Get Mystery Box with random crypto!

የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የቴሌግራም ቻናል አርማ deaconhenokhaile — የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች
የሰርጥ አድራሻ: @deaconhenokhaile
ምድቦች: ሃይማኖት
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 64.09K
የሰርጥ መግለጫ

ይህ ቻናል በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ፈቃድ ትምህርቶች የሚለቀቁበት ነው::
@deaconhenokhaile
"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን"
2ኛ ቆሮ. 2:14

Ratings & Reviews

2.00

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

0

4 stars

0

3 stars

1

2 stars

0

1 stars

1


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች

2024-05-18 15:43:06 + የሚያምር እግር +

በጸሎተ ሐሙስ ልብን የሚሰውር አንድ ነገር ተፈጽሞ አለፈ፡፡ ይህም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር የማጠቡ ነገር ነው፡፡ የሰውን የቆሸሸ እግር እያሸ የሚያጥብ አምላክ ፣ የተማሪዎቹን እግር የሚያጥብ መምህር ፣ የባሪያዎቹን እግር የሚያጸዳ ጌታ ማየት እንዴት ያስጨንቃል?

እስቲ ለአንድ አፍታ ወደዚያ ቤት በሕሊናችን ተጉዘን እንግባና ጌታን እግር ሲያጥብ አብረን እንመልከተው፡፡
የአምስተኛው ክፍለ ዘመን ባለቅኔ የቅዱስ ኤፍሬም ተማሪ ሶርያዊው ቄርሎና በመንፈስ ሆኖ ያንን ቤት በዓይነ ሕሊናው እንዲህ ቃኝቶት ነበር ፦

‘ጌታ ውኃ ቀዳና መታጠቢያውን ተሸከመ፡፡ የማበሻ ጨርቅ ያዘና ታጠቀ፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ፡፡ ሕሊናዬን አንዳች ነገር ሲወጋው ተሰማኝ ዕንባዬም ፈሰሰ፡፡ በፍርሃት ፊቴን ሸፈንኩ ዓይኖቼንም በመሳቀቅ ዞር አደረግሁ፡፡ ሲያጥባቸው ለማየት አቅም የለኝምና ብወጣ ተመኘሁ’ ይላል፡፡ (Hymns of Cyrillona, On The Washing of the feet, Gorgias Press pg 72)እውነትም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጎንብሶ ማጠብ ለማሰብ ይከብዳል፡፡

ጌታችን ሐሙስ ዕለት ያደረገውን ነገር መጥምቁ ዮሐንስ ቢያይ ኖሮ ምን ይል ይሆን? ጌታ ሊጠመቅ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዮሐንስ ‘አንተ እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ?’ ብሎ አልነበር? መጥምቁ ዮሐንስ ሆይ ና ተመልከት! በአንተ በባሪያው እጅ ሊጠመቅ ሲመጣ ስለ ትሕትናው የተደነቅህበት ጌታ ዛሬ ደግሞ አጥምቁኝ ከማለት አልፎ የባሪያዎቹን እግር ሲያጥብ አጎንብሶ ታየ፡፡ አንተ ‘የጫማውን ጠፍር ተጎንብሼ ልፈታ አይገባኝም’ ያልክለት ጌታ አጎንብሶ የሐዋርያቱን ጫማ ሲፈታና እግራቸውን ሲያጥብ ብታይ ምን ትል ይሆን? በዮርዳኖስ ዳር ‘አንተ እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ?’ ያልከውን ጌታ ቅዱስ ጴጥሮስ ‘አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?’ ሲለው ተመልከት! በእርግጥ በዮርዳኖስ ወንዝ ከታየው ትሕትና የበለጠ ትሕትና በዚያች የመታጠቢያ ውኃ ውስጥ ታየ፡፡ ውኃ በተሞላ በአንድ ማስታጠቢያ ውስጥ የፍጡር እግርና የፈጣሪ እጅ አንድ ላይ ሆነው የታዩበትን ያን ቅጽበት እጅግ ታላቅ ትሕትና ተማርንበት፡፡ ፍጡር ፈጣሪውን ሲያጠምቀው ከማየት በላይ ፈጣሪ የፍጡርን እግር ሲያጥብ ማየት ድንጋይ ልባችንን የሚሰብር ቅጽበት ነው፡፡

ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት የነበሩት ነቢያትስ ይህንን ቢያዩ እንዴት ይደነቁ ይሆን? ኢሳይያስ ሆይ ‘ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ሆኖ አየሁት’ ያልክለት ጌታ ዝቅ ባለ መቀመጫ ላይ ቁጭ ብሎ የአሳ አጥማጆችን እግር ሲያጥብ ተመልከተው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ሆይ ‘እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን’ ብለህ የዘመርክለት ጌታ እግር እያጠበ ነው፡፡ የሚገርመው እግር ከማጠቡ በፊትም ውኃ አስቀረበ አይልም ምክንያቱም ውኃውን የቀዳውም እርሱ ራሱ ነበረ፡፡ አብርሃም ለእንግዶቹ እንዳለው ‘ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ’ ብሎ ውኃ አላስቀዳም፡፡(ዘፍ. 18፡4) ራሱ ውኃውን ቀድቶ በመታጠቢያው ሞልቶ የባሪያዎቹን እግር አጠበ፡፡ ለነገሩ በትሕትና የተጠመቀበትን የዮርዳኖስን ወንዝስ ቢሆን በውኃ የሞላው እርሱ አልነበረምን?

