Get Mystery Box with random crypto!

መንጋነትን ተፀየፍ ሲግመን ፍሮይድ፣ አርኪመድስ፣ ኒቼ፣ ቻርለስ ዳርዊን፣ ጋሊሊዮ፣ ሶቅራጥስ፣ ቡድ | የስብዕና ልህቀት

መንጋነትን ተፀየፍ

ሲግመን ፍሮይድ፣ አርኪመድስ፣ ኒቼ፣ ቻርለስ ዳርዊን፣ ጋሊሊዮ፣ ሶቅራጥስ፣ ቡድሃ፣ ቶማስ ኤዲሰን፣ ቫን ጎ፣ የእኛው ሀገር ፈላስፋ ዘርዓያዕቆብ ... ሌሎችም ሌሎችም በየስርቻው በየጉራንጉሩ በእኛም ሀገር ጭምር አሉልህ፡፡ አብዛኞቹ በዘመናቸው የተወገዙ ወይ አድማጭ ያጡ ነበሩ፡፡ ዛሬ እግርህን በጀብደኝነት አንፈራጠህ ቆመህ ሰልፊ (ራስ በራስ ፎቶ) የምትነሳበትን ስልጣኔ የመሰረቱት ግን እኔው ዘመንን የቀደሙ የትናንት መሰሎችህ ነበሩ፡፡ ካምቤል ኢጁጋርጁክ የተሰኘ የካናዳ ካሪቦ ኢስኪሞ ጎሳዎችን መንፈሳዊ መሪ አባባል ይጠቅሳል፡፡ ኢጁጋርጁክ እንዲህ አለ....

"እውነተኛ ጥበብ ከሰው ልጅ ተሰውራ ትገኛለች፡፡ በታላቅ ሕመምና የብቻ አርምሞ ካልሆነ የሚደረስባት አይደለችም፡፡ ፈተናን መጋፈጥና ብቻነት ግን ወደዚህ ድብቅ ዕውቀት መገኛ ስውር ቦታ አዕምሮን ይመራሉ፡፡"

የምንኖረው ግን በጅምላ በሚመለክበት፣ በጅምላ በሚወገዝበት፣ በጅምላ በሚኮነንበት፣ ሽያጩም፣ ዘረፋውም፣ ግድያውም፣ ቀብሩም ጅምላ ሆኖ ተነጥሎ መቆም ወንጀል በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው፡፡

እናስ በዚህ ሂደት ከመንጋው የመነጠል፣ ከዘመን የመጣላት፣ ከትውልድ የመኳረፍ አዝማሚያ የሌለው ጠቢብ የመንጋውን መፈክር በውብ ቃላት ሸላልሞ ከማተም በስተቀር ረብ ያለው ሀቲት ሊወጣው ይችላልን? ምንኖረውን የሆነውን ለመጻፍ፣ ለመዝፈን፣ ለማቅለም፣ ለማሰማመር ብዙ መጣር አርቲስት መሆን ያስፈልጋል እንዴ? በየትኛውም ዘመን ተወለድ (በእኛም ዘመን ይሁን) ብዙዎች ከሚስማሙበት ከተለየህ፣ ብዙዎች የሚያደንቁት ካልመሰጠህ፣ ብዙዎች በጅምላ የሚጠሉትን ካልጠላህ ውግዘት ውርደት፣ ግዞት ይደርስብሃል፡፡ ምክንያቱም አንተ የሚቀጥለው ትውልድ አባል ነህ፡፡

የእኛን ነገር እንኳን ተውት፣ ተውት አዲስ አተያይ ማመንጨቱን፣ የሚቀጥለውን ትውልድ ትልም የማርቀቅ ቅብጠቱን ተውት... ተውት፡፡ እኛ ከዘመንና ከትውልድ መኳረፍ ያቃተን፣ ዘልማዳዊ የነተበ ሕይወት የማይሰለቸን፣ አንሰን አንሰን የምናሳንስ፣ በአጥንት እንደሚጣሉ የተራቡ ውሾች እርስ በእርስ የምንናከስ ሕዝቦች ነን፡፡

ለብቻ መቆም መቻል ግን ውበት ነው፡፡ ፅናት ነው፡፡ ጥንካሬ ነው፡፡ ለብቻ መቆም(solitude) መሟላት እንጂ መነጠል (isolate) አይደለም፡፡ መነጠል ብሎ ነገር የለም፡፡ የምትነጠለው ጉልህ ስብዕና አጥተህ ተጀምለህ የተቆጠርክ ዕለት ነው፡፡ እንደ ጉሬዛ ከዛፍ ዛፍ እየዘለልክ ብትኖር እንኳን ከሰው እንጂ ከምልዓተ ዓለሙ መነጠል አትችልም፡፡ ማንም ሁን ከየትም ና አንተ የምልዓተ ዓለሙ የልብ ትርታ ነህ። አንተ አንተን መሆን ከቻልክ ያለ አንተ ዓለሙ ይጎድላል፡፡

ተደርቦ ተጀምሎ መቆጠርን ተፀየፍ፡፡ በስብዕናህ ራስህን ችለህ ስትር ብለህ መቆምን ቻልበት፡፡ ሰዎችን በሙሉ ልብህ ተቀበል፡፡ ለመሸኘትም ግን ምንጊዜም ዝግጁ ሁን፡፡ በጊዜ ውስጥ አስቀድሞ ያልሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ መወለድህም፣ መሸለም መጋዝም በጊዜ ውስጥ ቀድሞውኑ የታሰበ ነው፡፡ ይኼንን ማሰብ መቀበል ስለማትፈልግ ዘወትር ለእያንዳንዷ የሕይወት እርምጃ እንግዳ ትሆናለህ፡፡ ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡

ይኼንን የምነግርህ እኔ እንኳን ዘወትር እንደ ተማሪ ነኝ፡፡ ከሰው ልትደበቅ ትችላለህ፡፡ ማንም ግን ከራሱ መደበቅ አይችልም፡፡ በራስህ ምላስ መቅመስ ካልቻልክ አንተ ጣዕምን አታውቃትም፡፡ ብቻህን መቆም ከቻልክ አንተ ነፃ ወጥተሃል፣ ክንፎችህን ሰርተሃል፡፡ ነፃ በወጣህ ጊዜ ሕይወትን በምልዓት ትኖራታለህ፡፡ ሁልጊዜ ከራሳቸው መታረቅ ተስኗቸው ቀላሉን መንገድ በመሻት እንደሚማስኑ ደካሞች አትሆንም፡፡

ግለሰቦች ሲሳሳቱ ስህተቱ ከራሳቸው ወይም በጣም ከጥቂቶች የተሻገረ ጥፋትን አያስከትልም፡፡ መንጋው ከተሳሳተ ግን አያድርስ ነው፡፡ የመንጋው፣ የጅምላው ስህተት የሚያደርሰውን የጥፋት መጠን ለማወቅ ሩዋንዳን መጥቀሱ ብቻ ይበቃል፡፡ መንጋው እንዲያውም ልክ ሆኖ አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡ አንተ የዚህ የጅምላ ስህተት አካል መሆንን ተጸየፍ፡፡


አስቀድሜ እንዳወጋሁህ ዛሬ ዘመናዊው ዓለም የደረሰበትን የኑረት ቅኝት የቀረጹት ሺኅ እንኳን የማይሞሉ በራሳቸው መሻት ወይም በመንጋው ግፊት ተገልለው ማሰብ የቻሉ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሌላው ግብስብሱ ለድምቀት ለጭብጫባ ብቻ የሚፈለግ የቤተሙከራ አይጥ ሆኖ አልፏል፡፡ ያልፍማል፡፡ አንተም በፊናህ ጥቂት ስንኝ ቋጥረህ በብዙ የምታቧትር፣ በርካታ የግል አድናቂዎችን ቤት ለቤት እየዞርክ ለመፍጠር የምትማስን ሆነህ ባየሁ ጊዜ ግን አዘንኩልህ፡፡ አንተ ግን ከሰው ይልቅ ሰዎች በልጠውብህ ተቧድነህ ባሩድ ስታሸት ስትወራወር ባየሁህ ጊዜ አነባሁ፡፡

አንተ እኮ አንተ ነህ፡፡ በሰዎች መካከል ስትሆን ደቃቅ አሸዋ ላይ እንደወደቀች አንዲት የጤፍ ዘር ታንሣለህ፡፡ ምርጫህ በሌሎች ምርጫ ይወሰናል፡፡ ድምጽህ በሌሎች ጩኸት ይሸፈናል፡፡ ቁጣህ በሌሎች ግድየለሾች ፌዝ ይከለላል፡፡ ሕማም፣ ሕመምህ በሌሎች ለዛየለሾች ሁካታ ይጨፈለቃል...

ግለሰባዊነት ይለምልም!

ምንጭ-ከባዶ ላይ መዝገን
ደራሲ- ያዕቆብ ብርሀኑ

@Zephilosophy
@Zephilosophy