Get Mystery Box with random crypto!

የኬንያው ፕሬዝዳንት የጫት ዕገዳን በመቃወም ምርቱን እንደሚያስፋፉ ተናገሩ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊ | FastMereja.com

የኬንያው ፕሬዝዳንት የጫት ዕገዳን በመቃወም ምርቱን እንደሚያስፋፉ ተናገሩ

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አንዳንድ የአገሪቱ ግዛቶች በጫት ሽያጭ መጠቀም ላይ ያጣሉትን አወዛጋቢ ዕገዳ ውድቅ በማድረግ ምርቱ እንዲስፋፋ እንደሚያደርጉ አስታወቁ።

ኬንያ ውስጥ ጫት መቃም እየጨመረ ላለው የአእምሮ ጤና ችግር፣ ለወንጀልን መስፋፋት እንዲሁም ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት ነው ተብሎ ይታሰባል።

በኬንያ የባሕር ዳርቻ አካባቢ የሚገኙ ሦስት ግዛቶች ባለፈው ሳምንት ጫት መሸጥ እና መቃምን ካገዱ በኋላ ጫት በሚያምርቱ አካባቢዎች ቁጣን ቀስቅሷል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ግን ጫት ሕጋዊ ምርት መሆኑን ጠቅሰው ሽያጩም መከልከል የለበትም በማለት የግዛቶቹን እርምጃ ተቃውመዋል።

ሙጉካ በመባል የሚታወቀው የጫት ዓይነት ርካሽ እና ጠንካራነቱ የሚነገርለት ሲሆን ሞምባሳ፣ ኪሊፊ፣ ታይታ ታቬታ እና ክዋሌ በተባሉት የባሕር ዳርቻ ግዛቶች ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።

ባለፈው ሳምንት የሞምባሳ ግዛት አስተዳዳሪ አብዱልሰዋማድ ሸሪፍ ናሲር ሙጉኮ የተባለው የጫት ዓይነት በተለይ በወጣቶች ላይ ባለው ጎጂ ውጤት ምክንያት ወደ ግዛታቸው እንዳይገባ፣ እንዳይዘዋወር፣ አዳይሸጥ እና እንዳይቃም ከልክለዋል።

አስተዳዳሪው እንዳሉት ሞምባሳ ውስጥ በሚገኙ የሱስ መገገሚያ ማዕከላት ከሚታከሙት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የጫት ሱሰኞች ናቸው።

በተመሳሳይም የኪሊፊ እና ታይታ ታቬታ ግዛቶች አስተዳዳሪዎችም በጫት ሽያጭ እና አጠቃቀም ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ አሳውቀዋል።

ይህ የግዛቶቹ ውሳኔ ጫቱ በሚመረትበት ኢምቡ ግዛት ያሉ ገበሬዎችን እና ነጋዴዎችን ተቃውሞ ቀስቅሷል። ውሳኔው ተግባራዊ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ሥራቸውን እንዲያቆሙ እንሚያስገድዳቸው ገልጸዋል።

ጫት ከሚመረትበት ግዛት የመጡ የማኅበረሰብ መሪዎች በጫት ላይ የተጣለውን ዕገዳ በተመለከተ ሰኞ ዕለት ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተወያይተዋል።

የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ “ጫት [ሙጉካ] በሕግ የታወቀ ነው፤ ስለዚህም ከአገሪቱ ሕግ ተቃራኒ የሆኑ ውሳኔዎች ተቀባይነት የላቸውም” ብሏል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ እንዳሉት ጫት በአገሪቱ ሕግ እንደ አንድ ምርት የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህ የበጀት ዓመት በአገሪቱ ያለውን የጫት ምርት ለማስፋት መንግሥታቸው 3.7 ሚሊዮን ዶላር እንደሚመድብ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ሁለት የመብት ተከራካሪዎች ግዛቶቹ በጫት ላይ ያጣሉትን ዕገዳ ተቃውመው ፍርድ ቤት ክስ አቅርበዋል።

ሞምባሳ ውስጥ የተጣለው የጫት ዕገዳ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ ባለፈው አርብ ከ10 በላይ የጫት ነጋዴዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል።

ዕገዳው ከበርካታ የሃይማኖት ተቋማት ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፣ በሞምባሳ ያሉ ሙስሊም መሪዎች ጫት ከተከለከሉ ዕጾች መካከል እንደመደብም እየጠየቁ ነው።

ምንም እንኳን የኬንያ ብሔራዊ ፀረ ዕጽ ተቋም በጫት ላይ ዕገዳ ባይጥልም፣ ቅጠሉ በውስጡ በያዛቸው ንጥረ ነገሮች ምክንያት ጎጂ ብሎ ለይቶታል።

ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው