Get Mystery Box with random crypto!

#ጊጎ (GIGO) የሚለውን ምህፃረ-ቃል የሚጠቀሙት የኮምፒውተር ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ጊጎ ሲተነተን | PAPIO BELETE 💚💛❤️

#ጊጎ (GIGO) የሚለውን ምህፃረ-ቃል የሚጠቀሙት የኮምፒውተር ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ጊጎ ሲተነተን (garbaga in garbage out) በአማርኛ “ቆሻሻ ከገባ ቆሻሻ ይወጣል” ማለት ነው፡፡ የኮምፒውተር ባለሙያዎች ይህን ቃል የሚጠቀሙት ስለኮምፒውተር አለመሳሳት ሲያስረዱን ነው፡፡ “ኮምፒውተር አይሳሳትም ከተሳሳተም እኛ ተጠቃሚዎቹ የተሳሳተ ትእዛዝ በመስጠታችን የተነሳ ነው ሊሳሳት የቻለው” እንደ ለማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ የሰራው ኮምፒውተር ካልተሳሳተ የሰው ልጅ ስለምን ሊሳሳት ቻለ ? የሚለውን ጥያቄ እንደ አንድ ትልቅ አጀንዳ የራሳችንን መላምት ልንሰጥበት እንችላለን። ታላቁ የስነልቦና ሊቅ #ሲግመንድ_ፍሩድ “child is the father of man” ( ልጁ የሰውየው አባት ነው) ማለት ነው ሲል አባባ ተስፋዬ ደግሞ “የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች” እንደሚሉት መሆኑ ነው፡፡ “የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች” ሲባል ቁም ነገሩ የአበባው መልክ ሳይሆን ፍሬው ላይ ነው፡፡ ፍሬው ለነገም ዘር ዛሬም የልፋት ውጤት ነው።

የገባ ነው የሚወጣው፤ የተተከለ ነው የሚፀድቀው፤ የተንከባከቡት ነው የሚያፈራው፤ የተዘራ ነው የሚበቀለው፡፡ ስለዚህ አዘራራችን በልኩ እና ቀና ቀናውን መልካሙን ዘር መሆን አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዘራችን ከመከነ፤ እንክርዳድ ከበቀለበት፤ ከጠወለገ ተጠያቂው ፍሬው ሳይሆን አዝመራውን ያዘመረ፤ ፍሬውን ኮትኩቶ ያበቀለው ነው፡፡ እኛ የልጆቻችን ገበሬዎች ነን እነሱ ደግሞ ፍሬዎቻችን፡፡ ምርቱን የፈለገ ሰው ሌት ተቀን ሳያርፍ አረሙን ያርማል፤ ውሀ ያጠጣል፤ አዝመራውን ያዘምራል፤ ጎተራውን ይጠብቃል፡፡

ድሮ ልጆች ሲያጠፉ፤ ስርአት ሲጎድላቸው “እናንተ አሳዳጊ የበደላችሁ!” ይባላል፡፡ ዘንድሮስ ምንድነው የሚባለው? ፌስቡክ የበደላችሁ፤ ዲሽ ያንጋደዳችሁ፤ ሆሊውድ ያጣመማችሁ ነው የሚባለው፡፡ ድሮ ጥሩ ቤተሰብ ባይኖር እንኳ መልካም መካሪ ጎረቤት አይጠፋም፡፡ ጉርብትናው በኑሮ ሩጫ ስለጠፋ ልጆቻችን ቴሌቪዥንና ሞባይላቸው እያንጋደደ ያሳድግልን ጀመር፡፡
ዛሬ በብልሹ ምግባር እራስ ወዳድ የሆኑት ልጆቻችን ትናንት ለእነሱ የትኛውንም መስዋእትነት ከፍለን ስላላስተማርናቸው፣ ስላላሳደግናቸው ነው፡፡ ዛሬ ማንንም አንውቀስ፡፡ ምክንያቱም ጥፋቱ የኛው ነው፤ ጊጎ ነው፡፡

ኮንትራት ተፈራርመው የተጋቡት ልጆቻችን እንደ አባቶቻቸው በየሰፈሩ ቅምጥ ላለማስቀመጥ ሊሆን ይችላል፡፡ እስኪብርቶ በመጨበቻቸው ሰአት ጠርሙስ መጨበጥ የተማሩት እኮ ትናንት በጆግ ጠላ አምጡ ብለን ስንልካቸው ነው፡፡ ጫት የለመዱት ያኔ እኛ እየቃምን ልጆቻችን ቡና ሲያፈሉልን በማጨሻው ላይ እጣኑን ሲያደርጉልን ነው፡፡ እውቀት በደንብ ያልጨበጡ ተማሪዎች ጥፋቱ ከእነሱ ወይስ ካስተማሪው ?
ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው ይባላል፡፡ ሚዲያዎቻችን የተዘራው እንደሚበቅል ረስተውታል፡፡ የሬዲዮ ፕሮግራሞቻችን ጠባም መሸም ኳስ ኳስ ብቻ ነው፡፡ ለምን ? ሲባሉ “ሰው ኳስ ይወዳል” ነው መልሱ፡፡ ሰው የሚሰማውን ነው የሚወደውም የሚፈልገውም፡፡ የኳስ ዘር እየዘራን እንዴት የስነጽሑፍ፣ የባህል፣ የ ታሪክ የሀገር እውቀት ያለው ትውልድ ከየት ነው የሚያብበው፡፡

በየሚዲያው ላይ “ከሁለት እና ከሦስት በላይ ፍቅረኛ ያላችሁ፤ ከትዳር በፊት ወሲብ መፈፀም ምን ይጠቅማል፤ ጫት ለጥናት ያለው ጥቅም፤ በትዳር ላይ የማገጣችሁ ተሞክሮአችሁን አካፍሉን” እያልን ክብር የማይገባውን፤ እውቅና ሊሰጠው የማይገባውን ጉዳይ እውቅና እየሰጠን፤ እንዴት ብለን ነው እሴት አክባሪ፤ ታሪኩን አዋቂ እና ታሪክ ሰሪ ትውልድ የምንፈጥረው ??
አውቀንም ሆነ ሳናውቅ የምንናገረው፤ የምንፅፈው ጽሑፍ፤ በሚዲያ የምናስተላልፈው የምናደርገው ድርጊት ሰዎች ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ጊዜ፣ ሁኔታ፣ ቦታ፣ ስለፈቀደልን የፈለግነውን ነገር እንደፈለግን መወርወር የለብንም፡፡ መልካሙን እንዝራ መልካሙን መልሰን እናጭዳለን፡፡
.
ቃልኪዳን ሀይሉ
.