Get Mystery Box with random crypto!

የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት 11ኛ ትውልድ የነበሩት #ብጹዕ_አቡነ_ዲዮስቆሮስ (አባ ወልደ ትንሳይ | PAPIO BELETE 💚💛❤️

የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት 11ኛ ትውልድ የነበሩት #ብጹዕ_አቡነ_ዲዮስቆሮስ (አባ ወልደ ትንሳይ ግዛው)
አቡነ ዲዮስቆሮስ በጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት የትውልድ ቦታ #ኢቲሳ ጽላልሽ በመጋቢት 24 1911 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ብጹእነታቸው በተወለዱበት ኢቲሳ ተክለ ሃይማኖት የድቁናን ትምህርት ተከታትለው ከግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ ድቁናን ተቀብለው በመናገሻ ጸዋትወ ዜማን፣ በደብረ ማርቆስ ቅኔን፣ በቆላ እስጢፋኖስና ዲማ ጊዮርጊስ ትርጓሜን ተምረው ወደ ትውልድ ስፍራቸው ተመልሰው መምህር በላይ ከተባሉ ሊቅ ዘንድ በመቀመጥ ትምህርታቸውን እያጠናከሩ ሳለ የፋሺሽት ኢጣልያ ጦር ኢትዮጲያን በመውረሩ ትምህርታቸውን አቋርጠው አርበኞችን በመቀላቀል ለ4 አመታት ከታገሉ በኋላ በጣልያን ጦር ለአንድ አመት በምርኮ ቆዩ፡፡

በዚህ ወቅት ብጹዕነታቸው ኢትዮጵያ ከጣሊያን ነጻ ከወጣች በምንኩስና እግዚአብሔርን ለማገልገል ቃል ገቡ፡፡ በቃላቸው መሰረት ኢትዮጵያ ነጻ እንደወጣች ወደ ደብረ ሊባኖስ በማቅናት ነሐሴ 24 1933 ምንኩስናን፣ መጋቢት 24 1934 ደግሞ ቅስናን ተቀበሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በአዲስ አበባ ለ6 አመታት አገልግለው በ1940 መጋቢት 24 ቁምስናን በመቀበል በአዲስ አበባ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ኡጋዴንና አካባቢው በእልቅናና በመምህርነት አገለገሉ፡፡
ከዚህ በኋላ ብርሃን ሆነው ወዳበሩባት ወሊሶ ሊቀ ካህናት ሆነው መስከረም 1 1945 ተጓዙ፡፡ ቀጥለውም ግንቦት 30 1970 ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ማእረገ ጵጵስናን በመቀበል የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ጨቦና ጉራጌ ሐገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡

በወሊሶ አገልግሎታቸውን በጀመሩባት የቤተሳይዳ ማርያም ቤ/ክ ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሆኑና ከተለያዩ ዓለማት ይመጡ ለነበሩ ህሙማን ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው የፈውስ ጸጋ ይፈውሱ ነበረ። አዕዛብን ሳይቀር በጥምቀት ዳግም እንዲወለዱ ያደረጉ ታላቅ ሐዋሪያም ናቸው።
ብጹዕነታቸው ለወጣቶች ከፍተኛ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ወጣቶች በወቅቱ በነበረው መንግስታዊ የኮሚኒዝም ፍልስፍና ተወስደው እንዳይጠፉ በቤተ ክርስቲያን ፍቅር ተተክለው እንዲቀሩ ይለፉ ነበር፡፡ እንዳሁኑ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጊቢ ጉባኤያት ባለተዘረጉበት በዛ ዘመን እርሳቸው ጋር መጥተው ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡ ከ70 በላይ ድሃ እና ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ሕጻናት በማሳደግ ለቁም ነገር እና ለወግ ለማእረግ አብቅተዋል፡፡

