2024-03-27 22:56:01
ኒላ ዘ መንፈስ 2
(አሌክስ አብርሃም)
በክፍል አንድ ትረካችን አናላ ወይም በቁልምጫ ስሟ ኒላ የምትባል ህንዳዊት ሴት ከፍቅረኛዋ ጋር ይጓዙበት የነበረ የመንገደኞች ባቡር ሐዲዱን በመሳቱ ትሞታለች። ይች ሴት በዘመድና ወዳጆቿ ዘንድ የምትታወቀው በውብ ጥቁር ፀጉሯ ሲሆን እርሷም ለፀጉሯ ያላት ፍቅር እና እንክብካቤ የማምለክ ያህል ነበር። ምን ያደርጋል ያ አደጋ ነፍሷን ነጠቃት። ሰው ሟች ነው! ቆንጆም ሴት ትሁን ጀግና ወንድ ማንም ከዚህ ህግ አያልፍም። ይሁንና ኒላ ለራሷም ባልገባት ሁኔታ ከሁለት ዓመት በኋላ እዚች ምድር ላይ ያውም ኢትዮጵያ ፣ ያውም ፊደል የተባለች ታዋቂ ኢትዯጵያዊ የፊልም ተዋናይት ውስጥ መንፈስ ሁና ተከሰተች። ኒላ ራሷ እንደምትለው ለሁለት አመት የት እንደነበረች ምን እንደነበረች አታውቅም! የምታውቀው ነገር ተዋናይቷ የገዛችው «ሂውማን ሄር» የኒላ እንደነበርና ተዋናይቷ ፀጉር ጋር ሲነካካ ለሁለት ዓመት ሙት የነበረ ፀጉሯ ህይዎት እንደዘራ፣ ወዲያው በፀጉሩ በኩል ሙሉ መንፈስ ሁና ሰውነቷ ውስጥ እንደገባች ነው። ቀጣዩን እነሆ . . .
** * ****
የዛን ቀን ምሽት ፊደል መተኛት አልቻለችም! በፍርሃት አልጋዋ ላይ ተቀምጣ ሳታቋርጥ ውስጧ ተቀምጣ የምታወራውን ኒላ ግራ በመጋባት ታዳምጣለች።
«ተነሽ ገላችንን እንታጠብ፤ በላብ ጠረን ገደልሽኝኮ » አለች ኒላ! ፊደል አሁንም እያላባት ቢሆንም ምን ትሁን ምን ትፈልግ የማታውቃት እንግዳ ፊት ልብሷን ማውለቅ ፈራች! በቀስታ «የእኔ እህት ለምን ወደምትሄጅበት አትሄጅልኝም ? ፀጉርሽንም ውሰጅው አልፈልግም በጣም እያስጨነቅሽኝ ነው!» አለቻት!
« አንች የማይገባሽ ደደብ ሴት ነሽ ልበል? ነፍስሽን ከስጋሽ «ተለይተሽ ሂጅ» ማለት ትችያለሽ? ራሴን እንዳጠፋ እየጠየቅሽኝ ነው? በቃ ይሄ የአንች ሰውነት የእኔም ነው! ፈልጌሽ አልመጣሁም! ደህና ያረፈ ነፍሴን አምጥተሽ የቀሰቀሽው አንች ነሽ! እንዴት እንደገባሁም እንዴት እንደምሄድም አላውቅም ! ያለን አማራጭ ተከባብረን አብረን መኖር አለበለዚያ ተያይዘን ወደመቃብር መውረድ ነው! ይብላኝ እንጅ ላንች፣ መሞት እንደሆነ ለእኔ ብርቄ አይደለም. . . ይልቅ ተነሽ እንታጠብ እንዴት ነው ላብ በላብ የሆነው በቡድሃ! ለሞላ ሰውነት እዚች ውስጥ ታስቀምጠኝ! » አለች በቁጣ!
