Get Mystery Box with random crypto!

እብሎይ ግን የቀድሞ ጸሎቱን አላቋረጠም እንዲህም እያለ እኔ ክፉ ባሪያ በየሰባቱ ሰባ ጊዜ በደልኩ | ብስራት ሚዲያ

እብሎይ ግን የቀድሞ ጸሎቱን አላቋረጠም እንዲህም እያለ እኔ ክፉ ባሪያ በየሰባቱ ሰባ ጊዜ በደልኩ ቸር ጌታ ሆይ መሐሪ አባት ሆይ ይቅር በለኝ የማይበድል ባሪያ የማይምር ጌታ የለምና። በዚችም ዕለት እስከ ሌሊቱ እኩሌታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አደሩ እርሷም እሑድ ናት:: በዚያችም ጊዜ ከፊተኛው የሚበልጥ የሽቱ መዓዛ ሸተተ ገዳማዊውም ወንድሜ ዕብሎይ ና በውኃ ታጠብ ደስ ይበልህም በዚች ሰዓት ከተቀበልከው መከራ ታርፋለህና አለው:: በዚያንም ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለሁለቱም ቍርባኑን አቀበላቸው አባ ዕብሎይም አረፈ መላእክትም ነፍሱን ተሸክመው እስከ አርያም በረሩ።

ያ ገዳማዊም እኔ ሽማግሌ ነኝ ሥጋውን መሸከም አልችል የምቆፍርበትም የሌለኝ ምን አደርጋለሁ ብሎ የሚያስብ ሆነ በዚያንም ጊዜ ሁለት አንበሶች መጥተው ለሥጋው ሰገዱ መቃብሩንም ቆፍረው ሥጋውን እንደ ሰው ተሸክመው ወስደው ቀበሩት ገዳማዊውንም እጅ ነሱት እርሱም ባረካቸውና በሰላም ሔዱ።

ከዚህም በኋላ ያ ገዳማዊ የሚቀብረኝ አገኝ ይሆን ብሎ አሰበ ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ አትዘን ሥጋህን እኔ አስቀብራለሁ ያለ ሦስት ቀንም አልቀረህም ወዳንተም ሦስት ሰዎችን እልካለሁ የበግ ጠባቂው የአባ እብሎይን ገድል ንገራቸው እነርሱም ለሌሎች ይንገሩ ከእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ እንዳይቆርጡ በኃጢአት ለወደቁ አለኝታ ይሆን ዘንድ።

በማግሥቱም ሦስት ሰዎች መጡ እርሱም የበግ ጠባቂውን የአባ ዕብሎይን ተጋድሎ ነገራቸው እነርሱም እጅግ አድንቀው ጻፉት ከገዳማዊውም ዘንድ እስከ ሦስት ቀን ተቀመጡ ከዚህም በኋላ ገዳማዊው ተነሥቶ ጸለየ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ እነዚያ ሁለት አንበሶችም መጡ መቃብርንም ቆፍረው እንደ ሰው ወስደው ቀበሩትና ከእነዚያ ሦስት ሰዎች ጋር ተጓዙ ወደ አስቄጥስ ወደ አባ መቃርስ ገዳም እስከሚአደርሷቸው መርተው ወሰዱአቸው ሰዎቹም የሆነውን ሁሉ ለመነኰሳቱ ነገሩአቸው። እነርሱም እጅግ አደነቁ የበግ አርቢው የአባ ዕብሎይን ገድል ጻፉ ሁል ጊዜም በእሑድ ዕለት የሚያነቡት ሆኑ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አሞኒ

በዚህችም እለት ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጻድቃን አቡነ አሞኒ የተወለዱበት በዓልና ለልጃቸው አቡነ ዮሐኒም መታሰቢያቸው ነው፡፡ አባታችን የካቲት5 ቀን አክሱም ውስጥ ሲወለዱ ሰይጣናት የወላጆታቸውን ቤት ከበው በማየታቸው እንደተወለዱ በእጃቸው ቢያመለክቱ በአንድ ጊዜ 60 ሰይጣናት ተሸንፈው እንጢስ በነው ጠፍተዋል። አሞኒ ማለት አሸናፊ ማለት ነው። አባ አሞኒ የራስ ፀጉራቸው ልብስ መጎናጸፊያ ሆኖቸው የኖሩ ታላቅና ቀደምት አባት ናቸው።