ጴጥሮስ ተጨነቀ ፤ ‘ጌታ ሆይ አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?’ አለና ተከላከለ፡፡ የጴጥሮስ ጭንቀት ብዙ ነገር ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ ‘ኪሩቤል በፊትህ ግርማ እንዳይቃጠል ፈርተው በፊትህ ሲቆሙ በክንፎቻቸው እግራቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ታዲያ እኔ እጠብልኝ ብዬ እንዴት ደፍሬ እግሬን እሠጥሃለሁ? ሱራፌል የልብስህን ጫፍ የማይነኩህ ጌታ የእኔን እግር እንዴት ታጥባለህ? በባሕር ላይ በአንተ ትእዛዝ የተራመድሁት አይበቃኝም? እንዴት እግርህን ልጠብህ ትለኛለህ? ይህንን ዕዳ እንዴ እሸከመዋለሁ?’ የሚል ጽኑ ጭንቀት ያዘለ ጥያቄ ነበር፡፡ ጌታ ግን ዕውር ባበራባቸው እጆቹ እግር አጠበባቸው፡፡ ሸክላ ሠሪው አጎንብሶ የሸክላውን እግር አጠበ፡፡ ሰውን ከምድር አፈር የፈጠረው አምላክ ትቢያውን በክብር አስቀምጦ እግሩን አጠበው፡፡

ጌታችን ያጠበው ከሰዓታት በኋላ እግሬ አውጪኝ ብለው ጥለውት የሚሸሹትን የደቀ መዛሙርቱን እግሮች ነበረ፡፡ ለአንድ ሰዓት እንኳን አብረውት ሊተጉ የማይችሉትን ተማሪዎቹን እግር አጠበ፡፡ ጥለውት እንደሚሔዱ እያወቀ ‘ንጹሐን ናችሁ’ ብሎ አወደሳቸው፡፡ ‘ወደ አብ እንደሚሔድ አውቆ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው’ እንደሚል ምድር ላይ በቀረችው ጊዜ ያልከፈለው የፍቅር ዕዳ እንዲኖርበት አልፈለገምና ጊዜውን ለመውደድ ተጠቀመበት፡፡ የሚወዳቸውን ደቀ መዛሙርት እግራቸውን አጥቦ በፍቅር ተሰናበታቸው፡፡

ጌታ ሆይ የእኔንስ እግር የምታጥበው መቼ ነው? በእውነት በምድር ላይ ከእኔ እግር በላይ የቆሸሸ አለ? ያልረገጥሁት የኃጢአት ጭቃ ፣ ያልነካሁት የበደል ቆሻሻ እንደሌለ አታውቅምን? ‘በክፉዎች ምክር የሔደ’ እግሬን የማታጸዳው ለምንድን ነው? (መዝ. 1፡2) ‘የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም’ ብለህ የለምን? እውነት ነው ፤ እግሬን ከኃጢአት ከከለከልክልኝ ሌላውን አካሌን ማዳንህም አይደል? አጥብቀህ ከምትጠላቸው ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን ‘ወደ ክፉ የሚሮጥ እግሬን’ የማታጥብልኝ ለምንድን ነው? (ምሳ. 6፡18) እባክህን እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፡፡ በእርግጥ የሐዋርያትን የቆሸሸ እግር በውኃ እንዳጠብከው አስበን አደነቅን እንጂ በማግሥቱ ደግሞ የዓለምን ኃጢአት በደምህ አጥበሃል፡፡ ከዳንሁ በኋላ የቆሰልሁትን ፣ ከታጠብኩ በኋላ ያደፍሁትን እኔን በከበረ ሥጋና ደምህ ከኃጢአቴ እድፍ ታጥበኝ ዘንድ ነው ልመናዬ፡፡

በጌታ እጅ የታጠበው የሐዋርያት እግር እንዴት የታደለ ነው? በእሱ ስለታጠበ ዓለምን ዞሮ ወንጌል ለማዳረስ የቻለ እግር ሆነ፡፡ ጌታ ያላጠበው እግር ወንጌል ለዓለም አያደርስም፡፡ ባልታጠበ እግራችን ብንዞር እኛ እንጂ ወንጌል ዓለምን አይዞርም፡፡ ስለዚህ ሐዋርያ ሊሆን የሚሻ ሁሉ ጌታ ሆይ እግሬን እጠብልኝ ብሎ መለመን አለበት፡፡ ወንጌሉም ‘የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ’ ይላልና ክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ሊሆኑ ለሚወዱ ሁሉ እግራቸውን ማጠቡን አሁንም አያቋርጥም፡፡

ጌታ ያጠበው እግር ምን ይሆናል ካልከኝ ‘የሚያምር እግር ይሆናል’ እልሃለሁ፡፡ ሐዋርያት እግራቸው እጅግ ያምር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በእግሩ እብጠት የማይንቀሳቀሰው ቅዱስ ያዕቆብ ሳይቀር እግሩ ያማረ ነበር፡፡ ምክንያቱም ‘መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?’ ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ሮሜ 10፡15

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 24 2016 ዓ.ም.
ኢየሩሳሌም ፤ ፳ኤል
6.3K views: ፦, 12:43
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-05-16 17:05:14 + የሚሮጥ ዲያቆን +

የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ነው:: አቧራማውን የጋዛ ምድረ በዳ በፈጣን ሩጫ እያቦነነ የሚከንፍ አንድ ወጣት ታየ:: ሩጫው የነፍስ አድን ሠራተኞች ዓይነት ፍጥነት ያለው ነበረ:: አንዲትን ነፍስ ሳታመልጠው ለማትረፍ እየከነፈ ነው:: የሚሮጠው ደግሞ በፍጥነት በሚጋልቡ ፈረሶች የሚጎተት የቤተ መንግሥት ሠረገላ ላይ ነው:: በሰው አቅም ፈረስ ላይ ሮጦ መድረስ ባይቻልም ይህ ወጣት ግን ፈረሶቹ የሚያስነሡትን የጋዛን አቧራ በአፉ እየቃመ በአፍንጫው እየታጠነ እንደምንም ደረሰ::
በሠረገላው ውስጥ አንድ ጸጉረ ልውጥ የሩቅ ሀገር ሰው ተቀምጦ በእርጋታ መጽሐፍ እያነበበ ነው::

