Get Mystery Box with random crypto!

ያሬዳውያን: በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሕዱ አምላክ አሜን። ክርስቶስ ተንሥአ እምሙታ | ቤተ_ዜማ

ያሬዳውያን:
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሕዱ አምላክ አሜን።

ክርስቶስ ተንሥአ እምሙታን በዐቢይ ኃይል ወስልጣን አሰሮ ለሰይጣን አግዓዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍስሐ ወሠላም።

             ልደታ ለማርያም

{ መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን }
                መዝ 86÷1

እመቤታችን ልደቷ እንደእንግዳ ደራሽ እንደውኃ ፈሳሽ ሆኖ ሳይነገር ሳይታወቅ ሳይጠበቅ የመጣ አይደለም፤ እንደልጇ ሁሉ አበው ሲሿት በምሳሌ ጥላነት ሲያዩዋት፣ ነቢያቱ ሲተነበዩላት ዳዊት ልጄ ሆይ ስሚኝ በማለት ሰሎሞንሞ እቴ ሙሽራዬ እያለ በትንቢት መነጽርነት ሲያናገራት የነበረች ናት እንጂ ።

አስቀድሞ ለአዳም በገባለት ቃልኪዳን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለው በማለት እርሱ ይወለድባት ዘንድ ያላት የመረጣት የአዳም የልጅ ልጅ እንደምትወለድና ከእርሷም እንደሚወለድ ነግሮታል።

ከዚህ በጎላ እና በተረዳ ግን ነቢዩ ኢሳይያስ "ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓዐርግ ጽጌ እምኔሃ" ... ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከግንዱ ይወጣል ... በማለት በትር ብሎ በትረ አሮን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእሴይ ሥር ከዳዊት እንደምትወለድና ከእርሷም ጽጌ የተባለ ክርስቶስ እንደሚወለድ ተናግሯል።

የእመቤታችን ልደት ሊቁ "መኑ ይእቲ እንተ ትሔውጽ ከመጎኅ ያላት" ... ይህች እንደማለዳ ፀሐይ ያለች ማናት ... በማለት የገለጣት ለአማናዊው ፀሐይ ጎኅ፤ ለአማናዊው ወንጌል ንዑስ ወንጌል የሆነች የእመቤታችን ልደቷ ለልደተ ክርስቶስ ጎኅ ሆኖልን፤ በእርሷ መወለድ የእርሱን ሰው ሆኖ መወለድ እውን ሆኖልን ያረጋገጥንበት ነው።

ደራሲም ድንግል በልደቷ ለአዳምና ለልጆቹ ከመርገሙ መዳኛ ስለመሆኗ እንዲህ ብሎ ይጠቅሳል :-

ማርያም ድንግል በልደትኪ መጠነ አቅሙ፤
አዳም ይዌድስኪ ምስለ ደቂቀ ኩሎሙ፤
እስመ ለአዳም ብኪ ተስእረ መርገሙ።
        መልክአ ልደታ

የእመቤታችን ልደት ከአምስቱ ልደታት አንዱ የሆነው እንደ ልደተ አቤል ያለ ይኸውም ከእናትና ከአባት የሚወለዱት ልደት ነው። ልደቷም መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን... መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው..  በማለት ቅዱስ ደዊት "አድባር ቅዱሳን" ብሎ ከገለጣቸው በምድር  ከተነሱት ሁሉ በግብራቸው በጽድቃቸው በትሩፋት በክብር  እንደ ተራራ ከፍ ብለው ከሚታዩት ከተነሱት ከታላላቅ ቅዱሳን ወገን ነው። ታሪክ በእንተ ልደተ ማርያም

ጰጥሪቃና ቴክታ የሚባሉ ደጋግ ቅዱሳን ባለጸጋ ለእንሶቻቸው የወርቅ ጉትቻ እስኪያረጉ ድረስ ሁሉ የተትረፈረፋቸው ሰዎች ነበሩ። እነርሱም መካን በመሆናቸው ያዝኑ ነበር። አብዝተውም እግዚአብሔርን ለመኑት ጠየቁትም  በኋላም ሕልምን አዩ።

ሕልሙንም ሕልም ፈቺ ዘንድ ሔደው ፍቺውን ጠየቁት። እርሱም ነጭ ጥጃ መልኳ ደምግባቷ ያማረ ምግባሯ የተወደደ ሴት ልጅ ናት። እንዲህ አይነቷ እሷን የምትመስል እየወለደች ትሔዳለች፤ የመጨረሻዋ ጥጃ ጨረቃ መውለዷም ከሰማይ ዝቅ ከምድር እና ከፍጥረታት ወገን ግን ከፍ ያለች ልጅ ናት የፀሐዩ ነገር ግን አልተገለጠልኝም አላቸው። እነርሱም ይህንኑ ሰምተው ሄዱ። ሄኤማንን ወለዱ። ሄኤሜን ዴርዴንን፣ ዴርዴን ቶናን፣ ቶና ሲካርን፣ ሲካር ሔርሜላን ወለደች። ሔርሜላና ማጣትም የጌታ አያቱ የምትሆን ሐናን ወለዱ።

ኢያቄም እና ሐና

ከነገሥታቱ ከይሁዳ ወገን የሚሆን ኢያቄም ቀለዮጳ የሚባል አንድ ባለጸጋ ሰው ነበር። እርሱም ከካህናቱ ከነገደ ሌዊ የምትወለደውን ሐናን አገባ። እነርሱም የተቀደሱ ደጋግ ነበሩ። በደቂቀ እሥራኤል ዘንድም አብዝተው መስዋዕትን ያቀርቡ ነበር።