በደመና ተጭነው ኢየሩሳሌም ደብረ ዘይት ድረስ በመሄድ ከአባ ዕብሎይ ጋር ተገናኝተው ብዙ ምሥጢርን አውርተዋል። አባ ዮሐኒንያ ሳደጉት አስተምረው ያሳደጓቸው አባ አሞኒ ናቸው፡፡ የእናቱን ጡት ፈጽሞ ጠብቶ የማያውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸውን አባ ዮሐኒን እሳቸው እያጫወቱት የታዘዘ አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው ቶራ (ሰሳ) እያጠባችው ነው ያደገው፡፡

አባ አሞኒ ልጃቸው አባ ዮሐኒ አድጎ 12 ዓመት ሲሆነው ከዚህም በኋላ ዲቁና ሊያሾሙትና አክሱም ጽዮን ወስደው ሊያስባርኩት ቤተ ካህናት ከተባለው ቦታ ይዘውት ሲሄዱ ልዩ ስሙ ሲሂታ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ከወገባቸው በላይ እራቁታቸውን የሆኑ እንስራ የተሸከሙ ዐሥር ሴቶች አገኙ፡፡ አባ ዮሐኒም አባታቸውን "አባቴ እነዚህ ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ጽጉራቸው የረዘመ ምንድን ናቸው? እንደ እኛ የሆኑ መስህታን የሚባሉት እነዚህ ናቸውን?" አሏቸው፡፡ አባ አሞኒም "አይደሉም ልጄ ዝም ብለህ ሂድ" አሏቸው፡፡ በኋላ ግን ትዝ ሲላቸው "በዱር እንስሳት ያሳደኩት ልጄ ወንድና ሴት ለይቶ ሲያውቅ በዚያው ሊሳሳት አይደልምን?" ብለው በማሰብ ዲቁናና ክህነቱ ይቅርበት ብለው ተመልሰው ወደ በዓታቸው ይዘውት ገቡ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ አበይዶ ወደ አባ አሞኒ መጣና እሳቸውን ከአባ ዮሐኒ ጋር እያገለገሏቸው ተቀመጡ፡፡ ዮሐኒ እየጻፈ አበይዶ የሚጻፍበትን ቆዳ እያዘጋጁ ሦስቱም በአንድነት በተጋድሎ መቀመጥ ጀመሩ፡፡

አባ ዮሐኒ ሃያ ዓመት አባ አሞኒ ደግሞ አርባ ዓመት በሆናቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸውና "አሞኒ ሆይ ከእንግዲህስ እግዚአብሔር ወደኔ ና ብሎሃል" አላቸው። እሳቸውም ልጆቻቸውን አባ ዮሐኒንና አባ አበይዶን ጠርተው "በሉ እንግዲህ እኔ ወደ እግዚአብሔር መሄዴ ነውና ጸልዩልኝ" አሏቸው፡፡ ከማረፋቸውም በፊት አባ ዮሐኒን ለብቻቸው ጠርተው "አንተ አባ ዮሐኒ ካሁን በፊት ሲሂታ ላይ ያየሃቸው ሴቶች ናቸው፣ አዳምንም ከገነት ያስወጡ ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደ እነርሱ ያለ የደረሰብህ እንደሆነ ካለህበት ገደል ተወርውረህ ውደቅመ በባሕር ውስጥ ጥለቅ" ብለው ነግረዋቸው ዕለት ኅዳር5 ቀን በሰላም ዐረፉና ወደ ጠራቸው እግዚአብሔር ሄዱ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #መዝገበ_ቅዱሳን)
@Bisrat_Midea