እግሩን እንደ ክንፍ ያቀለለው ሯጩ ዲያቆን ፊልጶስ ይባል ነበር:: በዚያ ምድረ በዳ ብቻውን ሲሮጥ የሚያጨበጭብለት ሰው የሚሸልመው ደጋፊ አልነበረም:: እንዲያውም ልብ የሚሰብ ኀዘን ላይ ነበረ:: እስጢፋኖስ የሚባል አብሮት ዲቁና የተሾመ የቅርብ ጓደኛውን በድንጋይ ወግረው በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደሉበት ገና አርባ ቀን አልሆነም:: "ቤተክርስቲያን ስደት ላይ ሆና ምን ስብከት ያስፈልጋል?" በሚል ቀቢጸ ተስፋ እጁን አጥፎ ያልተቀመጠው ፊልጶስ ግን የወንድሜን ኀዘን ልወጣ ሳይል የምሥራች ለማብሠር በበረሃ ሮጠ::

ቀርቦ ያናገረው ጃንደረባ ደግሞ "የሚመራኝ ሳይኖር እንዴት ይቻለኛል?" የሚል ኦሪትን ይዞ ትርጓሜ ፍለጋ የሚቃትት ፣ ጥላው ይዞ አካሉን ፍለጋ የሚጨነቅ ትምህርት የተጠማ ኢትዮጵያዊ ነበረ:: ስለዚህ ይህ ዲያቆን መዳን የምትሻውን የጃንደረባውን ነፍስ በመዳን እውቀት አረስርሶ አሁኑኑ ካልተጠመቅሁ አሰኛት:: ብቻውን የሮጠውና አንድ ሰው ያስተማረው ዲያቆን ፊልጶስ ሮጦ ያዳነው አንድ ሰውን ብቻ አልነበረም:: በአፍሪቃ ቀንድ ለምትገኘው ሀገር ኢትዮጵያና ሕዝቦችዋ የመዳን ቀንድ የሆነ ክርስቶስን አሳያቸው:: አንድ ኢትዮጵያዊ አጥምዶ በእርሱ ብዙዎችን ከማጥመድ በላይ ምን ሙያ አለ? ጴጥሮስን በጀልባው ላይ ከዓሣ አጥማጅነት ወደ ሰው አጥማጅነት የቀየረ አምላክ ገንዘብ ያዡን ባኮስ ነፍሳት ያዥ አድርጎ ሸኘው:: "የህንደኬ ሹም ባኮስ ሆይ ከአሁን ወዲህ በህንደኬ ገንዘብ ላይ ብቻ አትሠለጥንም ፤ የእግዚአብሔር ገንዘቦች የነፍሳት ግምጃ ቤት ላይ የሠለጠንህ የመንግሥተ ሰማያት በጅሮንድ አደርግሃለሁ" ብሎ ሾመው::

ይህ ከሆነ ሁለት ሺህ ዓመት አለፈ:: የጃንደረባው የልጅ ልጅ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከሠረገላ አልፎ በፍጥነት በሚሔድ ብዙ ዓይነት መጓጓዣ ሊሳፈር ተሰለፈ:: ትዕግሥት አጥቶ በገንዘብ ላይ ከመሠልጠን ይልቅ ገንዘብ ሠልጥኖበት በፍጥነት ከነፈ:: አንዱ ፊልጶስ ብቻ ሮጦ የማይደርስበት እልፍ ሕዝብ ዛሬ ሠረገላውን አጨናንቆታል:: እንደ ጃንደረባው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን ስልኩ ላይ ያቀረቀረ ፣ ስለ ትንቢት ትርጉም ሳይሆን ስለ ኑሮ ብልሃት የተመራመረ ትውልድ ተነሥቶአል:: የኢሳይያስ ትንቢት ስለማን ቢነግር የማይገደው የሕይወት ውጣ ውረድ ፍቺ የሚሻ ትንቢት የሆነበት ፣ በመንፈስ ጭንቀት የታወከ ምስኪን ትውልድ ተነሥቶአል:: በእርግጥ ይህ ትውልድ ከዚህ ጭንቀት ለመውጣት የሚመራው ሳይኖር እንዴት ይቻለዋል? ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ፊልጶስ ከወዴት ይምጣ?

ኸረ የዲያቆን ያለህ? ነፍስ አድን ፊልጶሳዊ ዲያቆን ሆይ ከወዴት ነህ? ነፍሳትን ለማዳን የሚያሳድድ እንጂ የሥጋ ምኞቱን የሚያሳድድ ዴማሳዊ ዲያቆን አልጠፋም:: እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ የሚወገር ዲያቆን እንጂ ድንጋይ አንሥቶ የሚማታ ዲያቆን አልጠፋም:: ሰረገላ ላይ ሆነው ግራ የተጋቡ ባኮሶች ብዙ ናቸው የፊልጶስ ግን እጥረት አለ:: ችግራቸውን ፈትቶ ጥያቄያቸውን መልሶ የሚሰወር ከሠረገላ አልወርድም ብሎ የማያስቸግር ፊልጶስ ግን እጥረት አለ:: ከእናንተ ቀድመን በተሾምን ዲያቆናት አንገትዋን የደፋች ቤተ ክርስቲያን በእናንተ ቀና እንድትል እንመኛለን:: የሚሮጥ ዲያቆን ያድርጋችሁ:: ምእመናን እሱን ፍለጋ የሚሮጡለት ዲያቆን ሳይሆን ነፍሳትን ፈልጎ የሚሮጥ ዲያቆን ያድርጋችሁ:: ከመቅደሱ ጠፍቶ የሚፈለግ ሳይሆን ፈረስ የማያመልጠው ዲያቆን ያድርጋችሁ::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ዲበ ሠረገላ ሰማይ
ለኢጃት ዲያቆናት ሲመት
ግንቦት 6 2016 ዓ.ም.
13.5K views: ፦, 14:05
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-04-14 12:52:04
13.1K views: ፦, 09:52
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-03-13 20:58:36 ቅትለተ መነኮሳት ከዝቋላ ወደ ደቡብ አፍሪቃ

