Get Mystery Box with random crypto!

#የካቲት_5 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የካቲት አምስት በዚች ቀን | ብስራት ሚዲያ

#የካቲት_5

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት አምስት በዚች ቀን የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት #ቅዱስ_አክርጵዮስ አረፈ፣ አባት ጴጥሮስ የተባለ #አባ_ብሶይ አረፈ፣ አስቀድሞ ራሱን ለኃጢአት አስገዝቶ የነበረ ጽኑዕ ተጋዳይ #አባ_ዕብሎይ አረፈ፣ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጻድቃን #አቡነ_አሞኒ የተወለዱበት ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አክርጵዮስ

የካቲት አምስት በዚች ቀን የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባት አክርጵዮስ አረፈ። እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥረኛ ነው።

ይህም አባት እግዚአብሔርን የሚፈራ ንጹሕ ቅዱስ ነው ። በእስክንድርያ አገርም ቄስ ሁኖ የሚያገለግል ነበር ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ከላድያኖስ በአረፈ ጊዜ የእስክንድር አገር ሕዝቡና ኤጲስቆጶሳቱ መረጡት በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

ከዚህም በኋላ እንደ ሐዋርያት መልካም ጉዞን ተጓዘ የእግዚአብሔርን ሃይማኖት ሕይወት የሆነ ሕጉንም እያስተማረ ቅዱሳት መጻሕፍትንም እያነበበላቸውና እያስተማራቸው መንጋዎቹን ይጠብቃቸው ነበር ሁል ጊዜም ይመለከታቸዋል አንድ የብር አላድን ወይም አንድ የወርቅ ዲናርን ጥሪት አላኖረም ከዕለት ምግቡ ከቁርና ከሐሩር ሥጋውን ከሚሸፍንበት ልብስ በቀር ምንም አላከማቸም።

በዚህም ተጋድሎ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኑሮ ጌታችንንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ብሶይ

በዚችም ዕለት ተጋዳይ የሆነ አባት ጴጥሮስ የተባለ አባ ብሶይ አረፈ እርሱም ከላይኛው ግብጽ አክሚም ከሚባል ከተማ ነው። በጐልማሳነቱም ጊዜ የከፉ ሥራዎችን የሚሠራ ሁኖ ነበር በመብላትና በመጠጣትም ይደሰት ነበር። እግዚአብሔርም የነፍሱን ድኅነት ሽቶ ጽኑ ደዌ አመጣበትና ለመሞት ተቃረበ።

ነፍሱንም በተመሥጦ አውጥተው የሥቃይ ቦታዎችንም ጥልቅ የሆነች ጕድጓድንም አሳዩት፡፡ በዚያም ብሩህ ልብስ የለበሱ ሰዎች አሉ በእጆቻቸውም የሰው በድን ነበረ አራት ክፍል አድርገው ለያዩትና የሰውን ገንዘብ የሚሰርቀውን ሁሉ እንዲህ ያደርጉበታል አሉት። ይህንንም ነገር በሰማ ጊዜ ጮኸ ከልቡም አዝኖ አለቀሰ ከዚህም በኋላ ነፍሱ ተመለሰች ዐይኖቹንም ወደ ሰማይ አቅንቶ ጌታዬና ፈጣሪዬ ከዚህ ደዌ ከአዳንከኝ እኔ ስለ ኃጢአቴ ንስሐ በመግባት በፍጹም ልቡናዬ አመልክሃለሁ ከእንግዲህም ከቶ ለዘላለሙ የሴት ፊት አላይም አለ።

በዚያንም ጊዜ ከደዌው አዳነውና ተነሥቶ ብንዋይ ወደሚባል ገዳም ሔደ መነኰሳቱም ከፈተኑት በኋላ የምንኲስናን ልብስ አለበሱት በግብጽ አገር ሁሉ እስከሚሰማ ታላቅ ተጋድሎን በጾም በጸሎት በመስገድም ተጋደለ ከሁሉ በላይም ከፍ ከፍ አለ ለመነኰሳትም ትምህርት የሚሆኑ የሚጠቅሙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ አንድ ጊዜም እንጀራ ሳይቀምስ ውኃ ሳይጠጣ አንድ ወር ጾመ እንዲህም እየተጋደለ ሠላሳ ስምንት ዓመት ያህል ኖረ።

መላዋንም ሌሊት በጸሎትና በስግደት በመትጋት ቁሞ ያድራል ሰዎች የሚሠሩት ሁሉ ጻድቅም ቢሆን ኃጢአተኛም ቢሆን በፊቱ ግልጥ ሆነ ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመና በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ዕብሎይ_ገዳማዊ

በዚህችም ቀን አስቀድሞ ራሱን ለኃጢአት አስገዝቶ የነበረ ጽኑዕ ተጋዳይ አባ ዕብሎይ አረፈ። ይህም የበጎች አርቢ ራሱን ለሰይጣን በማስገዛት ከኃጢአት ሥራ ምንም የቀረው የለም ያመነዝራል ይሰርቃል ይቀማል ይገድላል በዚህም የሰይጣንን ሥራ እየፈጸመ አርባ ዓመት ያህል ኖረ።

በአንዲትም ዕለት ከቀኑ እኩሌታ ከበጎቹ ጋር በዱር ውስጥ ሳለ እነሆ የመውለጃዋ ጊዜ የደረሰ ያረገዘች ሴትን አየ ሰይጣንም በልቡ ክፉ ሐሳብን ጨመረ እንዲህም አለ የተረፈችኝ ኃጢአት አንዲት አለች እርሷም ያረገዘች ሴት ሆዷን ሠንጥቄ በእናቱ ሆድ ሕፃኑ የሚተኛበትን አይ ዘንድ ነው።