ፊደል እየተንቀጠቀጠች ወደሻወር ሄደች! ልብሷን በፍርሃት . . . በቀስታ አወላለቀች! የሻወሩን ውሃ በቀስታ ከፍታ ሙቀቱን በእጇ «ቸክ » ካደረገች ኋላ በደንብ የሞቀ ውሃ እስኪወርድ ሰውነቷን በእጇ ከልላ ዳር ላይ ቆመች! ጠባቡ ሻዎር በእንፋሎት መታፈን ሲጀምር በቀስታ ወደሚወርደው ውሃ ራመድ አለች!
«እንዴ ፀጉርሽን ሳትሸፍኝው ልትገቢ ባልሆነ?» አለች ኒላ ! በጩኸት!
«እረስቸው ነበር » ብላ ሮዝ ቀለም ያለውን የፀጉር መሸፈኛ የፕላስቲክ ቆብ አጠለቀች ! እና የቀኝ ትከሻዋን አስቀድማ ወደውሃው ገባች! ውሃው የፀጉር መሸፈኛው ላይ ሲያርፍ ዝናብ የቆርቆሮ ጣራ ላይ የሚፈጥረው አይነት ድምፅ ይፈጥራል! ወይም እንደዛ ይመስላታል ፊደል።
«ኡኡኡኡ አንች የማትረቢ ሴት አብደሻል? ወደዛ ውጭ ! » ብላ ጮኸች ኒላ! ጩኸቷ ጎረቤት ሁሉ ይሰማ ነበር!
«እንዴ ምን ሁነሻል? ታጠቢ አላልሽኝም እንዴ?» ብላ ዘላ ወጣች!
«እና ታጠቢ ማለት ተቀቀይ ነው?እንደዚህ በተፍለከለከ ውሃ የምትቀቀይው ድንች ነሽ? ለነገሩ ከአንች ድንች ይሻላል ከንቱ! በዚህ አይነትማ ፀጉሬን ከጥቅም ውጭ ነው የምታደርጊው. . . ቆይ ቆይ ለመሆኑ ተምረሻል? ወይስ ይሄን መቀመጫሽን እያገማደልሸ ብር የሚያሳይሽ ማንም እከካም ቦርጫም ባለትዳር ጋር መተኛት ብቻ ነው እውቀትሽ?»
« ለምን ስትናገሪ ስርዓት አይኖርሽም ? እኔ ሴት አዳሪ አይደለሁም፣ የተከበርኩ የፊልም ባለሙያ ነኝ! ለከት ይኑርሽ ! መንፈስ ሁኝ ፀጉር የራስሽ ጉዳይ ነው! . . . » ብላ ቱግ አለች ፊደል! እንባ እየተናነቃት!
«ሂሂሂሂሂሂ ! የተከበርኩ? ማነው የሚያከብርሽ? ሂሂሂሂ ያች ጓዝ ሚስቱ ስትደብረው ነው አንች ጋር እየመጣ የሚዝናናው ትራክተር የሆነ ሰውየ ?! ወይስ ያ ካሜራ ፊት እንደበቀቀን የሚጮህ ዳይሬክተር ተብየ? ስሙንማ ይዞታል!የታባቱ ተምሮ ነው ዳይሬክተር የሆነው? የዩ ቲዮብ ምሩቅ ወይስ "ዳይሬክተር" የዳቦ ስም መሰለው እናቱ የምታወጣለት? አንችም "ዳይሬክተር አወጣኝ" እያልሽ ቀሚስሽን ትነሰንሻለሽ! ልብሽ እብጥ ብሏል!