ከእለታት አንድ ቀንም ከደቂቀ እሥራኤል ወገን የሆነ ሮቤል የተባለ ሰው መጣና " በእኛ ፊት መሥዋዕትን ታቀርብ ዘንድ አይገባም፤ በእሥራኤል መካከል ዘር የለህምና" አለው። አይሁድ እና ካህናቱም ልጅ ስለሌላቸው ይንቋቸው ይጠሏቸው፤ መሥዋዕታቸውንም ለመቀበል እምቢ ይሉ ነበር።

ኢያቄምም ፈጽሞ አዘነና ስእለቴን እስኪሰጠኝ ወደእኔና ወደሚስቴም እስኪያይ ድረስ አልመገብም አልጠጣምም ብሎ ሱባኤ ለመያዝ ወደ ገዳም /በረሓ ወጣ። ሰባቱ ሰማያት እንደመጋረጃ ተገልጠው ነጭ ወፍ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ በራእይ አየ።

ታላቁ የፋሲካ በዓል በደረሰ ጊዜ አንዲት የመንደሩ ሴት ወደሐና መጥታ ለምን ታዝኛለሽ? ራስሽንስ ለምን ትጎጃለሽ? በዓል ስለደረሰ መምህሬ የሰጠኝን ይህንን ልብስ ልበሺ ልብሱ የነገሥታት ልብስ ነውና አንቺ ትለብሽው ዘንድ ይገባሻል አለቻት።

ሐና ግን አዝና ነበርና ብቸኛ በመሆኔ፣ ልጅም ስለሌለኝ ኀዘንተኛ ነኝና ያማረ ልብስን አለብስም፤ ደግሞም ማን እንደሰጠሽ በምን አውቃለሁ? እኔንም ከኃጢአትሽ ልትጨምሪኝ ነውን? አለቻት። ሴቲቱም በምላሹ ተናዳ እግዚአብሔር ማኅጸንሽን በመዝጋቱ ደግ አድርጓል አለቻት።

ሐናም ከቀድሞው አብልጣ አዘነች። ፈጥና ተነስታም ወደቤተ መቅደስ ሔደች። አእዋፋትንም ከልጆቻቸው ጋር ባየች ጊዜ አንስሳት አራዊት ልጆች አላቸው፤ ምድር እንኳን ፍሬ አላት ለእኔ ግን ልጅ የለኝም፤ ለሁሉ ልጅ አለውና ለእነርሱ ልጅን የሰጠህ ወደእኔ ተመልከት ልጅንም ስጠኝ ብላ እያለቀሰች ትጠይቅ ነበር።

ቅድስት ሐና ሆይ እግዚአብሔርስ አንቺን ሳይመለከት ቀርቶ አይደለም። ከተናገረው ቀን ሳያጓድል ይመጣ ይወርድ ይወለድ ዘንድ ያለበትን ጊዜ እየጠበቀ ነበር እንጂ። እነሆም ቀኑ ደረሰ እግዚአብሔርም ወደአንቺ አየ ስእለትሽን ሰማ ልመናሽንም ተቀበለ ልጅንም ሰጠሽ፤ በአንቺም ዘንድ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም "ነጸረ አብ እምሰማይ ወኢረክበ ዘከማኪ" ያላትን ከፍጡራን መካከል አምሳያ የሚተካከል የሌላትን አንድያ እናቱን አገኘ።

ቅድስት ሐናም ነጭ ርግብ መጥታ በራሷ ላይ ተቀምጣ ከራሷ ላይም ወርዳ በጆሮዋ ገብታ በማሕፀኗ ስትተኛ በራእይ ተመለከተች። እነሆም በሐምሌ 30 ቀን የጌታ መልአክ (ቅዱስ ገብርኤል) ከሰማይ ወርዶ በፊቷ ቆመ፤ ጸሎትሽ ተሰምቷል ልምናሽንም ተቀብሏል ትፀንሻለሽ አላት። እርሷም ልጅን ከሰጠኝስ እስከ ዘመኑ ፍጻሜው ድረስ እንዲያገለግል ለእግዚአብሔር እሰጣለሁ አለች። መልአኩም ወደ ኢያቄምም ሔዶ ይህንን ብሥራቱን አበሠረው።ኢያቄምም ተደስቶ ሁለት በጎችንና 12 ላሞችን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።

አንድ ሱባዔ ይዘው ከቆዩ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ንጽሕት ብጽእት ድንግል ማርያምም ነሐሴ 7 ቀን በብሥራተ መልአከ በንጹሕ መኝታ ተጸነሰች። ስለ ጽንሰቷም የብሕንሳው ሊቀጳጳስ አባ ኅርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ላይ "ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ .... ድንግል ሆይ ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነሽ አይደለሽም በሕግ በንጹሕ መኝታ ከኢያቄምና ከሐና ተወለድሽ እንጂ... በማለት ንጹሕ ከሆነ አልጋ ንጹሕ ከሆነ መኝታ መገኘቷን ይናገራል። ጠቢቡ ሰሎሞንም.. ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ምንም ነውር የለብሽም።.. (መኃ 4፥7) ብሎ ከማኅጸን ጀምሮ ጥንተ አብሶ እንደሌለባት ያስረዳናል።#ተአምረ_ማርያም_እምማኅፀነ_ሐና