ያን ጊዜም ተወርውሮ ሔደ በራስዋ ጠጕር ይዞ ከምድር ላይ ጣላት ሾተልም አንሥቶ ሆዷን ሠነጠቀ ሕፃኑንም በማሕፀኗ ውስጥ እንዴት ሁኖ እንደተኛ አየው እርሷም በጻዕር ተጨንቃ አስቀድማ ሞተች ሕፃኑ ግን በጻዕር እየተሠቃየ ብዙ ቆይቶ ሞተ። በግ አርቢውም የሠራውን ይህን ታላቅ ኃጢአት ተመልክቶ ደነገጠ እጅግም አዘነ መራራ ልቅሶንም በማልቀስ ታላቅ ኃጢአትን ሠርቻለሁና ወዮልኝ አለ።

በዚያንም ጊዜ በጎቹን እንደተበተኑ ትቶ በእጁ በትሩን ብቻ ይዞ ወደ አስቄጥስ ገዳም እስከሚደርስ እያለቀሰ ተጓዘ ወደ አረጋውያን መነኰሳትም አልገባም ከእርሳቸው ዐሥር ምዕራፍ ያህል ርቆ ወደ በርሀ ውስጥ ገባ እንጂ በቤት ውስጥም አያድርም ነበር ከአራዊት ጋር የሚኖር ሆነ እንጂ ከዕፀዋትም ፍሬ በየጥቂቱ ይመገብ ነበር ከዕንባ ጋርም እየጮኸ አቤቱ በደልኩ ክፉ ሥራንም ሠራሁ ይቅር በለኝ እኔ ኃጢአተኛ የሆንኩ ክፉ ባርያ ነኝና አንተም ቸር አምላክ ይቅር ባይ አባት ነህና የማይበድል ባሪያ የማይምር ጌታ የለምና ይቅር በለኝ እንዲህም እየተጋደለ አርባ ዓመት ኖረ።

ከሌሊት ቍር ከቀን ፀሐይ ሐሩርና ትኩሳት የተነሣ ሥጋው ደርቆ ጠቆረ ከዚህም በኋላ እንዲህ የሚለውን ቃል ሰማ ስለ ሴቲቱ ደም ጌታ ይቅር ብሎሃል ጽና በርታ ይህንንም ያለው እንዳይታክትና ዳግመኛ በኃጢአት ውስጥ እንዳይወድቅ ነው።

ይህንም በሰማ ጊዜ ከሦስት ቀን ብቻ በቀር ያቺን ዓመት እስከሚፈጽም መሪር ልቅሶ እያለቀሰ ተጋድሎውን ጨመረ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ከእርሱ ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ርቆ የሚገኝ ከቶ ሰውን ሳያይ በዚያች በረሀ ሰባ ዓመት የኖረውን አንዱን ገዳማዊ አንተ ካለህበት ቦታ ወደ ውጭ ሒድ ሽማግሌ ሰው ታገኛለህ ኃጢአቱን ከአመነልህ አጽናናው ኃጢአትህ ሁሉ ስለ ሕፃኑም መገደል ተሠርዮልሃል በለው በማለት አዘዘው።

በዚያንም ጊዜ ያ ገዳማዊ ሒዶ አገኘው አርስበርሳቸውም ሰላምታ ተሰጣጡ እርሱ ዕብሎይ ግን ያለማቋረጥ ያለቅስ ነበር ገዳማዊውም የሠራኸውን ንገረኝ በምን ምክንያትስ ወደዚህ መጣህ አለው። እርሱም ሁሉንም ነገረው ያረገዘችዋንም ሴት ሆድዋን እንደሠነጠቀ ነገረው ገዳማዊውም ኃጢአትህ ሁሉ ተሠርዮልሃል አባቴ ሆይ ደስ ይበልህ ነገ የእግዚአብሔር መልአክ ወዳንተ መጥቶ የክርስቶስን ሥጋና ደም ያቀብልሃል አለው።

የቀዳሚት ሰንበት ዕለትም በነጋ ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሁኖ የማያውቅ ጣፋጭ ሽታ ሸተተ አባ ዕብሎይም ገዳማዊውን አባቴ ሆይ ከፍርሀት የተነሣ ነፍሴ ከሥጋዋ ልትለይ ደረሰች አለው ይህንንም ባለ ጊዜ በመነኰስ አምሳል ከአጠገቡ ቁሞ መልአኩን አየው እርሱም ተቸገርኩ እግዚአብሔርም አዳነኝ:: ነፍሴ ሆይ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሽ:: እግዚአብሔር ረዳትሽ ነውና፡፡ ነፍሴን ከሞት አድኗታልና። ዐይኖቼንም ከእንባ እግሮቼንም በዳጥ ከመሰናከል። በሕያዋን አገር እግዚአብሔርን አገለግለው ዘንድ እያለ ይዘምር ነበር።

የበጎች ጠባቂ የነበረ አባ ዕብሎይም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ወድቆ እንደ በድን ሆነ መልአኩም በሰው አምሳል እጁን ዘርግቶ አነሣው ልቡም ጸንቶ በመልአክ እጅ ከሰማይ የወረደለትን ሥጋውንና ደሙን ተቀበለ መልአኩም ወደ ሰማይ ዐረገ።

አባ ዕብሎይም ቍርባኑን በተቀበለ ጊዜ ሰውነቱ ሁሉ እንደ በረድ ፀዓዳ እንደ ፋናም ብሩህ ሆነ በዚያችም ዕለት ሁለቱም ደስ እያላቸው እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ እስከ ማታ ዋሉ።