Get Mystery Box with random crypto!

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውን ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ተገልብጣ ቢያንስ 38 ሞቱ #FastMereja አብ | FastMereja.com

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውን ስደተኞችን የያዘች ጀልባ ተገልብጣ ቢያንስ 38 ሞቱ
#FastMereja
አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ከየመን የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጣ ቢያንስ 38 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ለነፍስ አድን ሠራተኞች እንደተናገሩት ጀልባዋ 250 የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍራ የነበረ ሲሆን፣ ለመገልበጥ የበቃችውም በካበድ ነፋስ ምክንያት ነው ተብሏል።

መሞታቸው ከታወቀው 38 ሰዎች ውጪ ሌሎች 100 ሰዎች የደረሱበት ያልታወቀ ሲሆን፣ እነሱን ለማግኘት ፍለጋ እየተደረገ ነው።

ከየመን ዋና ከተማ አደን በስተምሥራቅ የምትገኘው የሩደም አካባቢ ባለሥልጣናት እንዳሉት አደጋው በደረሰባት ጀልባ ላይ ተሳፈረው ከነበሩት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሲሆኑ፣ የመንን ወደ ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለመሸጋገሪያነት ይጠቀሙባታል።

የሩደም አካባቢ አስተዳዳሪ የሆኑት ሃዲ አል-ኹርማ ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በጀልባዋ ላይ የመስመጥ አደጋው የደረሰው ወደ ባሕር ዳርቻው ከመቃረቧ በፊት ነው።

በስፍራው የነበሩ ሰዎች 250 የሚሆኑ ስደተኞችን አሳፍራ አደጋው የደረሰባት ጀልባ ላይ የነበሩ በርካታ ሰዎችን ሕይወት ማትረፋቸው ተነግሯል።

“ዓሳ አስጋሪዎች እና ነዋሪዎች አብረዋቸው በጀልባዋ ላይ የነበሩ 100 የሚሆኑት ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን የተናገሩ 78 ሰዎችን በሕይወት አድነዋል” ሲሉ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

ጨምረውም በአደጋው ምክንያት የጠፉትን ሰዎች ለማግኘት የሚደረገው ጥረት የቀጠለ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅትም ስለደረሰው አደጋ እንዲያውቅ መደረጉ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ 97,000 ስደተኞች በጦርነት ውስጥ ወደ ምትገኘው የመን ገብተዋል።

በየመን ያለው ጦርነት እና በቅርቡ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ቢሆንም ስደተኞች ወደ አገሪቱ በአደጋኛ የባሕር ጉዞ መግባታቸውን ቀጥለዋል።

ከጂቡቲ በመነሳት በሕገወጥ መንገድ በቀይ ባሕር በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት በሚጓዙ ስደተኞች ላይ ተመሳሳይ አደጋ በተደጋጋሚ ሲደርስ ቆይቷል።

በዚህ አደገኛ መንገድ የሚጓዙት አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ለሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ከመክፈላቸው በተጨማሪ እንግልት እና በደል እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።

ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ብቻ በተከታታይ በደረሱ ሁለት አደጋዎች 60 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ባሕር ውስጥ ሰምጠው ለሞት መዳረጋቸው መዘገቡ ይታወሳል ሲል ቢቢሲ አማርኛ ነው ያስነበበው።