አባ ተክለ ሃይማኖት (አባ ተክላ) ደቡብ አፍሪቃ ገጠር ውስጥ የሚያገለግሉ መነኩሴ ነበሩ:: ወላጆቻቸው ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምልጃቸውን በመማጸን ተስለው ስለወለዱአቸው ስማቸውን በጻድቁ ስም ሰይመዋቸዋል:: ከባለጸጋ ቤተሰብ የተወለዱትና የሚተዳደሩበት የራሳቸው መርከብ የነበራቸው እኚህ ወጣት የእንጦንስ የመቃርስን መንገድ ተከትለው ሀብታቸውን ሸጠው ለድኆች ሠጥተው የቀረውን ለገዳም አውርሰው መነኮሱ:: ከዓመታት በፊት በገዳማቸው ተገኝቼ በረከት በተቀበልሁበት ወቅት እንዴት እንደመነኮሱ ፣ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ያላቸውን ፍቅርና አንዳንድ ነገሮችን አጫውተውኝ ነበር:: ለእኔም ያሳዩት ስስትና ፍቅር ከሕሊናዬ የማይጠፋ ነው:: ዛሬ በግፍ ሰማዕትነትን እንደተቀበሉ ቢቢሲ ዘግቦ አየሁ:: ሰይጣን የእውነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን አድራሻ መቼም አይሳሳትም::

በግብፃዊው ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም በተሰየመ ገዳም የመነኮሱ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት በሆኑ በሳምንቱ በኢትዮጵያዊው ጻድቅ ተክለ ሃይማኖት ስም የተሰየሙ መነኩሴ ከወንድሞቻቸው ጋር ሰማዕትነት ተቀበሉ:: ሰይጣን ከሃይማኖታችን እንጂ ከዘራችን ጠብ የለውም::

ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ
እስመ በጸሎተ ጻድቅ ትድኅን ሀገር

“በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ" ማቴ. 24:9

https://www.facebook.com/share/U25yhRDtJaBojkjB/?mibextid=WC7FNe
12.8K views: ፦, 17:58
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-23 13:04:15 ምንኩስና የተጀመረው እንዴት ነበር? ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻዎቹ ባሻገር የምንኩስናን ታሪክ ስናጠና በ4ኛው ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ ይታወቃል:: ለሦስት መቶ ዓመታት በአሰቃቂው ዘመነ ሰማዕታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መከራ ስትቀበል ክርስቲያኖችም በየቀኑ ሲገደሉ የነበረበት ዘመን ድንገት አበቃ:: በደማቸው ለመጠመቅና በሞታቸው ክብር ለመቀዳጀት የተዘጋጁ ምእመናንን ድንገት "በቃ ከእንግዲህ አትሞቱም" የሚል አዋጅ ታወጀባቸው::

ዕረፍት አገኘን ብለው የተደሰቱ እንደነበሩ ሁሉ ለሰማዕትነት ቆርጠው ለክብር አክሊል ተዘጋጅተው የነበሩ ብዙዎች ግን ድንገት ሰማዕትነት ሲቆም አዘኑ:: ከሰማዕትነት ክብር ወርደው እንደማንኛውም ሰው መኖር ከበዳቸው:: ስለዚህም በሰይፍ ባይሞቱም በፈቃዳቸው ሞተው ለክርስቶስ ሕያው ሆነው ሊኖሩ ወደ ገዳማዊ ሕይወት ወደ ምንኩስና ጎረፉ:: ይህም ክስተት ለምንኩስናና ለገዳማዊ ሕይወት ምክንያት ሆነ::

ዝቋላን በመሳሰሉ ገዳማት የሚገኙ መነኮሳት በሥጋ የሚሞቱበት ቀን ሳይደርስ በክርስቶስ ፍቅር በፈቃዳቸው የሞቱ ሐዋርያው እንዳለው "ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር የሰቀሉት" ናቸው:: ሰማዕትነትም ቀድመው የተመኙት ክብር ነበር:: በእነርሱ መገደል የሞትነው በእነርሱ ጸሎት ብርሃንነት የምንኖር ፣ ስንጨነቅ ከእግራቸው ሥር የምናለቅስ ፣ በዓለም ማዕበል ስንላተም በመስቀላቸው መልሕቅ ወደ ጸጥታ ወደብ የምንደርስ እኛው ነን::

ባለቆቡ ሰማዕት አባቴ ሆይ እርስዎን የገደሉ የገደሉት የእኔን ተስፋ ነው:: ሰማዕቱ መነኩሴ ሆይ በእርስዎ ሞት የተቀደደው የዕንባዬ መሐረብ ነው:: አንጀታችን በኀዘን እርር የሚለው ለእናንተ ሳይሆን ለራሳችን ነው:: ከእናንተ ጸሎት በቀር ምርኩዝ የሌለን እኛ ይለቀስልን እንጂ ለእናንተ አናለቅስም:: ቀድማችሁ የጠላችኋት ዓለም ብትጠላችሁ አይገርምም:: በፍቅርዋ ለተሸነፍን ለእኛ ግን ዕንባ ያስፈልገናል:: እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን የትኛዋ እንደሆነች ፣ ዘመነ ሰማዕታትን የምትደግመዋ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ማን እንደሆነች በደማችሁ ያሳያችሁ ምስክሮች ሆይ ለእኛ እንጂ ለእናንተ አናለቅስም:: የእኛን እግር ከማጠብ ፣ የእኛን ብሶት ከመስማት ፣ የእኛን የክርስትና ስም ዘወትር በጸሎት ከመጥራት ፣ እኛን ተቀብሎ ከማስተናገድ አረፍ ብላችሁ ከመነኮሳችሁለት አምላክ ዕቅፍ ስለገባችሁ አናዝንም:: የምናዝነው በተራራ ላይ ያለ መብራታችን ለጠፋብን ለእኛ ነው:: የእኛ ደብረ ታቦር ዝቋላ ሥሉስ ቅዱስ በደመና ይጋርድሽ እንጂ ምን እንላለን?