"እንዴዴዴ"
"የምን እንዴ ነው! ያም ቦርጫም እከካም በገንዘቡ ነው የገዛሽ ፤እንደትራክተር! ትራክተር እንኳን ያርሳል፣ አንች በጀርባሽ ተነጥፈሽ የሰው ባል አምሮት መወጫ ከመሆን ውጭ ምን ጥቅም አለሽ? ፊልም ትላለች እንዴ ? ቦሊውድን ያላየ! ሁለተኛ እንደዚህ ትጮኺብኝና አሳብጀ ልብስሽን አስጥየ ነው መሳቂያ የማደርግሽ! ከንቱ! ሸር . . ጣ! አሁን ውሃውን አቀዝቅዥው ! ዘንቧጣ! ደግሞ ራቁትሽን ሲያዩሽ ምንድነው የምትመስይው? ልብስ ነው ሰው ያስመሰለሽ! ከአምስት ዓመት በኋላ ማንም ዙሮ የማያይሽ ቆዳ ፊት ነው የምትሆኝው! ያ ሰሊጣምና ትራክተራም ራሱ እንዳላየ ነው የሚያልፍሽ »
ፊደል ተሳቀቀች! ማንም በሰውነቷ እንዲህ ዝቅ አድርጓት አያውቅም! አይቷት የማይንሰፈሰፍ ወንድ የለም! ቢሆንም መመላለስ አልፈለገችም! ሲጀመር ምን ጋር ነው የምትመላለሰው? ይችን ጉድ ፈራቻት፤ ይችን አስቀያሚ ሴት ክፉኛ ፈራቻት! እናም በትህትና « እኔኮ ቀዝቃዛ ውሃ ስለማልወድ ነው» አለች! ፍርሃት በተቀላቀለበት ሳግ የሚተናነቀው ድምፅ ! ይችን ፍጥረት ትሁን ቅዠት ምኗም መጋጨቱ ...! እንደውም ወደፖሊስ ጣቢያ ሂዳ ኡኡ ልትል አማራት!እዛው አሳድሩኝ ልትል ፈለገች፤ ፈራች በጣም ፈራች!
«ወደድሽ አልወደድሽ ግድ አይሰጠኝም! ሰውነቱ የጋራችን መስሎኝ! በሙቅ ውሃ የተቀቀለ አስቀያሚ ሰውነት ውስጥ ተቀምጨ መኖር የሚያስደስተኝ ይመስልሻል? ወጣት ነኝ ሳልሞት በፊት ገና ሃያ አራት ዓመቴ ነበር ! ግን ደደብ አልነበርኩም! ስለሙቅ ውሃ በኃላ አስረዳሻለሁ! አሁን ሙቀቱን ቀንሽው በይ ! ምናይነቷ ውስጥ ነው ያስቀመጠኝ ? ቆንጆ ብቻ ! » ተነጫነጨች! ፊደል ቀዝቃዛ ውሃውን ጨመረችው እና «አሁንስ?» አለቻት የማትታይ የማትታወቅ ሴት በራሷ ፍላጎት ላይ ፈቃድ መጠየቋ ደግሞ አበሳጫት!
«በእጅሽ ሞክሪዋ እኔ መንፈስ ነኝ! እጅ የለኝ እግር ፤በአንች እጅ ነው የማውቀው !» ፊደል እጇን ዘርግታ የሚወርደውን ውሃ ሞከረችው
«አሁንም ትኩስ ነው በደንብ ቀንሽው » ቀነሰችው «አሁን ይሻላል! »
ፊደል በጣም ከመፍራቷ ብዛት ውሃ ውስጥ ሁና ሁሉ ያልባት ነበር። «ይልቅ የገላ ሳሙናሽ ሸታው ደስ ሲል» ፊደል አልመለሰችም! ኒላ ወሬዋን አላቆመችም! « ኡፍፍ ሻዎር ስወስድ. . . ፍቅረኛየ ሮሃንን ነው የማስታውሰው ! በጣም የሚያምር አስተማሪ ነበር . . .እንደዛ ሰሊጣም ሽማግሌሽ እንዳታስቢው! እዛ እከካም ዳይሬክተር ተብየ ጋርም እንዳታወዳድሪው ! ወንዳወንድ ነበር. . . ጅኒየስ! ብዙ ሐሳብ ነበረን!ብዙ! " ጮክ ብላ ማንጎራጎር ጀመረች
የህንድ ተራሮች ግዝፈት
ሞገስህን አይሸፍኑም
ሙቀት ያለህ ስሜት ያለህ
ተራራ ነህ ውብ ተራራ
በአለት ማንነትህ ውስጥ
ፍቅር የሚንተገተግ
እንደ እሳተ ገሞራ ...
6.5K viewsPapi, 19:56