Get Mystery Box with random crypto!

የሚያሳስበኝ (በእውቀቱ ስዩም) ይሄ ጨዋታ አይደለም፥ በቀደም ከሜክስኮ ወደ ፒያሳ የሚያወጣውን | የስብዕና ልህቀት

የሚያሳስበኝ
(በእውቀቱ ስዩም)

ይሄ ጨዋታ አይደለም፥
በቀደም ከሜክስኮ ወደ ፒያሳ የሚያወጣውን የቸርቺል አቀበት ስወጣ ሁለት ጎረምሶች ከግራ ቀኝ አጀቡኝ፤ አንዱ ናፕኪን እንድገዛው ጠየቀኝ ፤ ቸል ብየው ተራመድሁ፤ ከቀኘ ያለው ጎረምሳ ክንዴን አፈፍ አድርጎ ይዞ “ ብራዘር ርቦኛል የዳቦ መግዣ ስጠኝ “ አለኝ፤ ጣቶቹ ክንዴን ላይ የካቴና ያክል ከበዱኝ፤ ልመና ሳይሆን ልዝብ እገታ ይመስላል፥ በተቻለኝ መጠን ኮስተር ብየ ክንዴን እንዲለቀኝ ወተወትኩት፥ አለቀቀኝም፤ ናፕኪን የሚሸጠው ጉዋደኛውን ‘ ልቀቀው ፤ “ ብሎ ከገሰጸው በሁዋላ “ ግን ርቦን ነው “ የሚል ቃል ጨመረ፤ ድርድር መጀመሩ ነው፥ አስራ አምስት ብር መጽውቸ ተገላገልሁ፤ ወይም ለጊዜው የተገላገልሁ መሰለኝ።
ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ ከፒያሳ ወደ ቀበና ስረማመድ ቱሪስት ሆቴል አካባቢ አንዲት ትንሽየ ልጅ እየሮጠች መጣችና ሱሪየን ይዛ ጎተተችኝ፤ ዝምብየ ተጎተትኩላት፥ ትንሽ ጎን ለጎን እንደተራመድን እግረኛው መንገድ ላይ አንድ የግድግዳ ሰአት የሚመስል ሚዛን የተዘረጋበት ቦታ ደረስን፤ ጩጨዋ ወደ ሚዛኑ ገፋችኝ፤
ሚዛኑ ላይ ወጣሁና “ ስንት ኪሎ ነኝ ?” ብየ ጠየቅሁዋት ፥
ሚዛኑን ቸል ብላ አይን አይኔን እያየች “ አንድ “ አለችኝና ገራም ፈገግታ አሳየችኝ፥
ሚዛኑ በምን መንገድ እንደሚሰራ እምታውቅ አይመስለኝም። ሚዛኑም ሰበብ ነው፤ ያልፎ ሂያጁን አንጀት በልታም ይሁን አስቸግራ ትንሽ ገንዘብ ሰርታ እንድትመለስ ከወላጆቹዋ የተሰጣት ተልኮ ወይም የተጣለ እዳ መሆኑ ገባኝ፥ ለተመዘነኩበት የሚጠበቅብኝ ክፍያ አንድ ብር ቢሆንም ከቦርሳየ አስር ብር አውጥቸ ከፈልኩ፥
“ አመስግኚው’ የሚል ድምጽ ሰማሁ፤ ዞር አልሁ አንዲት ሌላ መንገደኛ ልትመዘን ከሁዋላየ ወረፋ ይዛለች፥ ብላቴናይቱ ግን የሰጠሁዋትን ብር በትንንሽ እጆቸዋ አጣጥፋ ይዛ ፈገግ ብላ ከመቁለጭለጭ ውጭ የምስጋና ቃል አልወጣትም፤
መንገዴን ስቀጥል “ ግን እኮ አምሳ ብር ልሰጣት እችል ነበር “ ፤ የሚል ጸጸት እንደ አሜኬላ ጠቅ አደረገኝ፥ ብሰጣት ምን ዋጋ አለው፤ ማዶ ተቀምጦ በአይኔ ቁራኛ የሚከታተለን ሊስትሮ ሊቀማት ይችላል የሚል ማመኻኛ ፈጥሬ ራሴን ለማጽናናት ሞከርሁ፤ ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ ራሴን ለማጽናናት ያፈለቅሁት ሀሳብ የበለጠ ድብርት ለቀቀብኝ ፤
ድሮ ፥ በገርነቴ ዘመን ፥ የቅዱሳንን ገድል ሳገላብጥ ለንስሀ ሲሉ ራሳቸውን እየገረፉ የሚያሰቃዩ መነኮሳትን ታሪክ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፤ በሸገር መንገድ ላይ ስረማመድ የሚሰማኝን ሀዘን ራስን እንደ መግረፍ ነው የምቆጥረው፥ አንድ የዘነጠ ካፌ ገብተህ በጣም አሪፍ ቁርስ ከበላህ ጸጋ ነው ፤ ግን በዙርያህ የከበበህን ድህነት እና ችጋር ስታስብ ንጹህና የሚጥም ቁርስ መብላትን ብቻ እንደ ትልቅ በደል እና መተላለፍ ትቆጥረዋለህ፥ ባዲሳባ መንገድ ላይ እየሄድኩ የምጋፈጠው ድብርት፥ ሳላውቀው፥ ይሄን በደል ለማስተረይ በራሴ ላይ የምጭነው ቅጣት ይሆን?
እየለመለመ የነበረው ያገራችን ኢኮኖሚ ይህ ነው የሚባል ፋይዳ በሌለው ጦርነት ምክንያት ደካክሟል፥
የተረፈው ያገራችን ሀብት በጥቂት ባለሀብቶች፥ ባለስልጣኖች እና የሀይማኖት ተቋሞች እጅ ተጠራቅሟል፥ አብዛኛው ህዝብ የሚኖረው የቀን ገደብ በሌለው ህማማት ውስጥ ነው፥ ሀብት የላቸው በሀብታቸው ስራ ይፍጠሩ፤ ባለጸጋ ላደረጓቸው ሰራተኞች ደመወዝ ይጨምሩ፤ ህዝብም መንግስትም ምርት የሚደረጀበትን እና በፍትህ የሚዳረስበትን መንገድ ይተልሙ፤ ሰው ሰራሽ ችግር ሰው ሰራሽ መፍትሄ አያጣም። ምኞቴ ነው፥

@Human_Intelligence