Get Mystery Box with random crypto!

' አድዋና መንግሥት አድዋና ሕዝብ ' _________ #የአድዋ_በዓል_ትዝብቴ! እንደ ሀገር ከአድ | የኤፍሬም እይታዎች (መ/ር)

" አድዋና መንግሥት አድዋና ሕዝብ "
_________
#የአድዋ_በዓል_ትዝብቴ!

እንደ ሀገር ከአድዋ የገዘፈ፤እንደ ዓለምም አስደናቂ የሆነ ከአድዋ የላቀ ብሔራዊ በዓል የለንም።

የአድዋ ድል የዓለም የጭቁን ሕዝቦች ሁሉ ድል ነው።የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የአድዋ ድል የመላው ዓለም ተፈጥሮአዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሠበት፤ በእውነትና በፍትህ ለነጻነትና ለህልውና አጥንት ተከስክሶ ደም ፈሶ ህያው ደማቅ አኩሪ ታሪክ የተጻፈት፤ በአድዋ ታላቅ ህዝቦች በኢትዮጵያ ጀግኖች ታሪክ የተሰራበት ታላቅ ድል ነው።አድዋ የመላው የጥቁር ሕዝብ ድል ነው፡፡

የአድዋ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይወሰን የአፍሪካውያን ሁሉ በዓል፤በዓለም ያሉ የጭቁን ሕዝቦች ሁሉ የነጻነታቸው ፋና ወጊ በዓል ተደርጎ መከበር የሚገባው ነው።አድዋ የዓለም የአሸናፊነት ደማቅ ታሪክ፤ የይቻላል መንፈስ ምንጭ ነው። አድዋ ጥቁሮች ቀና እንዲሉ ያደረገ፤ ባርነትን ያስቀረ የነጻነት ምልክት የጥቁሮች የአሸናፊነት ሰንደቅ ምልክት ነው፡፡
አደዋ መሪ አለው፡፡ የጥቁሮች አባት የጀግንነት ምልክት ቆራጥ ለሀገሩ፣ደፋር ለወታደሩ ታግሎ ያታገለ የዓለም የምንጊዜም ድንቅ መሪ አጼ ምንሊክ፡፡ አድዋ ተራራ ነው ጣልያን የተሸነፈበት ብቻ ሳይሆን የነጮች ዕብሪት የተቀበረበት የጥቁሮች አሸናፊነት የተበሰረበት ልዩ ቦታ፡፡ የአድዋውን ድል ያለ አጼ ምንሊክ ማሰብ አይቻልም፡፡ ድሉን ወዶ የድሉን መሪ መጥላት ባንዳነት ነው፡፡

ብናውቅስ አድዋ ክብራችን
ምንሊክ ደግሞ የድንቅ መሪ ምልክታችን፡፡
የአድዋ ነገር እንዳለመታደል ሆኖ የእኛ ድል ሆነና " በእጅ የያዙት ወርቅ..." ሆኖብን በሀገር ደረጃም አኮሰስነው። ጭራሽ ከአጼ ምንሊክ የሚሸሹ መሪዎችን ማየት ጀመርን፡፡

ለምን ይሆን አድዋን የመሰለ ደማቅ ታሪክ እንኳን አንድ አድርጎን በአንድ ስሜት ማክበር የተሳነን?

በጋራ ታሪካችን በአድዋ እንኳን ከልዩነት ወጥተን አንድ መሆን አልቻልንም። ከአድዋ የተሻለ ለእኛ የጋራ ታሪክ ምን ይሆን? ።
ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያን የመሩ መሪዎች አድዋን የጋራ ብሔራዊ በዓል አድርጎ ለመቀበልና ለማክበር ለምን ከበዳቸው ? መሪዎቻችን "ለእጅ መታጠብ ቀን" የሚሰጡትን ትኩረት ያህል እንኳን ለአድዋ መስጠት አይፈልጉም።በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት የጋራ የሆነ ከመሪ እስከ ተመሪ በጋራ የሚያከብሯቸው የአደባባይ ብሔራዊ በዓላት አሏቸው። በእነዚህ በዓላት ላይ መሪዎች ያለምን ማወላወል ከሕዝቡ ጋር ተገኝተው ያከብራሉ።የደመቀ እንዲሆንም አስቀድመው ይሰራሉ። ነገር ግን ከአድዋ የደመቀ አስደናቂ ታሪክ የተፈጸመበት ሁነት የላቸውም።
አድዋ አሜሪካ ቢሆን? አድዋ እንግሊዝ ቢሆንስ? ...

አድዋ ያልተረሳው በመንግሥት አይደለም በሕዝብ ነው። አድዋ በመንግሥት ተዘንግቷል በሕዝብ ግን ተወስቷል። አድዋን የሚጠሉ መሪዎች አሉን አድዋን የሚወድ ሕዝብ ግን አለን። አድዋ የሕዝብ ነው። መሪዎች ያልፋሉ አድዋ ግን የማያልፍ የማይፋቅ በኢትዮጵያውያን የልብ ጽላት ላይ የተጻፈ አኩሪ ታሪክ ነው።
ሕዝቡ በራሱ አድዋን ያከብራል።ጀግኖቹንም ያወሳል።#የአድዋን_ድል_ባታከብሩም_አድዋን_የሚያከብረውን ሕዝብ ግን አክብሩ! ከእንግዲህ አጀንዳ አትፍጠሩለት። አድዋንም አጼ ምንሊክንም መጥላት ይቻላል፡፡ነገር ግን ታሪኩን ከዓለም የጥቁር ሕዝብ ልብ ላይ መፋቅ አይቻልም፡፡
አድዋ ብዕሩ ደም፣ ወረቀቱ መሬት ሆኖ የተጻፈ ማንም ሊያጠፋው የማይችል ደማቅ የነጻነትና የአሸናፊነት ታሪክ ነው!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች !

የኤፍሬም እይታዎች!
........................... ...