Get Mystery Box with random crypto!

አለቃ ወይስ መሪ? (“አመራር A to Z” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ) መሪ ሁ | እውቀትን ፍለጋ

አለቃ ወይስ መሪ?
(“አመራር A to Z” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)

መሪ ሁሉ አለቃ ነው፣ አለቃ ሁሉ ግን መሪ አይደለም!

መሪ ባለው ቀደም ብሎ የመራመድ ሚና ፈርን የመቅደድ ሃላፊነቱ ስላለው አለቃም ነው ብንል አንሳሳትም፡፡ ሆኖም፣ በተለያዩ የስልጣን ምንጮች አለቃ የሆኑ ሁሉ መሪዎች ናቸው ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ አለቃ፣ አለቃ ነው፤ በማስፈራት ይገዛል እንጂ አይመራም፡፡ መሪ አለቃ ነው ተብሎ ቢጠራም እንኳ በተለምዶ አለቆች የሚያሳዩትን ባህሪ አያንጸባርቅም፡፡ ስለዚህ መሪ የአለቅነቱ ዝንባሌ በጎላ ቁጥር የመሪነቱ መልክና ተጽእኖ እየደበዘዘና እየጠፋ ይሄዳል፡፡

ማንኛውም አለቃ መሪ ለመሆን በተከታዮቹ ወይም በሰራተኞቹ ላይ የአብሮ ሰራተኝነትን ስሜት ሊያሳድር ይገባዋል፡፡ “አለቃ ስለሆንኩኝ ብቻ ሊታዘዙኝና ሊያከብሩኝ ይገባል” ከሚል አመለካከት ወጥቶ በሚያስፈልጋቸው ሁኔታ ሁሉ ለመገኘት ራሱን በማቅረብ፣ ብቃቱን በማዳበርና በምሳሌነት በመምራት ተጽእኖን ማሳደር ይጠበቅበታል፡፡

ስለዚህም ሰዎች፣ መሪን በናፍቆትና በአክብሮት ሲታዘዙት፣ አለቃን ግን በፍርሃት ይታዘዙታል፡፡ የሚከተሉትን ንጽጽሮች እንመልከት፡፡

• አለቃ ሰዎችን በኃይል ይነዳል፤ መሪ ሰዎችን በመልካም ተጽእኖ ያነሳሳል፡፡

• አለቃ በስልጣኑ ላይ ይደገፋል፤ መሪ ባዳበረው ተቀባይነት ላይ ይደገፋል፡፡

• አለቃ ፍርሃትን ይለቅቃል፤ መሪ ፍቅርንና አክብሮትን ያስፋፋል፡፡

• አለቃ “እኔ” ማለት ያበዛል፤ መሪ “እኛ” ይላል፡፡

• አለቃ ስህተተኛው ማን እንደሆነ ያውጣጣል፤ መሪ ስህተቱን ፈልጎ ለማረም ይፈጥናል፡፡

• አለቃ ትኩረቱ ስራው መሰራቱ ላይ ብቻ ነው፤ መሪ ስራውን የሚሰሩት ሰዎች ላይም ትኩረቱን ይጥላል፡፡

• አለቃ ካላከበራችሁኝ ይላል፤ መሪ በሁኔታው መከበርን ያነሳሳል፡፡

በነገራችን ላይ የእውነተኛ መሪነት ጉዞ የሚጀምረው የአንድ ድርጅት የበላይ ከመሆን ሳይሆን አሁን ባለንበት ደረጃ ከሚኖረን ትክክለኛ መርህና ዝንባሌ መሆኑን አንዘንጋ፡፡

ዛሬ በመሪነት ሳይሆን በአለቅነት ዝንባሌ የሚሰሩ የድርጅት አመራሮች ትናንትና በመሪዎቻቸው የአለቅነት ዝንባሌ ሲበሳጩ የነበሩና ከዚያ ሁኔታ ትምህርትን ሳያገኙ ዛሬ ስልጣን ሲይዙ ያንንንው ስህተት የሚደግሙ ናቸው፡፡

አመራር ማለት መልካም ተጽእኖ በማምጣት ሰዎች ራእዩን በመከተላቸው የሚያገኙትን እድገትና ጥቅም በማሳየት ቀዳሚ መሆን ማለት ነው እንጂ ስልጣንን መቆናጠጥ ብቻ አይደለም፡፡

@Ewiketinfilega
@Ewiketinfilega