Get Mystery Box with random crypto!

ወንፊት ነፊ አትሁኑ የእግዜር ቃል ሁሉን አቃፊ ነው። አጥርና መገደቢያ በዚያ የሉም። እና ለምን | የስብዕና ልህቀት

ወንፊት ነፊ አትሁኑ

የእግዜር ቃል ሁሉን አቃፊ ነው። አጥርና መገደቢያ በዚያ የሉም። እና ለምን ይሆን የእናንተው በአጥር መከበቡ?

ምንጭ ፦ መጽሀፈ ሚርዳድ
ፀሀፊ፦ ሚካኤል ኔይሚ
ተርጓሚ፦ ግሩም ተበጀ

የእግዜር ቃል ማቅለጫ ነው። የቱንም አክብሮ የቱንም ሳያቀል፣ የፈጠረውን ሁሉ አቅልጦ አንድ ያደርጋል። የመረዳት መንፈስ አለውና፣ እርሱና ፈጠራው አንድ መሆናቸውን ሙሉ ለሙሉ ይረዳል-አንዱን ለይቶ አለመቀበል ሙሉውን አለመቀበል፣ ሙሉውን አለመቀበል ደግሞ ራሱን አለመቀበል መሆኑን ጭምር! ስለዚህም ዓላማና ትርጉሙ ለዘለዓለሙ አንድ ነው።

የሰው ልጅ ቃል ግን ወንፊት ነው። ከፈጠረው ውስጥ ገሚሱን አቅፎ ገሚሱን ይገፋል። ዘለዓለሙን፣ ይሄን ወዳጅ ብሎ እንዳቀረበ ያንን ጠላት ብሎ እንዳራቀ ነው - ነገር ግን ዘወትር የትናንት ወዳጁ የዛሬ ጠላት፣ የዛሬ ጠላቱ የነገ ወዳጅ እየሆነው

እናም፣ የሰው ልጅ ከራሱ ጋር በገጠመው ጨካኝ እና ፍሬ አልባ ጦርነት ሳቢያ ውስጡ በንዴት ፍሟል።

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ፣ የሰው ልጅ፣ እሱና ፈጠራው ሌላም ሳይሆን አንድ መሆናቸውን፣ ጠላትን ማባረር ወዳጅን ማባረር፣ ጠላት ላይ በር መዝጋት ወዳጅ ላይ በር መዝጋት መሆኑን እንዲረዳ የሚያደርገውን ቅዱስ መንፈስ ስላጣ ነው። “ጠላት” እና “ወዳጅ" የሚሰኙት ሁለቱ ቃላትም የእርሱ ቃል፣ የእርሱ "እኔ" ፈጠራዎች ናቸው::

የጠላኸው እና መጥፎ ነው ብለህ የወረወርከውን ያለምንም ጥርጥር ሌላው ወድዶ እና ጥሩ ነው ብሎ ያነሳዋል። እውን አንድ ነገር በአንዴ ሁለት ተፃራሪ ነገሮችን መሆን ይችላልን? እውነታው ግን፣ ይሄኛውንም ያኛውንም አይደለም - ያንተው “እኔ” መጥፎ ሲያደርገው ሌላው “እኔ” ጥሩ እድርጎት እንጂ!

መፍጠር የሚችል፣ የፈጠረውን መልሶ እንዳልተፈጠረ ማድረግ እንደማይሳነው አልነገርኳችሁምን? ጠላታችሁን ራሳችሁ እንደፈጠራችሁት ሁሉ ራሳችሁ ጠላትነቱን ልታጠፉ ወይም ዳግም ወዳጅ አድርጋችሁ ልትፈጥሩትም ትችላላችሁ። ለዚያ ደግሞ የእናንተ “እኔ” ማቅለጫ ሊሆን ግድ ይለዋል። ለዚያ የመረዳት መንፈስ ያስፈልጋችኋል።

ስለዚህም ... እንዲህ እላችኋለሁ - ከጸለያችሁ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም መረዳትን በመሻት ጸልዩ። ባልደረቦቼ ሆይ ... ወንፊት ነፊ አትሁኑ።

የእግዜር ቃል ሕይወት ነውና፤ ሕይወትም ሁሉም አንድ እና የማይከፋፈል ሆኖ የሚሰራበት ማቅለጫ ነች - ሁሉም በፍጽም ሚዛን፣ ሁሉም በደራሲው ቅድስት ሥላሴ ፊት ክብር የተቸረው ሆኖ! ባንተስ ፊት ምን ያህል የገነነ ክብር ይኖረው ይሆን?

