Get Mystery Box with random crypto!

ፍቅር በዚያ ወራት  ክፍል 2 (ሚካኤል .አ) የክፍላችን በር ጋር እስክደርስ የነበረኝ በራስ | Fikir Eske Mekabir

ፍቅር በዚያ ወራት 

ክፍል 2

(ሚካኤል .አ)

የክፍላችን በር ጋር እስክደርስ የነበረኝ በራስ መተማመን ስሜት እምን ጉድጓድ እንደገባ አላውቅም። ዶክተር ዛኪን ሳየው ልቤ በአፌ ልትወጣ ታገለችኝ። 

እንደ ልማዱ ፅድት ብሎ መጥቷል። (በጣም የሚገርመኝ ነገር ጫማው ላይ እንኳ ብናኝ አቧራ የለምኮ ) ... ለነገሩ ከቤቱ ወጥቶ በኔ ልብ ላይ ተራምዶ ክፍል እየደረሰ በየት በኩል አቧራ ሊነካው ይችላል?

በማስተማሩ በፊት ሁላችንንም በስስት እያየ ሰላምታ ይሰጠናል...ጨዋታ አዋቂ ነው። 

ቢያንስ ፊት ለፊት ከሚቀመጡ አንድ ሁለት ልጆች ጋር ሳይጨዋወት ወደ ማስተማሩ አይገባም። ሲስቅ ከልቡ ነው ... ነጭ ባይሆንም ፈዛዛ ሽሮ መልክ ያላቸው ስድር ጥርሶች አሉት ። ድዱ በእጅ ሳይወቀር ተፈጥሮ አሽሞንሙና ሰርታዋለች ። 

እሱ ይስቃል.. .ልቤ ታለቅሳለች ። ስድር ጥርሶቹ የኔን ነፍስ የሚያጠፋባቸው ድርድር ጥይቶች መሆናቸውን ማን በነገረው ?

ፈገግታው ደስም ይለኛል.. .ያስቀናኛልም። 

በተለይ ለነጃት ሲስቅላት እነዳለሁ ።

ደግነቱ እንደዚህ አይነት አክራሪ ክርስትያን ሙስሊሟን ነጃት ሊወድ ስለማይችል ለራሴ ቅናት መፅናኛ አላጣም።

ይሁንና ግን ይሄን አስቤ እንኳ ልቤ እርፍ አትልልኝም...ያቺ ጣውንቴ አይኖቿ ያምራሉ ...ሰውነቷ ከኔ ይበልጥ የሚስቡ ይመስለኛል...ብዙ ጊዜ ዛኪ አቀርቅሮ ትምህርት ሲተነትን እነዛ ሎጋ የእግር ጣቶቿን እያየ ስለሚመስለኝ እበሽቃለሁ ።

የሆነ ቀን ላይ የፊት ኒቃቧ ሲወርድ መልኳን አየሁት ...ለክፋቱ ደግሞ ዶክተር ፊትለፊታችን ነው። መልኳን ሲያይ መደንገጡን አይቼበታለሁ ...(ድንገትም ስለማፈቅረው መስሎኝም ሊሆን ይችላል )

ከሁሉም ተማሪ በላይ ዘልዬ ፊቷን የሸፈንኩላት እኔ ነኝ። ሙስሊም ጓደኞቿ አላህ ይባርክሽ ብለው መረቁኝ... (ይሄን ያደረኩት ከነጃት የውበት ፆር ዛኪዬን ለመደበቅ መሆኑን የሚያውቀው አላህ ሲባርከኝ እኮ ታየኝ !)

በቃ ከዛን ቀን በኋላ አይኖቼ ሁለቱንም ይከታተላቸዋል። ለሴት ልጅ ውበት ግድ አልባው ዛኪ ለነጃት ግን የተመየ ስሜት ያሳደረ ይመስለኛል....። ክፍል ውስጥ ፊትለፊት ስለምትቀመጥ ሳያሳስቃት ምንም ነገር አይጀምርም። 

ደግሞ ሌላ የሚያበሽቀኝ ነገር የሷ ሳቅ ነው። ስታየው ገና አይኖቿ ይበራሉ.. .ትንሽ ያወራት ጊዜማ ነፍስያዋ ትዘላለች) 

በዚህ ቅናት ተነሳስቼ እኔም እንደሌሎች ቸካይ ተማሪዎች ፊትለፊት ሄጄ ተቀመጥኩ ።

ብዙ አልምጥ ጓደኞቼ ተሳለቁብኝ። ትምህርት እንደሚደብረኝ ብቻ ሳይሆን እኔም ትምህርትን እንደምደብረው ሁሉም በዙሪያዬ ያሉ ልጆች ያውቃሉ። የኔ ፊት ወንበር ሄዶ መቀመጥ ተማሪውን ብቻ ሳይሆን መምህሬንም ገርሞታል ።

"ዛሬ እንዴት ነው? ... የመማር ሞራልሽ መጥቷል ማለት ነው" ፈገግ አለልኝ ።

ሞትኩለት !

ክለብ ለክለብ የሚቅለበለበው ምላሴ ጉሮሮዬ ላይ ገብቶ ተሰነቀረ ።

የሆነ ቅጥ የሌለው መልስ መለስኩኝ.. .

"አ....አ......መ...ሰ....ለ....እ....ኝ "

ስደናበር ነጃትና ጓደኞቿ ተያይተው ሳቁብኝ። 

በቃ ጠመድኳት ይህችን ሴት !

"ንፁህ ምን ሆነሻል እጅሽ እየተንቀጠቀጠ ነው እኮ!  አመመሽ እንዴ? "

"አዎ ቲቸር !" 

ይኸው የኔ ትሁት ዛኪ ደገፍ አድርጎ ከክፍል እንድወጣ ዕድል ሰጠኝ ።

አለንጋ ጣቶቹ ወገቤን ሲይዙኝ የእውነት ታመምኩለት ...ሰውነቴን እሱ ላይ ጣልኩት ።

የክፍሉን በር ከፍቶ ወጣን ።

"አይዞሽ ንፁህ.. ."

እንዲህ ሲለኝ የነጃት የቅናት ዛር አናቴ ላይ ተፈናጠጠ ።

በድፍረት ከናፍሩን ስሜ ፍቅሬን ልገልፅለት ደፈርኩ ...

አንድ 

ሁለት

ሶስ.....

     (ይቀጥላል)
@fikireskemekabirtireka