Get Mystery Box with random crypto!

“በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።” 2ኛ ቆሮ 1 | ትምህርተ አበው

“በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።” 2ኛ ቆሮ 13፥11


ክርስትና ከዘር ከብሔር ከጎሳ በላይ ነው ክርስቲያኖች የኔ የምንለት ዘር ብሔር ጎሣ የለንም ርስታችን በዓይን ያልታየች በእጅ ያልተሰራች ሰማያዊት ናት የዚህ ምድር ኑሮአችን ልክ እንደ ኪራይ ቤት ነው ወደ ዘላለማዊ ርስታችን የምንጓዝበት ወረፋ እስከሚደርሰን ብቻ የምንቆይበት ጊዜያዊ ነው።ዘራችን ከክርስቶስ ነገዳችን ከሰማያውያን መላእክት ዘንድ ነው እንደ ሰው በዚህ ምድር ብንኖር በሰማይ እንደ መላእክት የምንሆን ነን::(ማቴ 22፥30)

ክርስቲያን የሰውን ደም በከንቱ አያፈስም የቃየልን ታሪክ ያውቃልና (ዘፍ 4፥12) ክርስቲያን የምስኪን እናትን እንባ በከንቱ እንዲፈስ ምክንያት አይሆንም እናቱን እንዲያከብር መጽሐፍ ይዘዋልና (ዘጸ 20፥12) ክርስቲያን አንተ ከዚህ ወገን ነህ አንተ ከዚህ ነው የመጣከው እያለ በብሔሩ ምክንያት ሰውን የሚያፈናቅል የሰውን ደም በከንቱ የሚያፈስ አይደለም ከሁሉ ጋር በፍቅር እንዲኖር ታዟልና (ሮሜ 12፥18)

ገዳዮች የዘነጉት ትልቁ ጉዳይ እነሱም ሟች መሆናቸውን ነው የምስኪናንን ደም በከንቱ ያፈሰሰ ደሙ ሳይፈስ አይቀርም የእናቶቻችን እንባ እንደ ራሄል ጸባኦትን ያንኳኳ ጊዜ ፍርድ ከሰማያዊው ጌታ ይመጣል ያኔ የምስኪናኑ ደም በምድር ያቅበዘብዛል በሰማይ ርስት ያሳጣል የዛሬ ባለ ግዜ አፈናቃዮች ነገ ከመንግሥተ እግዚአብሔር ይፈናቀላሉ የዛሬ ደም አፍሳሾች ነገ ደማቸው ይፈሳል የፍጥረቱ ደም በከንቱ ፈሶ ዝም የማይል አምላክ በተነሳ ጊዜ ለሁሉም እንደየሥራቸው ይከፍላል።


እባካችሁ ለግል ምድራዊ ጥቅማችሁን ስትሉ የምታፋጁን የተማራችሁ መሃይሞች ተውን ተውን ተውን ።እንደ ጥንቱ እንደ አባቶቻችን ልዩነታችንን ተቻችለን አንድነታችንን አጽንተን እንኑር ተውን ተውን ተውን።

እማምላክ ድንግል ማርያም በአስራት ሃገርሽ በምድርሽ በኢትዮጵያ ላይ የእናቶቻችን እንባ በከንቱ ፋሷል እና አንቺ አብሽልን።አዛኝቱ የወገኖቻችንን እልቂት በቃ በይን ከመሐሪው ልጅሽ አማልደሽ ምህረትን አስጭን

ዲ/ን ፍቃዱ ጎንፋ (ዘፍቁረእግዚእ)
ሰኔ 17/2014