2022-05-19 09:37:19
ሰላም ለእርስዎ ይሁን!
አንድ ሰው የወንጀል ድርጊት ፈጽሞ ከተገኘና በፍርድ ቤት ቅጣት ከተጣለበት በኋላ ቅጣቱን ሳይጨርስ ሊፈታ ነው ወይም ተፈታ ሲባል ሰምተው ያውቃሉ? ለምንና እንዴት ይህ ሊሆን እንደሚችልስ ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? እንግዲያውስ መሰረቷን በተሻሻለው የኢፌደሪ የወንጀል ህግ ላይ ያደረገችውው ይህችን አጭር መልእክት በማንበብ ስለአመክሮ ያለዎትን ግንዛቤ በጥቂቱም ቢሆን ያሳድጉ!
አመክሮ፡- አንድ ተቀጪ በእስር ወቅት ባሳየው መልካም ጠባይ የተነሳ የተጣለበትን ቅጣት ሙሉ በሙሉ ሳይፈጽም አስቀድሞ ከእስር በመልቀቅ ጠባዩን ለማሻሻልና ወደ መደበኛው ማህበራዊ ኑሮ ለመመለስ ሲባል የሚሰጥ የፈተና ወይም የሙከራ ጊዜ ነው።
ማንኛውም ተቀጪ በአመክሮ ለመፈታት እጩ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው በቅድሚያ የሚከተሉትን ዝቅተኛ መስፈርቶች አሟልቶ ሲገኝ ነው፡-
ሀ) ከተወሰነበት የእስራት ጊዜ ከሶስት እጅ ሁለቱን እጅ ሲፈጽም፤
ለ) ፍርዱ የእድሜ ልክ እስራት ሲሆን ሀያ አመት ሲፈጽም፤
ሐ) አስፈላጊ የሆነውን ነጻነት የሚያሳጣ ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ በመፈጸም ላይ ሳለ በስራውና በጠባዩ የተረጋገጠ መሻሻል ካሳየ፤
መ) በፈጸመው የወንጀል ድርጊት ምክንያት ለደረሰው ጉዳት በፍርድ ቤት በተወሰነው መሰረት ወይም ከተበዳዩ ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት በተቻለ መጠን ሊከፍል የሚጠበቅበትን ካሳ ለመክፈሉ ማረጋገጫ ካቀረበ፤ እና
ሰ) አመሉና ጠባዩ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚያስችለውና በአመክሮ መፈታቱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ የሚታመንበት ሆኖ ከተገኘ።
ለየት ያለ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር የአመክሮ ጊዜ የሚቆየው በመሰረቱ ተቀጪው ሳይፈጽመው የቀረው ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ እስኪፈጸም ድረስ ነው። ሆኖም አመክሮ የሚቆይበት ጊዜ በማናቸውም ሁኔታ ከሁለት አመት ሊያንስ እና ከአምስት አመት ሊበልጥ እንዲሁም ለእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጪዎች ከአምስት አመት ሊያንስ እና ከሰባት አመት ሊበልጥ አይችልም።
ማሳሰቢያ! በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ መሰረት ልማደኛና ደጋጋሚ ወንጀለኞች በፍጹም በአመክሮ ሊፈቱ አይችሉም!
ግንቦት 10 ቀን 2014 ኣ.ም
ፋሲካ አጌና (አቃቤ-ህግ)
175 viewsfasika aggena, 06:37