ገዳምንና ገዳማውያንን መንካት የንቡን ቀፎ ማፍረስ ነው:: ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ዐቃቢት ያሉት ሁሉ በገዳም ቀፎነት የተሠሩ የማር እንጀራዎች ናቸው:: ማሩን የሚጋግሩት ንቦች ያሉት ከቀፎው ገዳም ውስጥ ነው:: የአቡየ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የቆብ ልጆች በአስኬማ ላይ የሰማዕትነት አክሊል የደረባችሁ ቅዱሳን መነኮሳት ጸልዩልን በዙፋኑ ፊት ቆማችሁ "ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?" ብላችሁ ስለ እኛ አማልዱ:: (ራእ. 6:10)
14.8K views: ፦, 10:04
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-22 09:48:37 "ይህችን ዓመት ተወኝ!"

ከዓመት እስከ ዓመት - ፍሬን ሳላፈራ - ደረቅ እንደሆንኩኝ
በራድ ወይም ትኩስ - ሁለቱንም ሳልሆን - እንዲያው ለብ እንዳልኩኝ
አለሁኝ በቤትህ - ለሙን መሬትህን - እያጎሳቆልኩኝ
አውቃለሁ አምላኬ - ፍሬዬን ለመልቀም - እንዳመላለስኩህ
ዛሬም ሳላፈራ - እሾህን አብቅዬ - ደርቄ ጠበቅሁህ
ያልተደረገልኝ - ያላፈሰሰክብኝ - ያልሰጠኸኝ የለም
ነገር ግን ይህ ሁሉ - አላርምህ አለኝ - አልለየኝም ከዓለም
የማትሰለቸኝ ሆይ - ተነሥቼ እስክቆም - እባክህ ታገሠኝ
የእኔን ክፋት ተወው - መልአክህን ሰምተህ - ይህችን ዓመት ተወኝ!

አውቃለሁ ታውቃለህ - ቀጠሮን ሰጥቼ - እንደማላከብር
ብዙ ጊዜ አቅጄ - ብዙ ጊዜ ዝቼ - በወሬ እንደምቀር
‹ዘንድሮስ…!› እንዳልኩኝ - አምና ይሄን ጊዜ - ሰምተኸኝ ነበረ
ምንም ሳልለወጥ - ‹ዘንድሮዬ› አልፎ - በአዲስ ተቀየረ
ፍሬ የማይወጣኝ - እኔን በመኮትኮት - እጆችህ ደከሙ
እኔ ግን አለሁኝ - ዛሬም አልበቃኝም - በኃጢአት መታመሙ
የቃልህን ውኃ - በድንጋይ ልጅህ ላይ - ሳትታክት ስታፈስስ -
ዘመን ተቆጠረ
ወደ ልቤ ሳይሰርግ - ሕይወቴን ሳይለውጥ - እንዲያው ፈስሶ ቀረ
ቃልህን ጠግቤ - እያገሳሁት ነው - ሌሎች እስኪሰሙ
በቃልህ መኖር ግን - አልያዝህ አለኝ - ከበደኝ ቀለሙ
ብዙ ጥቅስ አገኘሁ - ከቅዱስ መጽሐፍህ - ገልጬ አይቼ
ከራሴ ላይ ብቻ - አንድ ጥቅስ አጣሁኝ - በበደል ተኝቼ
ውጤቴ ደካማ - ትምህርት የማይሠርጸኝ - ተማሪ ብሆንም
ይህችን ዓመት ተወኝ - ደግሞ ትንሽ ልማር - ታገሠኝ አሁንም!

እባክህ አልቆረጥ - በቅዱስ መሬትህ - ልቆይ ፍቀድልኝ
ያፈሩት ቅዱሳን - የፍሬያቸው ሽታ - መዓዛ እንዲደርሰኝ
የተሸከምከኝ ሆይ - ዛሬም ተሸከመኝ - አትሰልቸኝ አደራ
ማን ይታገሠኛል - ጠላት እየሆንኩት - አይሠሩ ስሠራ!
አታውጣኝ ከቤትህ - ብዙ ቦታ አልይዝም - ፍሬ ስለሌለኝ
ስፍራ የማያሻኝ - ቤት የማላጣብብ - ፍሬ አልባ በለስ ነኝ!
ቦታስ የሚይዙት - ባለ ምግባሮቹ - ቅዱሳንህ ናቸው
ልክ እንደ ዘንባባ - የተንዠረገገ - ተጋድሎ ጽድቃቸው!
ከሊባኖስ ዝግባ - እጅጉን የበዛ - ገድል ትሩፋታቸው!
እኔ አይደለሁም - ቦታስ የምትይዘው - የአንተው እናት ናት
ሥሮቿ በምድር - ጫፎቿ በሰማይ - ሲደርሱ ያየናት
ይሀችን ዓመት ተወኝ - ከሥርዋ እሆናለሁ - ባፈራ ምናልባት!..
ይህችን ዓመት ተወኝ - እባክህ አምላኬ - አንድ ዓመት ምንህ ናት
ሺህ ዓመት አንድ ቀን - አይደለም ወይ ለአንተ - ዓመት ኢምንት ናት!
ይሄ ዓመት አልፎ - ዳግም ‹ዓመት ሥጠኝ› - እስከምልህ ድረስ
እባክህን ጌታ - ይህችን ዓመት ተወኝ - የወጉን እንዳደርስ!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

---
18.1K views: ፦, 06:48
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-19 20:25:53 + ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል +

ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ ተኝቶአል:: ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጠይቀው መጣ:: ሆኖም እንደ ልማዱ እግዚአብሔር ይማርህ አላለውም:: ለጆሮ የሚከብድ ቃል ጥሎበት ወጣ:: "ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል!"

