Get Mystery Box with random crypto!

በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ እና እጅግ በጣም ሩህሩህ በሆነው ከጊዜያዊ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉ | BOON TECH

በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ እና እጅግ በጣም ሩህሩህ በሆነው

ከጊዜያዊ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ከቅርብ አመታት ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ብሄር፣ ማንነት እና ሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲሰነዘሩ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ ሲያወግዝ፣ ለጉዳቱ ተጠቂዎች አቅም በፈቀደ ድጋፍ ሲያደርግ እና ዘላቂ ሰላም የሚያመጡ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል ።

የአንድ ሃገር ዜጋ በሃገሩ በሰላም የመኖር ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሰረታዊ መብት ነው።
ባለፉት ጊዜያት በአማራ፣ ቤኔሻንጉል፣ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች እና በጋምቤላ ክልሎች ብሄር፣ማንነትን እና ሃይማኖትን መሰረት ባደረገ ዘግናኝ፣ አሰቃቂ ጥቃት እና ግድያ የበርካታ ንፁሐን ዜጎች ህይወት ማለፉን ከተለያዩ መረጃዎች ማረጋገጥ ችለናል። በተለይም በቅርቡ በመሰጊድ የተጠለሉ ምእመናንን ሳይቀር የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው የድርጊቱን አጸያፊነት ያሳያል።

ይህን የሃይማታዊውንም ሆነ የዓለማዊ ህግ የጣሰ አጸያፊ የጥቃት እና የግድያ ወንጀልን ጊዜያዊ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በጽኑ ያወግዛል። በቀጣይም፡-

1. የፌዴራል መንግስት፣ የክልል መንግስታት እና የሚመለከታቸው አካላት ይህን አጸያፊ ድርጊት እና በወንጀል የፈጸሙ አካልን በአስቸኳይ ለህዝብ አሳውቀው እና ለፍርድ እንዲያቀርቡ

2. በጥቃት ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀደመ ህይታቸው እንዲመለሱ፣ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ እና በዚህ ጥቃት እና ወላጅ አልባ የሆኑ ህፃናት ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ

3. የወደሙ የግለሰብ፣ የህዝብ ንብረት እና የእምነት ቦታዎችን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እናሳስባለን።

በአጠቃላይ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ማንኛውም በንፁኋን ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች እያወገዘ የሃገሪቱ ህልውና መሰረት የሆኑትን የአብሮነት፣ መከባበርና እና መተዛዘን እሴቶች መመናመንና የስርአት አልበኝነትና ጭካኔ መበራከት ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።

በቀጣይም መሰል ጥቃቶች እና ወንጀሎች እንዲቆሙ እና ዜጎች በሰላም በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ የፊደራል መንግስትም ሆነ የከልል መንግስታት ብሎም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ በመተባበር ሌት ተቀን እንዲሰሩ እያሳሰብን የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም የሚመለከታቸው ወገኖች በዚህ ረገድ የበኩላቸውን ኋላፊነት በመወጣት መሰል ጥቃቶች እንዳይከሰቱ የመፍትሄ መንገዶች ላይ መስራት እንዳለባቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በመጨረሻም ም/ቤታቸን ለሀገራችን ሁለታናዊ ሰላም መረጋገጥ ከሚመለታቸው አካል ጋር ጠንክሮ በመስራት ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።

አላህ ዓለማችን እና ሀገራችን ሰላም ያድርግልን!

ሰኔ 14/2014
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