Get Mystery Box with random crypto!

ነነዌና እኛ ! .............. ነነዌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው በስፋት ከተጻፈላቸ | የኤፍሬም እይታዎች (መ/ር)

ነነዌና እኛ !
..............
ነነዌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው በስፋት ከተጻፈላቸው የሜሶፖታምያ ከተሞች አንዷ ናት፡፡

ብዙ የሥነ መለኲት ምሁራን ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ 350 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንደ ነበረች ይስማማሉ፡፡

ምንም እንኳን በ4000 ቅ.ል.ክ. ገደማ በናምሩድ በኩል ብትቆረቆርም 《ዘፍ.10፡11-12》 የአሦራውያን ዋና ከተማ የሆነችው ግን በ1400 ቅ.ል.ክ. ነው 《2ነገ.19፡36》፡፡ በከተማዋ በጣም ታዋቂ የነበረው የጣዖት ቤተ መቅደስ የአስታሮት ቤተ መቅደስ ይባላል፡፡
በዚህች ከተማ የሚኖሩት ሰዎች የሚሠሩት ክፋትና ኃጢአት እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ጽዋው ሞልቶ መጥፊያቸው ስለ ደረሰ ለፍጥረቱ ርኅራኄ ያለው እግዚአብሔር ግን ንስሐ ይገቡ ዘንድ ነብዩ ዮናስን ልኮላቸዋል፡፡

ይህ ነብይ ከአሕዛብ ወደ አሕዛብ የተላከ ነብይ ነው፡፡ አላላኩም አንድ ነብይ ወደ እስራኤላውያን ተልኮ እንደሚያደርገው ለመገሰጽ ሳይሆን ወደ ንስሐ ይጠራቸው ዘንድ ነበር፡፡


ነገር ግን ነብዩ ወደዚያች ከተማ እንዲሄድ በእግዚአብሔር ቢታዘዝም ወደ ተርሴስ ሲኮበልል እንመለከተዋለን፡፡

☞ቅዱስ ጄሮም ነብዩ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲናገር፡-


“ዮናስ አሕዛብን ከመጥላቱ የተነሣ ሳይሆን መዳን ከእስራኤል እየራቀ መሆኑን በትንቢት መነጽር ሲመለከት ወደ ነነዌ አልሄድም አለ፡፡

ይኸውም ሙሴ ይህን ሕዝብ ከምታጠፋው እኔን ከሕይወት መጽሐፍህ ደምስሰኝ ያለው ዓይነት ነበር 《ዘጸ.32፡31-32》፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም “ስለ እነርሱ እርሱ ቢረገም እንደሚመርጥ እንደሰማነው” ብሏል 《ሮሜ.9፡3》፡፡


በእርግጥም በዘመነ ሐዲስ አሕዛብ በክርስቶስ አምነው ሲጠመቁ እስራኤል ግን መጻሕፍትን ብቻ ይዘው ቀርተዋል፤ እስራኤል ነብያትን ብቻ ይዘው ሲቀሩ አሕዛብ ግን የነብያቱን የትንቢት ፍጻሜ ይዘዋል 《ማቴ.12፡42》፡፡
ልብና ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ አምላክ ግን ዮናስ ላለመታዘዝ ብሎ እንዳላደረገው ስላወቀ በልዩ ጥበቡ ሲወስደው እናያለን፡፡


አስቀድሞ ታላቅ ነፋስን በመርከቢቱ ላይ አመጣ፤ ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ቀጥሎም ዓሣው በየብስ እንዲተፋው አደረገ፡፡
ዮናስ ወደዚያች ከተማ ከደረሰ በኋላ ግን ምንም እንኳን የሦስት ቀን መንገድ ዙሮ መስበክ ቢጠበቅበትም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ።

የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ (ጥቁር) ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ። አዋጅም አስነገረ፥ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፥ እንዲህም አለ፡- “ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ።
እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? በማለት፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስም ያዘዘን ይኼንኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሀሳብ መነሻ በማድረግ ነው፡፡


” ሰው ወዳጁ ጌታም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።

በእርግጥም እግዚአብሔርን የሚፈራ ልቡና የትምህርት ጋጋታ አያስፈልገውም፤ የቀናት ብዛት አያስፈልገውም፡፡

እኛ ክርስቲያኖችም ይህን በማዘከር “ንስሐ ብንገባ እንደ ነነዌ ሰዎች ጥቁር ለብሰን ብናለቅስ ከተቃጣው ማንኛውም መቅሰፍት በቤተክርስቲያን ላይ የተደቀነውም ፈተና እርሱ ይታደገናል ” በማለት ነው የሦሥቱ ቀን ሱባኤአችን፡፡ ይህ ጾም በየዓመቱ ከዓብይ ጾም መግቢያ ሁለት ሳምንት አስቀድማ ካለችው ሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ “ጾመ ነነዌ” በማለት እንጾማታለን፡፡ ዘንድሮም ዓብይ ጾም የካቲት 13 ስለሆነ ከሰኞ ጀምረን እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በድርብ መልኩ ጸሎተ ምኅላ ጨምረን ማቅ ለብሰን እንደነነዌ ሕዝቦች ጾመናል ጸልየናል፡፡

ይህ የሱባኤ ቆይታችን እግዚአብሔር የመረጠውን ዓይነት ጾም ሆኖ የእናት አባቶቻችን ልቅሶ ተመልክቶ የሕጻናቱን ልመና ተቀብሎ አምላክ ከተቃጣው ማንኛውም ዓይነት ፈተናም እንድናመልጥ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!

ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን የተሰዉ የሻሸመኔ ሰማዕታት ደም መንበረ ጸባዖት መልስ ያሰጠን፡፡ አሜን

የኤፍሬም እይታዎች
...............