ነቢዩ ይህንን ብሎት ከወጣ በኁላ ሕዝቅያስ ወደ ግድግዳው ዞሮ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ:: አምላኩ በንግግር ብዛት የሚሰማ አምላክ አይደለምና ፊቱን ወደ መቅደሱ አቅጣጫ አዙሮ አለቀሰ::

ከጥቂት ደቂቃ በኁዋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ሌላ መልእክት ይዞ ተመለሰ:: እግዚአብሔር እንዲህ ይላል :- ጸሎትህን ሰምቻለሁ ዕንባህን አይቻለሁ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ" (ኢሳ 38:5)

ሕዝቅያስ ቤትህን አስተካክል ከተባለ በኁዋላ ፊቱን አዙሮ ከማልቀስ በቀር ምንም አላደረገም:: ሕዝቅያስ ሆይ ከአልጋህ ሳትወርድ ያስተካከልከው ቤት ምን ዓይነት ቤት ነው? ለባሪያዎችህ መመሪያ ሳትሠጥ የምታስተካክለው ቤትስ እንዴት ያለ ነው? በደቂቃዎች ውስጥ ትሞታለህ ከተባልክ በኁዋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ያስጨመረልህ ምን ዓይነት ማስተካከያ አድርገህ ነው? ለእኛም ንገረንና ዕድሜ እናስጨምር::

ሕዝቅያስ ከአልጋው ሳይነሣ ያስተካከለው ቤቱ ልቡ ነበር::
ልብህን ካስተካከልህ ቤትህ ይስተካከላል:: እግዚአብሔር እንደሆን ትሞታለህ ቢልህም መሞትህን አይፈልግም:: እርሱ ካንተ ጋር ጸብ የለውም::

"በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?" ይላል መሐሪው (ሕዝ 18:23)

እርሱ ትሞታለህ የሚልህ መኖርህን ፈልጎ ነው:: አንዴ ብያለሁ ብሎ አይጨክንብህም:: በንስሓ ተመለስ እንጂ ምሬሃለሁ ለማለት ይቸኩላል:: አሁን ትሞታለህ ብዬው አሁን ትድናለህ ብለው ይንቀኛል ሳይል ተመልሶ ይምርሃል:: ኃጢአትህንም ወደ ጥልቁ ይጥለዋል:: በጎ እንድትሠራም ዕድሜ ይጨምርልሃል:: አንተ ብቻ ተመለስና አሁኑኑ ንስሓ ግባ::
ከበደል አልጋ ጋር ያጣበቀህን ፈተናም ድል መንሻው ጊዜ አሁን ነው:: ሕዝቅያስ በደቂቃ ዕንባ ምሕረት አግኝቶ ዕድሜ ካስጨመረ በዐቢይ ጾም ሙሉ የሚያለቅስ ምን ያህል ዕድሜ ያገኝ ይሆን?
ወዳጄ አንተም ተነሣና በዚህ ወር ቤትህን አስተካክል::
እንደ ሕዝቅያስ ፈጣሪህ ይጠብቅሃል:: የተቀየምከውን ይቅር በል የበደልከውን ካስ የሚበቀልህን የማይተኛ ጠላትህን ዲያቢሎስ ተበቀለው::

የዐቢይ ጾም የወንጌል ምንባብ ስለ ዲያቢሎስ ፈተና ሦስቱ ወንጌላት የተናገሩትን ስናስተውል ሦስት ዓይነት ጥቅሶች እናገኛለን::

አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። (ሉቃ 4:2)

በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ (ማር 1:13)
የሚሉት ቃላት ጌታችን ዐርባውንም ቀን መፈተኑን ያሳያሉ::

አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ እንዲህ አለው (ማቴ 4:2)

የሚለው ደግሞ ከጾሙ በኁዋላ የቀረቡለትን ሦስት ፈተናዎች የሚያሳይ ነው::
ሦስተኛው ጥቅስ ደግሞ ከተፈተነ በኁዋላ ያለው ሲሆን

ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። (ሉቃ 4:13) ይላል:: ዲያቢሎስ ፈተናውን ቢጨርስም የሚተወው ለጊዜው እንጂ መፈተኑን አያቆምም:: የዲያቢሎስ ፈተና ስልቱ ይቀያየራል እንጂ ይቀጥላል::

ዐቢይ ጾም ዲያቢሎስ ድል የተደረገበት የጦር ዐውድማ ነው:: በዚህ ወራት ድል ያላደረግነውን ፈተና በሌላ ጊዜ አናደርገውም:: ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል እንደሚባለው በዐቢይ ጾም የተኛ ክርስቲያን መቼም አይነቃም:: ከነስሙ ሁዳዴ (ሰፊ እርሻዬ) የምንለው ይህ ጾም ለነፍሳችን ብዙ ዘር የምንዘራበት አጋንንት መድረሻ የሚያጡበት ጾም ነው:: በዐቢይ ጾም ያልተገራ አንደበት መቼም አይገራም:: በዐቢይ ጾም ያልተፈወሰ ቂም መቼም አይፈወስም::

ጌታችን በወንጌል አንዴ ወደ እሳት አንዴ ወደ ውኃ የሚጥል ጋኔን ያለበትን ልጅ ሲፈውስ "ይህ ዓይነቱ ጋኔን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም" ብሎ ነበር:: ሀገራችንን አንዴ ወደ እሳት አንዴ ወደ ውኃ የሚጥላት የጥላቻ ጋኔንም ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም::

