Get Mystery Box with random crypto!

ኢትዮጵያውያን ምን ሆነን ነው ? --------------------------------------- | የስብዕና ልህቀት

ኢትዮጵያውያን ምን ሆነን ነው ?
---------------------------------------

አንድ ገብረ ጉንዳን ከሌላ ገብረ ጉንዳን ጋር በቅንጣቢ ሥጋ ወይንም አጥንት “እኔ ልብላ፤ እኔ ልብላ” በማለት ቡድን ለይተው አይጫረሱም። ወይንም በአንድ ቀፎ የሚኖሩ የንብ መንጋዎች ከሌላ ቀፎ ከሚኖሩ የንብ መንጋ ጋር በሚቀስሙት አበባ ወይንም በሚቀዱት ውሃ ተጣልተው ተቧድነው ሲጠፋፉ አናይም።

ለዚህም ዋንኛው ምክንያት ከሰው ልጅ በስተቀር የተቀረው ሥነ ፍጥረት በሥርዓት የሚመራበት ሕገ ህላዌ በዘረመሉ (DNA)ውስጥ ተቀርጾበት መገኘቱ ነው። በዘረመላቸው በታተመባቸው ቅመም (DNA code) መሠረት አለቃ እና ምንዝሩ፣ ንጉሡ እና ሠራተኛው ተናበው እና ተሳስበው እንዲሁም ተባብረው ይኖራሉ።

የሰው ልጅ ግን እንደ ደማዊ ፍጥረታት በሕገ ተፈጥሮ ሳይሆን በሕገ አእምሮ የሚመራ ነፃ ፈቃድ ያለው ልዕለ ፍጡራን ነው። የሰው ልጅ ከአንድ ዝርያ (Homo Sapiens) ግንድ የተገኘ ፍጥረት ሆኖ ሳለ እርስ በእርሱ እንዳይናከስ እና እንዳይጠፋፋ የሚከለክለው ተፈጥአዊ ቅመም (DNA code) በተፈጥሮው የለውም፡፡

ከዚህም የተነሳ ይህንን ከመሰለ ማኅበራዊ ምስቅልቅል እንዲጠበቀው ለዘመናት ሰዋዊ እሴቶችን በተረክ (Myth) እና በታሪክ (History) መገንባት አስፈልጎታል። እነኚህም ክፉውን ለመኮነን በጎ የሆነውን ደግሞ ለማመስገን የምንገለገልባቸው በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ሥር ሰድደው የምናገኛቸው በትምህርት፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት እና በባህል ውስጥ የሚገኙ ወግ እና ልማዶች ናቸው።

የሰው ልጅን ሞራል ለመግራት አነኚህ ማኅበራዊ እሴቶች ብቻቸውን በቂ ሆነው ስላልተገኙ የጥንታዊቷ ባቢሎን ንጉሥ ከነበረው ንጉሥ ሐሙራቢ ዘመን (ቅልክ 1792- 1750) ጀምሮ ደግሞ የተለያዩ የሲቪል ሕጎችን መደንገግ አስፈልጓል። እስከዛሬም ድረስ በዓለማችን የሀገሮችን ሕገመንግሥታት ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ሕጎች የሰውን ጠባይ ለመግራት እና ለማስገደድ የወጡ ናቸው፡፡

ከዚህ ሀተታ የምንገነዘበው የሰው ልጅ በትምህርት፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በባህል ወዘተ ባዳበራቸው የሞራል ወግ እና በልማዶች የፈቃድ ሕጎች ብቻ ሳይሆን በሲቪል አስገዳጅ ሕጎች የማይመራ እና የማይገዛ ከሆነ እርስ በእርሱ ለመጫረስ አንድ ጀንበር ብቻ የሚበቃው አደገኛ አውሬ መሆኑን ነው።

ከላይ ባነሳሁት የማኅበረ ሰብእ ሳይንስ እውነት ላይ ተመሥርተን በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለፍንበትንም ሆነ አሁን ያለንበት ማኅበራዊ ምስቅልቅል ምክንያት ስንጠይቅ እንደ አንድ ማኅበረ ሰብእ ያለፍንባቸውን የግማሽ ምእተ ዓመታት የቁልቁለት ጉዞ ብናጤነው ያጎደልነው ነገር ፍንትው ብሎ የሚታየን ይመስለኛል።

በተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ነገዶችም ይሁን እንደ ሀገር በጋራ ለዘመናት የገመድናቸውን ማኅበራዊ እሴቶች እና ውሎች በአብዮት ሰበብ በጣጥሰን ጥለናቸዋል። በነፃ ፈቃድ እንተዳደርባቸው የነበሩትን ልዩ ልዩ የትምህርት፣ የባህል፣ የሃይማኖት ወዘተ ወግ እና ልማዶቻችንን "ኋላ ቀር" የሚል ታርጋ ለጥፈንባቸው ነቃቅለን ጥለናቸዋል።

ፈላስፋው ዶ/ር ዕጓለ ገብረዮሐንስን የመሰሉ የሀገራችን ሊቃውንት አንደተነተኑት እንደ ሀገር ዘመናዊነትን ስንጀምረው ለዘመናት የቆየናቸውን ሀገራዊ አሴቶቻችንን ነቅለን ጥለን የአውሮፓውን ሥርዓተ ትምህርት ተከልን። ይህም ሀገሪቷን ከዐለት መሠረትዋ ነቅሎ አሸዋ ላይ እንደማቆም የሚቆጠር ነበር፡፡

በታሪክ አጥኚዎች ስምምነት መሠረት የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከተጠነሰሰበት ዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ዶ/ር ዐብይ ዘመን ድረስ ብናጠና አምስት ምድብ ሀገራዊ "ልኂቃን" ለየብቻ ሀገራዊ አበርክቶአቸውን ማየት ይቻላል።

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ (Pioneers of Chenge in Ethiopia) በሚለው ድንቅ ጥናታቸው እንደሚገልጡት ኢትዮጵያን ከድንቁርና እና ከኋላ ቀርነት ለማውጣት የዐፄ ምኒልክ ዘመን ሊቃውንት ሀገራዊ ምዴል በማፈላለግ የደከሙ ሲሆን የዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበሩት ደግሞ ዓለም አቀፍ ምዴል ፍለጋ ላይ ደክመው ነበር። (ጃፓን እንዴት ሰለጠነችን ያስታውሷል)

በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ዘመን ጉልበተኞች፣ በህወሓት ኢህአዴግ ዘመን ብሔርተኞች (ዘውጌ ልኂቃን) በመሰላቸው መንገድ "ሀገር ለማቅናት የሞከሩ" ሲሆን አሁን ያለንበት አምስተኛው ምድብ በብልጽግና (ኒዎ ኢህአዴግ) ዘመን ደግሞ የግጭት ጠማቂ (War lords) እና ብልጣ ብልጦች መንበረ ሥልጣኑን በመጨበጣቸው እንደ ማኅበረሰብ የምንፈወስበትን ሀገራዊ መድኃኒት ለማግኘት ሀሰሣው እስካሁን አልተሳካም።

ወደፊትስ ምን ይበጀን ይሆን ???

ዮሐንስ መኮነን

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence