Get Mystery Box with random crypto!

የህይወት ልጓም (Samuel Geda) አንድ የሥነ-ሕይወት (Biology) መምህር ለተማሪዎቹ፤ | የስብዕና ልህቀት

የህይወት ልጓም

(Samuel Geda)

አንድ የሥነ-ሕይወት (Biology) መምህር ለተማሪዎቹ፤ 'አባጨጓሬ ወደ ቢራቢሮ የሚለወጥበትን ዑደት' እያስተማራቸው ነው። ለጥቆም፤ "በሚቀጥሉት ሰዓታት ከአባጨጓሬ ወደ ቢራቢሮ የተቀየረው አካል፡ ከዕጭ-ሽፋኑ (cocoon) ውስጥ ለመውጣት ትግል የሚያደርግበት ጊዜ ነው፤ ሂደቱን ከመመልከት ውጪ ታዲያ ማንም ቢራቢሮውን ለመርዳት እንዳይሞክር!" ብሎ በማስጠንቀቅ፡ ተማሪዎቹን ጥሎ ከቤተ-ሙከራው ይወጣል።

ተማሪዎቹም የሚሆነውን ለማየት በጉጉት ይጠባበቁ ጀመር፤ ልክ መምህሩ እንዳላቸውም ቢራቢሮው ከእጭ-ሽፋኑ (cocoon) ውስጥ ለመውጣት ይታገል ጀመር። ይሁንና ከተማሪዎቹ አንደኛው ልጅ የቢራቢሮውን ትግል ዐይቶ ያዝንና ከመምህሩ ትእዛዝ በተቃራኒ- ብራቢሮውን ከእጭ-ሽፋኑ ሊያወጣው ይወስናል። 'ትግሉን ባቀልለት' ሲልም የእጭ-ሽፋኑን ይሰብረዋል፤ ይሁንና እንደጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ ከደቂቃዎች በኋላ ቢራቢሮው ይሞታል።

መምህሩም የተማሪዎቹን ሁኔታ ሊያይ ሲመለስ የተፈጠረውን ነገር ይነግሩታል። ይህን ጊዜ መምህሩ የእጭ- ሽፋኑን ለሰበረው ተማሪ፡ ሁኔታውን ያስረዳው ጀመር፤ "ቢራቢሮውን የገደልከው እርሱን ለመርዳት በማሰብህ ነው፤ ምክንያቱም ከእጭ-ሽፋኑ ለመውጣት ትግል ማድረጉ፡ አንተ እንዳሰብከው ቢራቢሮውን የሚጎዳ ሳይሆን ለክንፉ ጥንካሬና እድገት የሚረዳው ነበር። ይህ የተፈጥሮ ህግ ነውና። አንተ ግን ትግሉን በማቋረጥህ ወይንም በመከልከልህ ምክንያት ቢራቢሮው ሊሞት ችሏል።"

* * *
ይህ ህግ በህይወታችንም ይሠራል። ከትግል ውጪ ወደ ህይወታችን የሚመጣ (ምንም ዐይነት) ስኬት የለም። አንዳንዴ ወላጆቻችን ከሃዘኔታ ስሜት ተነስተው የትግል ህይወትን ከኛ በማራቃቸው ጎድተውናል፡ እንዳንጠነክርና እንዳናድግም አድርገውናል። ብዙውን ጊዜ ትግል ምቹ ሜዳን ስለማይፈጥርልን አንወደውም። የምንፈልገው ስኬት ሁሉ ያለ ትግል ሰተት ብሎ እንዲመጣ ነው። ስኬቱን እንፈልጋለን ትግሉን ግን አንፈልገውም።

አንድ ቢራቢሮ ቢራቢሮ ለመሆን-- ከእንቁላል ወደ እጭ (larva)፤ ከእጭ ወደ ሙሽሬ (pupa)፤ ከሙሽሬ ወደ አባጨጓሬ፤ ከአባጨጓሬ ወደ ቢራቢሮ፤ ከቢራቢሮነት መብረር እስከቻለባት ደቂቃና ሰአት ድረስ ያለውን *ትግል* ማለፍ የግድ ብሎታል። ልክ እንዲሁ፤ በህይወት ለማደግ/ለመለወጥ (ምንጊዜም) በትግል ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል። ስኬት መፈለግህ ጤነኛና ብሩህ አእምሮ የመያዝህ ምልክት ነው። ይሁንና ስኬታማ ለመሆን ጥንካሬና እድገት የግድ ይሉሃል፤ እነርሱ የሚገኙት ደግሞ በትግል ውስጥ ነው።

ይኸውልህ፤ የህይወት ትልቁ ልጓም ምንድነው ካልን- ትግል ነው። ነጻነት ያለው ሰው ለመሆን እንጂ ነጻ ለመሆን መፈለግ የለብንም። ፈጣሪም ቅርፅ የሚሰጠን በትግል ውስጥ እያቀለጠ ነው። ምናልባት ልጓም- እርምጃን የሚገታ፣ እረፍት የሚያሳጣ፣ ምቾት የሚነሳ፣ ገደብ የሚጥል፣ ከመንገድ የሚያስቀር፣... ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ፤ ልጓሙ- ከግብ የሚያደርስ፣ የተገራ ማንነትን የሚያላብስ፤ ብቁና ስልጡን የሚያደርግ፣ ወደ ዓላማ-መርና መርኽ-ገዝ ህይወት (Self actualization/realization) የሚያሳድግ፣ ጥንካሬን የሚሰጥ፣ ከሁሉ በላይ፡ ከራስ አልፎ ለሌላው የሚቆረስ ስብእና ባለቤት የሚያደርግ--ነው። ስለዚህ ትግል ማለት የስኬት ተቃራኒ ሳይሆን የስኬት አካል ነውና- ትልቁን የህይወት ልጓም- ትግልን አንጥላው!

መልካም ቀን

ሌሎችንም ያስተምር ዘንድ በቅንነት #ሼር ያድርጉ

Join: @Human_Intelligence
Join: @Human_Intelligence