ወዳጄ ከቁስልህ የምትፈወስበት ወር እንደደረሰ ዕወቅ:: አንተስ ብትሆን ልትላቀቀው እየፈለግህ ያቃተህ ክፉ ልማድ የለብህም:: እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም የማልፈልገውን ክፉ ነገር ግን አደርጋለሁ:: ምንኛ ጎስቋላ ለዚህ ለሞት ከተሠጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?" ብለህ ምርር እንድትል ያደረገህ ኃጢአት የለም? እንግዲያውስ እወቀው:: ይህ ዓይነቱ ወገን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም:: ይህ ጾም ቁስል የሚሽርበት ጾም ነው:: ይህ ጾም ሸክም ማራገፊያ ጾም ነው:: እንደ ሕዝቅያስ በዚህ ወር ቤትህን በንስሓ አስተካክል::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የካቲት 15 2012 ዓ ም
ዝዋይ ኢትዮጵያ
22.1K views: ፦, 17:25
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-19 11:19:10 ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g
15.6K views: ፦, 08:19
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-19 11:19:10 + ከሁሉ በኋላ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ታየኝ +

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን ስለ ጌታ ትንሣኤ ማስረጃ እያቀረበ ነው:: በዚያን ዘመን ለጌታ ትንሣኤ ማስረጃ ስትጠቅስ በማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ይላል ብለህ እንዳትጠቅስ ገና ወንጌላት አልተጻፉም:: ቢጻፉም ማቴዎስ በሕይወት እያለ በቃሉ መመስከር ሲችል ጽሑፉን ማስረጃ ማድረግ አያስፈልግህም:: ስለዚህ ለመነሣቱ ማስረጃዎች ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች ነበሩ:: በሕይወት ያሉትን የዓይን ምስክሮችን መጥቀስ ይቻላል:: የዓይን እማኞች ምስክርነት ከጽሑፍ በላይ የታሪክ ማስረጃ ነው:: ስለዚህ ጳውሎስ ስለ ጌታ ትንሣኤ "እነ እገሌ አይተውታል" እያለ መዘርዘርን መረጠ::

ጌታ ከተነሣ በኋላ እንደ ቀድሞው ለሁሉ አልታየም:: እርሱን ለማየት የተገባቸው ጥቂት ወደ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ነበሩ:: በማኅበር ያዩት አሉ:: በግል ያዩት አሉ::
ያዩት ነገር ወንጌል የሆነላቸው ብፁዓን ዓይኖች ያሏቸው እንዴት የታደሉ ናቸው? የተሰቀለውን ተነሥቶ ያዩት! ዳግም በሚመጣበት አካል የተገለጠላቸው ምንኛ የታደሉ ናቸው? ከመድኃኔ ዓለም አፍ ተቀብለው ኪዳን ያደረሱ! የጌታን ቅዳሴ ተቀብለው ያስቀደሱ! የትንሣኤው ማግስት ምስክሮች እንዴት ዕድለኞች ናቸው? ቢሞቱም እንኳን መነሣታቸውን በጌታ ትንሣኤ አይተው ደስ ብሎአቸው ያንቀላፉ እነርሱ ምንኛ የታደሉ ናቸው?

ቅዱስ ጳውሎስ በወንጌል ከተጠቀሱት ከነ ኬፋ በተጨማሪ ለይቶ ጌታ ለማን ለማን እንደታየ ገለጸ:: ለያዕቆብ ታየ ብሎ የእልፍዮስን ልጅ ለይቶ ጠቀሰው:: የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት እንደሚሉት ይህ ሐዋርያ ከሌሎች በተለየ የጌታን ትንሣኤ ሳላይ እህል አልቀምስም ብሎ የተሳለና አክፍሎትን የጀመረ ነበርና ጌታ ለይቶ ክብሩን አሳይቶታል:: ከዚያም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ ብሎ የጌታን ድኅረ ትንሣኤ አስተርእዮ ዘረዘረ:: እኔ ማለትን የማይወደው ትሑት ቅዱስ ጳውሎስ "ከሁሉ በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ አለ::

ጭንጋፍ ምንድር ነው? ጭንጋፍ (ጸዕጻዕ/ ተውራድ) ለፅንስ የሚነገር ቃል ነው:: መወለድ ያለበትን ጊዜ ያልጠበቀ ያለ ጊዜው የተወለደ ፅንስ ነው:: በመጠኑ ከሌላው ጊዜውን ከጠበቀ ፅንስ የሚያንስ ሲሆን ዕድገቱን በተገቢው ጊዜ ከሚወለድ ልጅ ጋር ለማስተካከል ሲባል በሙቀት ማቆያ ክፍል እንዲቆይ ይደረጋል:: ይህ ፅንስ ሲወለድ በሕመም ውስጥ ሆኖ ተሰቃይቶ ተጨንቆ ነው::

ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን ለመግለጽ የተጠቀመበት ይህ አንድ ቃል የሕይወት ታሪኩን ጠቅልሎ የያዘ ድንቅ ቃል ነበር::
ቅዱስ ጳውሎስ ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ብርሃን የሆነ ሐዋርያ ቢሆንም እንደ ዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በጊዜው የተጠራ አልነበረም:: እርሱ ከሐዋርያት ጋር አብሮ በዳግም ልደት የተወለደ ሳይሆን ያለ ጊዜው ክርስቶስ ባረገ በስምንተኛው ዓመት የተጠራ ነበረና ራሱን ካለ ጊዜው ከተወለደው ፅንስ ጋር አመሳስሎ እንደ ጭንጋፍ የምሆን ብሎ ጠራ::

