2023-04-16 11:08:04
የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት!
“አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።”( 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥20)
ውድ የገርጂ ሙሉ ወንጌል አባላትና አገልጋዮች በሙሉ እንኳን ጌታ በሰላም ጠብቆ ለ2015 ዓመተ ምሕረት የትንሳኤው በአል መታሰቢያ አደረሳችሁ !!
ትንሳዔውን ስናከብር የጌታ ኢየሱስ ሞትና ትንሳዔ ምን እንዳስገኘልን በማሰብ ለጌታችን ክብርን እየሰጠን ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱሳችንን እንደሚነግረን በጌታ ኢየሱስ ሞትና ትንሳዔ ያገኘናቸው ብዙ ትሩፋቶች ስላሉ እነዚህን የሞቱና የትንሳኤውን ትሩፋቶች ከቅዱስ ቃሉ በመረዳትና በመኖር ሊሆን ይገባል።የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ካስገኘልን ቁልፍ ትሩፋቶች መካከል ጥቂቶቹ :-
1ኛ) ኃጢአት: ሞትና ሲኦል በትንሳኤው ጌታ ተሸንፎአል።
ሞት ሆይ መውጊያህ የታል ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የታል ተብሏል ።(1ቆሮ 15:55)
ሀጢአትና ሞት የሸነፉት በትንሳኤው ጌታ ብቻ ስለሆነ በጌታ ስም ያመኑ ብቻ ናቸው አሸናፊ ሆነው የሚመላለሱት ።ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ከመነሳቱ በፊት ሀጢያትና ሞት ብዙዎችን የሰው ልጆች ሲያሸንፉና ሲውጡ ኖረዋል።በጌታ በኢየሱስ ብቻ ተሸንፈዋል።እኛም በወደደን በእሱ አሸናፊዎች ሆነናል።
2ኛ) ትንሳኤ አስገኘልን :- ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ የተነሳ ጌታ በመሆኑ ለእኛም ትንሣኤና ህይወት ሆኖልናል ። ኢየሱስ ክርስቶስ በኀጢአት ለሞትነው ሕይወት በእሱ ለሚያምን ሕያውነት ሰጥቷል። (ዮሐንስ 11:25)
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሳቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠቅም ለማያልፍም ርስት እንደ ምህረቱ ብዛት ዳግም ልደት ሰጠን።(1ጴጥ1:3-11)
ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሳው መንፈስ ከአማኞች ጋር ሕያው ሆኖ ይኖራል በአማኞችም ውስጥ ይሰራል ።(ኤፌ1:19-20)
3ኛ) በሞቱ የኃጢአት መስዋዕትና ማስተሰረያ
ለሰው ዘር በሙሉ ሆኗል ።ኢሳ53:1
ለአንዴና እና ለዘላለም ብቸኛው የኀጢአት መሰዋዕትና ማስተስረያ ሆኗል።ሮሜ 3:25
4ኛ) ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀን።ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን ጥል አስወግዶታል።እርቅንም አምጥቷል።(2ቆሮ 5:19)
ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ ከኃጢአተኛው የሰው ልጅ የሚጠበቀው በኢየሱስ ቤዛነት አምኖ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ብቻ ነው ።
5ኛ) መዋጀት :- የሰው ልጅ በኀጢአት ውድቀት ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቶ ሳለ እግዚአብሔር በክርስቶስ ቤዛነት ትልቅ ዋጋ ከፍሎ እንደገና ሰውን ወደራሱ መለሰው።ይህም የእግዘብሔርን የሰውን ልጅ በኃጢአት ከጠፋበት መልሶ የራሱ ያደረገበት የመዋጀት ሥራ በክርስቶስ ሞት የተገኘ ድል ነው ።(ገላትያ 3:13)
በመጨረሻም ኑሮአችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ ይመጣል የሚለውን የተስፋ ቃል ሁል ጊዜ በማሰብና በመዘጋጀት ሊሆን ይገባል። ጌታ ዳግመኛ ሲመጣ በስሙ ያመኑትን አምነው የፀኑትን ይወስዳቸዋል። (ዮሐ 14:1-2)አማኞች የእርሱን ዳግም ምጽአት በቅድስናና በፍቅር ሆነን እየጠበቅን ከተሰጠን የወንጌል ተልዕኮ አንጻር የምስራቹን በጨለማ ላሉት እያበሰርን ለዓለም ጨውና ብርሃን ሆነን ልንመላለስ ይገባናል።(1ጴጥ 2:9-10)
እንደተናገረው ጌታ በቶሎ ይመጣል !!
አሜን ማራናታ !!!
መልካም የትንሳኤ በአል መታሰቢያ ለእናንተና ለቤተሰቦቻችሁ እንዲሆን ከልብ እንመኛለን ::
ከገርጂ ሙሉ ወንጌል አጥቢያ የመሪዎች ጉባዔ
107 viewsedited 08:08