወደተቀመጠ የበረራ መስመር ቁጥት 191 ትኬት በመውሰድ ሁሉም ነገር ለመልካም እንደሆነ ታስታውሰዋለች፡፡

ዴኒስ፣ “እያንዳንዱ ቀን በሙሉ ኃይላችን ልንኖረው የሚገባን ስጦታ ነው” ሲል ይደመጣል፡፡ በዚህም መልእክቱ፣ መለወጥ የማንችለውን እውነታ ከመታገል ይልቅ ለመኖር ስለተፈቀደልን ደስተኞች ልንሆን እንደሚገባን ያስታውሰናል፡፡

ልክ እንደ ዴኒስ ምንም ብታደርግ ልትለውጣቸው የማትችላቸው “አናዳጅ” ገጠመኞች ዘወትር ከመንገድህ ላይ አይጠፉም፡፡ እነዚህ በየጊዜው መንገድህ ላይ የሚደነቀሩና ካሰብከው ሩጫ የሚገቱህ ገጠመኞች የሚሰጡህ ያለመመቸት ስሜት ወደ ስሜታዊነትና በዚያም ስሜታዊነት ተነድቶ ውሳኔን ወደመቀያየር ቀጠና የሚያስገባህ ከሆነ የጥሩ ምርጫ ሰው አይደለህም፡፡ ይህ አይነቱ የየእለት ገጠመኝና “እንቅፋት” በተገቢው ሁኔታ ካልተያዘ ለዋና ዋና የሕይወት አቅጣጫዎችህ እንቅፋት የሚሆንን ምላሽ እንድትሰጥ ሊጋብዝህ ይችላል፡፡

አንተ ከተረጋጋህና ከአቅምህ በላይ የሆኑትን ነገሮች ለፈጣሪ መልቀቅ ከተማርክ አንዳንድ እድል እንኳን አመለጠኝ . . . አንዳንድ ሰው እንኳን ከድቶኝ ሄደ . . . አንዳንድ የጀመርኩት ነገር እንኳን አልተሳካ . . . አንዳንድ ፍቅረኛ እንኳን እምቢ ብሎኝ ሄደ . . . የምትልበት ቀን ሊመጣ እንደሚችል ላስታውስህ!

“ምርጫና ውሳኔ” ከተሰኘው የዶ/ር
ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ

በቅንነት ሼር ያድርጉ

Join: @Human_Intelligence
Join: @Human_Intelligence