ጭንጋፍ ሲወለድ በመጠኑ ከሌላው ፅንስ ያነሰ ይሆናል::
ቅዱስ ጳውሎስም ራሱን ጭንጋፍ ካለ በኋላ "እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ" ብሎ አብራርቶታል:: (1ቆሮ 15:9)

ልጅ ጭንጋፍ ሆኖ ሲወለድ በሥቃይ ነው:: ጤና ያጣል ይታመማል:: እናቲቱም ትታወካለች በድብታ በጭንቀት ትቸገራለች:: ባለሙያዎቹ እንደሚሉት እናት ያለ ጊዜው ከተወለደ ልጅዋ ጋር እናታዊ ትስስር ለመፍጠርና የእናትነት ፍቅርዋን ለመሥጠት ባልጠበቀችው ጊዜ የመጣ በመሆኑ ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ትቸገራለች:: በአጭሩ ጭንጋፍ ሆኖ ሲወለድ እሱም ይሰቃያል እናቱንም ያስጨንቃል:: ወዲያው እንደሌላ ሕፃን በሰው እጅ አይታቀፍም:: ከተፈጥሮአዊ እስከ ሰው ሠራሽ እንደየጊዜው እየዘመነ በሔደው የልጅ ሙቀት መስጫ መንገድ እየታገዘ የሰውነት አካሎቹ በአግባቡ መሥራት እስከሚችሉና በሽታ መቋቋም እስከሚችል ይቆያል::

ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ጭንጋፍ ነበርኩ ያለው ለዚህ ነው:: በዳግም ልደት የተወለደው በደማስቆ መንገድ ወድቆ ሊቋቋመው ባልቻለው ብርሃን ተመትቶ ነበር:: "ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?" የሚል ድምፅ ሲሰማ ፅንስ ነውና ዓይኑን እንኳን መግለጥ አልቻለም ነበር::
ከተወለደ በኋላም ወዲያው ወደ ቤተ ክርስቲያን እቅፍ ወደ ሐዋርያት ማኅበር አልገባም:: እንደ ጭንጋፍ የምሆን እንዳለ ሙቀት ያስፈልገው ነበርና የሰው እጅ ሳያቅፈው ሦስት ዓመት በሱባኤ ቆይቶ በመንፈስ ቅዱስ ተማወቀ::

"ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ከሦስት ዓመት በኁዋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ" ብሎ ስለ መንፈሳዊ ኃይል መልበሱ ይናገራል:: (ገላ 1:15-18)

ጭንጋፍ ሆኖ የተወለደ ልጅ የሚገጥመው ችግር ከወላጆቹ ጋር በሥነ ልቡና ለመተሳሰር መቸገሩ ነው::
ቅዱስ ጳውሎስን ለማመንና እንደ ልጅ ለመቀበል የቤተ ክርስቲያን ማኅበርም ተቸግራ ነበር::
"ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት" ሐዋ 9:26 ስለዚህ ሐዋርያው እንደ ጭንጋፍ ነኝ አለ::

ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታ መነሣት ምስክሮች ብሎ ሌሎችን ከዘረዘረ በኋላ "ከሁሉ በኋላ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ታየኝ" ብሎ ተናገረ:: ክርስቶስ ተነሥቶአል ወይ ብለው ሲጠይቁህ አዎ ተነሥቶአል እነ እገሌ አይተውታል ብለህ ዘርዝረህ
"ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ" ብለህ መናገር መቻል እንዴት መታደል ነው!?

ወዳጄ ክርስቶስ መነሣቱን ታምናለህ:: ልክ ነህ ለብዙዎች ታይቶአል:: አንተስ ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ ማለት ትችል ይሆን? ጌታ ከተነሣ በኁዋላ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ለብዙዎች ታይቶአል:: ብዙዎቹ ቅዱሳን አይተውታል:: ቅዱስ እስጢፋኖስ አይቶታል : ቅድስት አርሴማ አይታዋለች : አቡነ ተክለ ሃይማኖት አይተውታል : አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ተመልክተውታል:: አባ ጳኩሚስ በዕንባ ተመልክቶታል : ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ አይታዋለች::

ሁሉም ቅዱሳን ብዕር ቢሠጣቸው ከዕንባ ጋር
"ከሁሉ በኁዋላ ለእኔም ታየኝ" ብለው የትንሣኤውን ማስረጃ ዝርዝር ይቀጥላሉ:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በበረሃ ሲጸልይ አይቶት ነበርና ሰው ባገኘ ቁጥር
ወቅቱ የፋሲካ ሰሞን ባይሆንም እንኳን በፈገግታ ተሞልቶ
"ክርስቶስ ተነሥቶአል!" ብሎ ያበሥርና ሰላምታ ይሠጥ ነበር::

ጌታ ሆይ ለእኔ ለኃጢአተኛው የምትታየኝ መቼ ይሆን? ቸርነትህን አይቻለሁ! ፍቅርህን አይቻለሁ! ብሩሕ ገጽህን የማየው መቼ ይሆን? መች እደርሳለሁ የአምላኬንስ ፊት መቼ አየዋለሁ? እኔም እንደ ቅዱሳንህ "ከሁሉ በኁዋላ ለእኔ ታየኝ" ብዬ የተቀመጠውን ብዕር አንሥቼ የምጽፈው መቼ ይሆን? አቤቱ ፊትህን እሻለሁ! አቤቱ ፊትህን ከእኔ አትመልስ! አቤቱ ፊትህን እሻለሁ!

"ኢየሱስ ክርስቶስ በግዕ ዘቀራንዮ
ለላሕይከ ንትሜነይ ከመ ንርአዮ"
"የቀራንዮው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ
ውበትህን ልናየው እንመኛለን"

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
16.6K views: ፦, 08:19
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2024-02-18 17:02:14

17.7K views: ፦, 14:02
ክፈት / አስተያየት ይስጡ