Get Mystery Box with random crypto!

የእግር ኳስ ወጎች…. የኤቡዌ ሚሊዮን ፓውንዶች የት ደረሱ? (በምስጋናው ታደሰ) ኢማኑኤል ኤቡዌ | FastMereja.com

የእግር ኳስ ወጎች….
የኤቡዌ ሚሊዮን ፓውንዶች የት ደረሱ?

(በምስጋናው ታደሰ)

ኢማኑኤል ኤቡዌ በአንድ ወቅት የአውሮፓ እግር ኳስ ድምቀቶች ከነበሩ አፍሪካውያን ከዋክብቶች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በአይቮሪኮስት መዲና አቢጃን የተወለደውና ከዝነኛው የአሴክ ሚሞሳስ አካዳሚ ተገኘው ኤቡዌ በተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈ ቢሆንም በተለይም ግን በአርሰናል በነበረው የሰባት ዓመታት ቆይታ በእጅጉ ጎልቶ መውጣት ችሏል፡፡ ከመድፈኞቹ ከተለያየ በኋላ በጋላታሳራይና ሰንደርላንድ ቆይታ አድርጎ በ2016 ጫማውን ሰቅሏል፡፡ ለሀገሩ ብ/ቡድን 79 ጨዋታዎችን አድርጎ 3 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

አሁን 39ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ኢማኑኤል ኤቡዌ በተጨዋችነት ዘመኑ ከሀብትና ንብረቱ ባሻገር ከ20 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ጥሬ ገንዘብ ነበረው፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ያንን ሁሉ አጥቶ ባዶ እጁን ቀርቷል፡፡ በአንድ ወቅትም ጎዳና እስከመውደቅ ደርሶ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ቤልጄማዊቷ የቀድሞ ባለቤቱና የሶስት ልጆቹ እናት አውሬሊዬ በፈጠረችበት ክህደት መሆኑን ነው የሚናገረው፡፡ አይቮሪኮስታዊው በቀለም ትምህርቱ የገፋ ባለመሆኑ በአንድ ወቅት ባለቤቱ የሆነ ፅሁፍ አምጥታ እንዲፈርም ሰጠችው፡፡ ሳያነበው ፈረመ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ሀብቱንና ኢንቨስትመንቶቹን በስሟ እንዳዞረላት የሚያረጋግጥ ሰነድ ነበር ያስፈረመችው፡፡ ከዛ በኋላ ፈታችው፤ ከቤቱም አስወጣችው፡፡ በሰሜን ለንደን የገዛውንና አብረው ይኖሩበት የነበረውን ግዙፍ ቪላ በስሟ ካዞረችው በኋላ ሸጠችው፡፡ ጎዳና ወደቀ፡፡ ራሱን ጣለ፡፡ የመንፈስ መረበሽ አጋጠመው፡፡ በተደጋጋሚ ራሱን ለማጥፋት ሞክሮ ተረፈ፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ ይሄንኑ እንደሚያሳብ ይናገራል፡፡

“እግዚያብሔር ይሄንን መጥፎ መንፈስ እንዲያርቅልኝ እፈልጋለሁ” የሚለው ኤቡዌ “ሀብትና ንብረቴን ተከራክሬ ለማስመለስ ብፈልግም ለጠበቃ የምከፍለው ገንዘብ የለኝም፡፡ ቤቴን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከውስጥ መኖሬን እንዳያውቁ ስለምፈልግ መብራቱን አጠፋ ነበር፡፡ ይሄም ለበለጠ ጭንቀት ዳርጎኛል” ይላል፡፡

ኤቡዌ በአርሰናል ቆይታው በርካታ ሚሊዮን ፓውንዶችን ሰርቷል፡፡ በቱርኩ ጋላታሳራይ ደግሞ ዓመታዊ 1.5 ሚሊዮን ፓውንድ (2.35 ሚሊዮን ዩሮ) ደመወዝ ያገኝ ነበር፡፡ ተጨማሪ የቦነስ ክፍያም ነበረው፡፡ ያ ሁሉ ገንዘብ ግን አሁን እጁ ላይ የለም፡፡ “ዛሬ ላይ ሆኜ ያለፈውን ጊዜ ሳስበው ራሴን በራሴ 'ኢማኑኤል፤ ምን ዓይነት ቂልና የዋህ ነበርክ? እንዴት ስለመጪው ጊዜ አታስብም?' ስል እጠይቃለሁ፡፡ በጋላታሳራይ ሳለሁ ስምንት ሚሊዮን ዩሮ አገኘሁ፤ ሰባት ሚሊዮኑን ለእሷ ላኩላት፡፡ ግን ካደችኝ፡፡ ቲዬሪ ሆንሪ በአርሰናል ቤት አብሮኝ ተጫውቷል፡፡ ዛሬ የቴሌቪዥን ተንታኝ ሆኖ ስመለከተው በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ ግን ደግሞ በራሴ አፍራለሁ፡፡ አብሬያቸው የተጫወትኳቸውንም ሆነ በተቃራኒ የገጠምኳቸውን ተጨዋቾች በቴሌቪዥን ስመለከታቸው 'ይሄን ጊዜ የእኔም ቦታ እዚህ ነበር' እያልኩኝ በእነሱ ብደሰትም በራሴ ግን አፍራለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ራስህን አጥፋ አጥፋ የሚል ስሜት ይፈጠርብኛል” ይላል፡፡

እጅግ በጣም ውድ የሆኑ መኪኖችን ያሽከረክር የነበረው አይቮሪኮስታዊው ኮከብ ዛሬ ለንደን ውስጥ የህዝብ ትራንስፖርት ነው የሚጠቀመው፡፡ የሀገሩ ልጅ የሆነችውና እሱ “እህቴ” ሲል የሚጠራት ያስሚን ራዛክ እዛው ለንደን ውስጥ ኢንፊልድ ተብሎ በሚጠራው መንደር ከመኖሪያ ቤቷ ሰርቪስ ክፍሎች አንዷን ሰጥታው በዛ ጎኑን ያሳርፋል፡፡ ሲያልቅ አያምር ይሏል ይህ ነው…

@FastMereja