መቼም ቢሆን በወንፊት አንገዋላዮች አትሁኑ ወዳጆቼ፤ ያኔ ሁሉን አቅፋችሁ፣ ሁሉን አልፋችሁ በገዘፈ ቁመና ትቆማላችሁ - ሊይዛችሁ የሚችል ወንፊትም አይኖርም።

አዎን ... ፈጽሞ በወንፊት አንገዋላዮች አትሁኑ ወዳጆቼ፡፡ የራሳችሁን ቃል ታውቁ ዘንድ፣ መጀመሪያ ነገር የቃሉን ዕውቀት እሹ። ቃላችሁን ስታውቁ ደግሞ፣ ወንፊታችሁን ለእሳት ትዳርጉታላችሁ። የእናንተ ቃል ገና መሸፈኛውን ያልገለጠ ቢሆን እንጂ የእያንዳንዳችሁ እና የእግዜር ቃል እንደሁ እንድ ነው!

ሚርዳድ መሸፈኛዎቹን ትጥሉ ዘንድ ይሻል...

የእግዜር ቃል፣ መቁጠር ያልጀመረ ጊዜ እና ያልተስፋፋ ቦታ ነው። እውን ከእግዜር ጋር ያልነበራችሁበት ጊዜ ነበረን? እግዜር ውስጥ ያልሆናችሁበት ቦታስ አለ? እና ታዲያ ዘላለምን በሰዓታት እና ወቅቶች የጠፈራችሁት ለምን ይሆን? ለምንስ ይሆን ቦታን በጋት እና ክንድ ለክታችሁ የገደባችሁት?

የእግዜር ቃል የማይወለድ ሕይወት ነው፤ ስለዚህም አይሞትም። እና ለምን ይሆን በልደት እና ሞት መከበባችሁ? በእግዜር ሕይወት ብቻስ አይደል የምትኖሩ? ሞት አልባውስ የሞት ሰበብ መሆን ይችላልን?

የእግዜር ቃል ሁሉን አቃፊ ነው። አጥርና መገደቢያ በዚያ የሉም። እና ለምን ይሆን የእናንተው በአጥርና መገደቢያ መከበቡ?

እኔም እላችኋለሁ፣ ሥጋ እና አጥንታችሁ እንኳ የእናንተ ብቻ ሥጋ እና አጥንት አይደለም። ሥጋ እና አጥንታችሁን እወሰዳችሁበት፣ መልሳችሁም የምትመልሱበት፣ ከዚያው ከምድር እና ሰማይ ገንቦ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው እጆች አብረዋችሁ ጠልቀዋል።

በዓይኖቻችሁ ውስጥ ያለው ብርሃንም የእናንተ ብርሃን ብቻ አይደለም። ፀሐይን አብረዋችሁ የሚጋሩት ሁሉ ጭምር እንጂ። ውስጤ ያለው ብርሃን ቢሆን እንጂ፣ ዓይናችሁ ከእኔ ምን ያይ ነበር? በዓይናችሁ ውስጥ ሆኖ የሚያየኝ የእኔው ብርሃን ነው። በዓይኔ ውስጥ ሆኖ የሚያያችሁ የእናንተው ብርሃን ነው፡፡ እኔ ድቅድቅ ጨለማ ብሆን፣ ዓይናችሁ፣ እኔን ሲያይ፣ ድቅድቅ ጨለማ ያይ!!!