የብጹዕነታቸው ትህትና ከፍተኛ በመሆኑ ለፈውስም ሆነ ለቃለ ወንጌል ወደእርሳቸው የሚመጡ ምእመናን እጃቸውን ይስሙ ነበር "አዳኙ አምላክ ነው የኔን እጅ ለመሳለም አትሩጡ። እኔ አዳኝ ብሆን #አንድ_ዐይኔን_አበራ_ነበር። ይልቁን እናትና ልጁን አመስግኑ። መባውን ከሳጥኑ አኑሩ፥ የሳጥናኤልን ቃል አትስሙ። በማለት እጃቸውን ለመሳም እንዳይጋፉ ይከለክሉ ነበር፡፡
አስገራሚው የብጹዕነታቸው የሕይወት ክፍል ደግሞ የጸሎት ህይወታቸው ነበር፡፡ ሁልጊዜም በፊቷ ቆመው የሚለምኑባት ሥዕለ ማርያም ነበረቻቸው። በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሕሙማን ሳይፈወሱላቸው ሲቀሩ በሥዕሏ ፊት ቆመው "ምነው እመ ብርሃን፥ ተይ አታሳፍሪኝ" ብለው ሲጸልዩ ሕሙማን ይፈዋሱላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ሀይለ ስላሴ ለአገልግሎት ይረዳቸዋል ብለው የሸለሙዋቸውን ላንድ ክሮዘር መኪና ነበራቸው ይህቺን መኪና በማሽከርከር ላይ ሳሉ ተገልብጣ ከሞት በተረፉ ሰዓት ይህች ስዕል ደረታቸው ላይ ተገኝታለች፡፡ ሥዕሏ በአሁኑ ወቅት በሰበታ ቤተ ደናግል ገዳም የመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ስትገኝ በየወሩ በሃያ ሰባት ቤተ ክርስቲያኑ ስለሚከፈት ትታያለች፡፡ ብጹዕነታቸው ብዙ ቋንቋ መናገር ባይችሉም፥ ከተለያዩ ዓለማት የመጣውን ሁሉ - የኳታሩን ፕሬዝዳንት ልጅ ጭምር - በቋንቋቸው ያናግሩ ነበር።

በንጉሱ ዘመን አፄ ኃይለ ሥላሴን ደፈረው ከሚናገሩ ከሚገስጹ አበው አንዱ ናቸው ንጉሱም አባታችንን እንደ አይን ብሌን የሚያዩአቸውና የሚያከብሩዋቸው ነበሩ።
በደርግ ዘመን ወታደሩ ወጣቶች ሊረሸን በተነሳ ግዜ አባታችን መሀል በመግባት መጀመርያ እኔን ገላችሁ ወጣቱን ጨርሱ በማለት ብዙዎችን ከሞት ታድገዋል። የግድያው መሪ ነገ አንተን እዚሁ እደፋሀለው ብሎ በመዛት ይሄዳል አባ ወልደ ትንሳኤል ሙዋቹን አምላክ ያውቃል ብለው ወደ በዓታቸው ያመራሉ በማግስቱ ያ ወታደር እዛው እዛተበት ቦታ መኪናው ተገልብጦ ሞቶዋል። በሰው ሞት ባንደሰትም የአምላክን ፍርድ እናደንቃለን።

እምነትን ከምግባር፣ ክብርን ከትህትና፣ የፈውስ ጸጋን ከትንቢት ስጦታ በአንድ የያዙት የወሊሶው ብርሃን አቡነ ዲዮስቆሮስ (አባ ወልደትንሣይ) በዛሬዋ ቀን ጥር 18 1991 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውናል። ከባንክ ደብተራቸው የተገኘው ስድስት ብር ብቻ ነበር። ስርዓተ ቀብራቸውም የወቅቱ ቅዱስ ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በመሰረቷት ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

#በረከታቸው_ይድረሰን

ምንጭ፡- ዜና ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፥ ዌኪፔዲያ የመረጃ ቋት፥ የመልአከ ሰላም አባ ገ/ሚካኤል፥ ሸገር ኤፍ ኤም ከፕ/ር መስፍን ጋር ካወጉት።