Get Mystery Box with random crypto!

መረጋጋት መልካም ነው። ለመሮጥ የተገባ ቀን አለ። አዎ! ለመሮጥ፣ ለመትጋት፣ ለመበርታት | እውቀትን ፍለጋ

መረጋጋት መልካም ነው።

ለመሮጥ የተገባ ቀን አለ። አዎ! ለመሮጥ፣ ለመትጋት፣ ለመበርታት የተገባ ቀን አለ። አንዳንድ ቀን ደግሞ ረጋ ለማለት፣ ለማሰብ፣ ለመቀዝቀዝ የተገባ ነው።

ዛሬ በዓል ነው - የእረፍት ቀን። እስኪ ረጋ፣ ሰከን፣ ዝም በልና አስብ።

ስለኑሮህ፣ ስለጤናህ፣ ስለጓደኞችህ፣ ስለቤተሰብህ፣ ስለሥራህ፣ ስለ ሥራ ባልደረቦችህ፣ ስለደንበኞችህ፣ ስለአለቆችህ፣ ስለመምህሮችህ፣ ስለአገርህ፣ ስለመሪዎችህ፣ ስለዜናው፣ ስለዓለም፣ ስለፈጣሪህ አስብ። ስለፖለቲካው፣ ስለሃይማኖት፣ ስለኢኮኖሚው፣ ስለቴክኖሎጂ፣ ስለምታስበው፣ ስለአጀንዳህ፣ ስለአዋዋልህ አስብ። የቱ ትኩረትህን ያዘው?

ሰማዩን ተመልከተው። ፀሓዩዋን እያት፣ ዛፎቹን እያቸው። ነፋሱን አስተውል። በመንገድ የሚጓዙትን የሚተምሙትን መኪኖችና ሰዎች ልብ በል። ወፎቹን አዳምጥ። ሌሎች እንሰሳቶችንም ተመልከት። ምን ይሰማኃል?

ወዳጄ ዓለም እና የሰው ልጅ ተፈጥሮ በብዙ ስንክሳር የተሞሉ ናቸው። ባሳለፍከው ህይወት ብዙ ክስተቶች ታይተዋል። የሚያሳዝንም የሚያስደስቱም ሁኔታዎች የህይወት ገጾች ናቸው። ሁሉ ይመጣል፣ ሁሉም ይሄዳል። ያለፈውና የሚሄደውን በሰላም ሸኘው። አሁን ካለው ጋር በሰላም ተከባብረህና ተሳስበህ ኑር። ታመን፣ እመንም። የሚመጣውን በልከኛ ተስፋ ተቀበለው። ዘልዓለማዊ ክስተት የለም፣ ለውጥ እንጂ። ከሁኔታዎች በላይ መሆንን እወቅበት። መረጋጋት መልካም ነው።

ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ነገሮች ሲለዋወጡ ህይወትን በእርጋታ ማጣጣም የቻሉ ግን ጥቂቶች ናቸው። ህይወትን ለማጣጣም ሀብት የግድ አይደለም፣ ቢኖር ግን ጥሩ ነው፣ ግን በልክ። ህይወትን ለማጣጣም ዘመድና ጓደኛ ቢኖሩ ጥሩ ነው፣ ግን በልክ። ህይወትን ለማጣጣም ጊዜ ማግኘት አስፈላጊ ነው። ጊዜህን መጠበቅና መቆጣጠርን እወቅበት።

ህይወትን ለማጣጣም ጊዜ ማግኘት ብቻውን በቂ አይደለም፣ መልካም ሃሳብም እንጂ። መልካም አስብ!

ዛሬ ለራስህ የጽሞና ጊዜ መድብ። አንድ ሰዓት በቂ ነው። ማንም የማይረብሽህ፣ ሬድዮ የማትሰማበት፣ ቴሌቪዥን የማታይበት፣ ስልክ የምትዘጋበት፣ ብቻህን የምታስብበት። ሃሳብህን የምታበራይበት፣ የምታጠራበት።

በሃሳብህ ራስህን በዘላቂ ደስታ ስለመምራት አስብ። ለራስህና ለሌሎች ስለ መኖር አስብ። የፖለቲካ መሪዎች፣ የሀብት ልዩነት፣ የሃይማኖት ልሂቃን፣ የብሔር ብሔረሰብ ልዩነት፣ የጾታ ልዩነት፣ ዝምድና፣ ጋብቻ፣ ቅጥር ባንተ ላይ ተጽዕኖ እንደማይፈጥሩ አስብ። ከማንም ከምንም ተጽዕኖ የነጻ ተፈጥሮ እንዳለህ አስብ። የሰዎች ወዳጅ መሆንህን አስብ።

ሁሉን ማድረግ እንደምትችል አስብ። ትችላለህ!

አየሩን ሳብ፣ ወድ ውስጥ ሳብ። ሳትጣደፍ ቀስ ብለህ ወደ ውጭ ተንፍስ። አተነፋፈስህን ተቆጣጠር። ውኃ ጠጣ። ሳትቸኩል ጠጣ።

መልካም ቃላትን አስብ። ወዳጅነት፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ተስፋ፣ እድገት፣ እረፍት፣ በጎነት፣ ነጻነትን አስብ። ሁሉ መልካም እንደሆነ አስብ። ስለሁሉ ነገር ፈጣሪህን አመስግን።

ዓለም ላንተ ምቾትና ደስታ የተሠራች ናት። ደስ ይበልህ!

በሩጫ ቀን በትጋት እንድትሮጥ፣ በእረፍት ቀን ጥሩ እረፍ።
ነገን መልካም ለማድረግ፣ ነገ ጥሩ ለመሥራት፣ ዛሬን እረፍ።

መረጋጋት መልካም ነው። እረፍት ከሃሳብ መረጋጋት ይጀምራል። ሃሳብህን አረጋጋ! እረፍ። እርፍ በል!

ዛሬ ያንተ ቀን ነው።



@Ewiketinfilega
@Ewiketinfilega