በደረቶቻችሁ ውስጥ ያለው ትንፋሽም የእናንት ብቻ አይደለም። ዓየር የሚተነፍሱና፣ ተንፍሰው የሚያውቁ ሁሉ በደረቶቻችሁ ውስጥ እየተነፈሱ ነው። አሁን ድረስ ሳንባዎቻችሁን የሚሞላው የአዳም ትንፍሽ አይደለምን? አሁን ድረስ ልቦቻችሁ ውስጥ የሚመታው የአዳም ልብስ አይደል?

ሐሳቦቻችሁም የእናንተ ብቻ ሐሳቦች አይደሉም። የጋራ ሐሳብ ባሕር የእኔ ትላቸዋለች፤ እናም ደግሞ ያንን ባሕር ከእናንተ ጋር የሚጋሩ አሳቢ ፍጡራን ሁሉ..

ሕልሞቻችሁም ቢሆኑ የእናንተ ሕልሞች ብቻ አይደሉም። መላው ሁለንተና በሕልሞቻችሁ ውስጥ ያልማል...

ቤቶቻችሁስ ቢሆኑ - የእናንተ ብቻ አይደሉም። የእንግዶቻችሁ ማረፊያ፣ ቤቱን የሚጋሯቸሁ ፍጡራን ሁሉ የዝንቦች፣ የአይጥ የድመቱ ሁሉ ማደሪያ ናቸው።

ስለዚህም፣ አጥሮችን ተጠንቀቁ። ስታጥሩ በማጭበርበር ነው፣ እውነትንም ከአጥሩ ውጪ ታገልሏታላችሁ። አጥሩ ውስጥ ፊታችሁን ለማየት ስትዞሩ ደግሞ፣ ሌላው ስሙ ማጭበርበር ከሆነው ሞት ጋር ፊት ለፊት ግጥም!

መነኩሴዎች ሆይ፣ ሰውን ከእግዜር መለየት አይቻል ነገር! ሰውን፣ ከእግዜር ቃል ከወጡት ከብጤዎቹ የሰው ዘርና ከመላው ፍጡራን መለየትም እንዲሁ...

ቃሉ ውቅያኖስ ነው፤ እናንተ፣ ደመናዎችን! እና .... እውን ውቅያኖስን በውስጡ ባይይዝ ደመና ደመና ይሆን ነበር? ቢሆንም ግን፣ ቅርፅና ማንነቱን በሕዋው ላይ ቀርፆ ለዘለአለም ለማኖር ደፋ ቀና ሲል ሕይወቱን የሚያባከን ደመና ጅል ነው። ከተንኮታኮተ ተስፋ እና ከመሪር ከንቱነት በቀር ከዚህ የጅል ልፋቱስ ምን ያጭድ ይሆን?

ራሱን ካላጣ በቀር ራሱን አያገኝም። እንደ ደመና ሞቶ ካልጠፋ በቀር፣ ብቸኛ እኔነቱ የሆንውን፣ ውስጡ ያለውን ውቅያኖስ ሊያገኝ አይችልም።

ሰው፥ እግዜርን ያረገዘ ደመና ነወ። ከራሱ ባዶ ካልሆነ ራሱን የማያገኝ! አህ .... ባዶ የመሆን ደስታ- አህ፣ ባዶ የመሆን ሐሴት!

በቃሉ ውስጥ ለዘለዓለሙ ካልጠፋህ፣ አንተን ... እንዲያውም አንተነትህን የሆነውን ቃል መቼም አትረዳው! አህ ... የመጥፋት ደስታ፣ አህ ... የመጥፋት ሐሴት!

ደግሜ እላችኋለሁ ... መረዳትን በመሻት ጸልዩ። ቅዱሱ መረዳት ልቦቻችሁን ሲያገኘው፣ “እኔ” ባላችሁ ቁጥር በፈጣሪ ታላቅነት ውስጥ የደስታ ምላሽ የማይደውልላቸው አንዳችም ነገር የለም።

@Zephilosophy
@Zephilosophy