2023-05-19 14:24:22
እንኳን ለቅዱስ ቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሰን አደረሳችሁ።
#ቅዱስ_ያሬድ_ማነው?
የቅዳስ ያሬድ አባቱ አብድዩ / ይስሐቅ/ እናቱ ክርስቲና /ታውክልያ / ይባላሉ። በሌላም በኩል አባቱ እንበረም እናቱ ትውልያ ይባላሉ የሚል ታሪክም አለ፡፡ የትውልድ ሥፍራው አክሱም ነው፡፡
የተወለደው በ505 ዓ.ም/ ሚያዝያ 5 ቀን ሲሆን በተወለደ በ7 ዓመቱ ወላጅ አባቱ ስለሞተ እናቱ የአክሱም ጽዮን መምህር ለነበረው ለአጎቱ ለጌዴዎን እያስተማረ እንዲያሳድገው ሰጠችው፡፡ ከአባ ጌዴዎንም ዘንድ እየተማረ ለ25 ዓመት ተቀመጠ፡፡
ሆኖም ቃለ እግዚአብሔር የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለሆነ በጣም ያዝን ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከትምህርት ድክመቱ የተነሣ አጎቱ በጨንገር ቢገርፈው በዚህ ተበሳጭቶ ትምህርቱን ትቶ ሄደ፡፡ በመንገድም ሲጓዝ ውሎ በቀትር ደክሞት ከዛፍ ሥር ዐረፈ፡፡
በዚያ ጊዜ አንድ ትል ከዛፉ ላይ ያለውን ፍሬ ለመብላት ስድስት ጊዜ በመውደቅና በመነሣት ዛፉ ላይ ለመውጣት ሞክሮ በሰባተኛው ሰተት ብሎ ወጥቶ ሲበላ ተመለከተ፡፡ እርሱም በፈጸመው የብስጭት ተግባር በመጸጸት ተመልሶና አጎቱን ይቅርታ ጠይቆ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
አጎቱም ተደስቶ ዓይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ እያለቀሰ ፈጣሪውን ለመነለት፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለቅዱስ ያሬድ ዕውቀትን ገልጾለት መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ዐወቀ፡፡
ከዚያም በኋላ ወደ መምህሩ ተመልሶ ትምህርቱን ቀጠለና ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ አጠና፡፡ ሢመተ ዲቁናን ቀጥሎም ሢመተ ቅስናን ተቀበለ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግእዝ፣ እዝልና አራራይን ከሦስት ወፎች/መላእክት በወፎች ተመስለው/ መማሩን ሊቃውንት ይገልጣሉ፡፡
እነዚህ በወፍ የተመሰሉ መላእክት እየመሩት ወደ አርአያም አርጎ የ24ቱን ካህናተ ሰማይ ዜማ ከተማረ በኋላ ጠዋት በ3 ሰዓት በአክሱም ቤተ ክርስቲያን «ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሣረረ ወበዳግመ አረአዮ ለሙሴ ዘከመ ይግበር ግብራ ለደብተራ» ብሎ አዜመ፡፡
ይህን ዜማ የደረሰበት ወሩ ታኅሳስ ቀኑም ዕለተ ሰኞ ነው ይባላል፡፡ የቅዱስ ያሬድ የመጀመሪያ ዜማው «አርያም» በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ከመላእክት ወይም ከሰማይ የተገኘ መሆኑን ለማጠየቅ የተሰጠው ስም ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ ይህንን ዜማ በተመስጦ ሲያዜም ንጉሡ ፣ ንግሥቲቱ ፣ ጳጳሱ መኳንንቱና ካህናቱ ወደ አኩስም ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው መጥተው በአድናቆት ያዳምጡት ነበር፡፡ ምክንያቱም ገድለ ቅዱስ ያሬድ እንደሚገልጥልን ከዚያ በፊት በውርድ ንባብ ከሚደረግ ጸሎትና መንፈሳዊ አገልገሎት በቀር ይህን የመሰለ ዜማ አልነበረምና፡፡
የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ብሉይን ከሐዲስ ያስማማ ፣ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በሚገባ የያዘ ፣ እንዲሁም ለልዑል እግዚአብሔር ፣ ለእመቤታችን ፣ ለቅዱሳን መላእክት ፣ ለሰማዕታት ተገቢ የሆነውን ምስጋና የያዘ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለአራቱ የዓመቱ ወቅቶች እንዲስማማ አድርጎ ለበጋ፣ ለክረምት ፣ ለመጸውና ለጸደይ እንደሚሆን አድርጎ ከፋፍሏቸዋል፡፡
ለየበዓላቱም ተስማሚ ድርሰት መድቦላቸዋል፡፡ ይህንን ድርሰቱን በግእዝ ፣ በእዝልና በአራራይ ዜማ ያዘጋጀው ሲሆን ለነዚህም ስምንት የዜማ ምልክቶች ሠርቶላቸዋል፡፡
የቅዱስ ያሬድ ዜማ አንዴት ሁሉንም ይመስጥና ወደ አርያም በመንፈስ ይወስድ እንደ ነበር ለማስረዳት በገድሉም በሌሎችም መጻሕፍት የተመዘገቡ ታሪኮች አሉ፡፡ አንድ ቀን ንጉሥ ገብረመስቀል ፣ ንግሥቲቱ ፣ ጳጳሱ ፣ ካህናቱና ምእመናኑ በተሰባሰቡበት ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ሲያዜም ንጉሡ በመመሰጡ የተነሣ በመሰቀል ተሰላጢኑ ጫፍ የቅዱስ ያሬድን እግር ወጋው፡፡
ነገር ግን ማንም አላወቀም ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ መዝሙሩን ሲፈጽም ንጉሡ መስቀል ተሰላጢኑን ቢያነሳው የቅዱስ ያሬድ ደሙ ፈሰሰ፡፡ ንጉሡ በዚህ ደንግጦ ለዚህ ካሣ ይሆን ዘንድ የፈለግከውን ጠይቀኝ እሰጥሃለሁ ብሎ ቃል ገባለት፡፡ ቅዱስ ያሬድ ግን ከዚህ ዓለም ተለይቶ በምናኔ መኖርና መዝሙሩንም በሚገባ ማዘጋጀት እንደሚፈልግ ገለጠ፡፡
ምንም እንኳን አክሱምን ለቅቆ መውጣቱ ንጉሡን ቅር ቢያሰኘውም ቃሉን አንድ ጊዜ በመስጠቱ ምንም ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ቅዱስ ያሬድም ከዚህ በኋላ አኩስምን ለቅቆ ወደ ስሜን ተራራ ጸለምት መጓዙ ይነገራል፡፡
በጐንደር ፎገራ በሚባል ሥፍራ ቅዱስ ያሬድ ጣዕም ያለው ዜማውን ሲዘምር ተጠምደው የሚያርሱ በሬዎች ድምፁን እየሰሙ ገበሬውን ሥራ ስለ አስፈቱት በዚህ ተናዶ ቅዱስ ያሬድን በጅራፍ እንደ ገረፈው ይነገራል፡፡ ቦታውም « ወርቀ ደም እየተባለ እስከ ዛሬ ይጠራል፡፡ ወርቃማና ንጹሕ ደሙ የፈሰሰበት ማለት ነው፡፡
ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ያዘጋጀበት ዘመን ከ540-560 ዓ.ም ባለው ጊዜ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዜማውን ካዘጋጀ በኋላ 11 ዓመት አስተምሯል፡፡ በእርሱ ዘመን ተሰዓቱ ቅዱሳን በሃይማኖት ችግር ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው መጥተው ስለ ነበር ቅዱስ ያሬድ ከአንዱ ከአባ ጰንጠሌዎን የውጭውን ሀገር ቤተ ክርስቲያን ባሕልና ሥርዓት ይጠይቅ ነበር፡፡
በጆሮ የሰማውንም በዓይን ለማየት ሁለት ጊዜ ሮም የተባለችውን የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን ጐበኘሁ ይላል፡፡ «ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ለቤተ ክርስቲያን ርዒክዋ» እንዲል፡፡ የታሪክ ምሁሩ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ ለቁስጥንጥንያ ዜማ መነሻው ቅዱስ ያሬድ ነው ይላሉ፡፡
ለዚህም ማስረጃ የሚያደርጉት የቁስጥንጥንያን ዜማ የደረሰው ሊቅ ዜማውን አገኘው የሚባለው የቅድስት ሶፍያን ቤተ ክርስቲያን ሲዞር ከሰማው ዜማ ነው፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ከተነሣበትና ወደ ሮሜ ሄድኩ ካለበት ዘመን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እናም ምናልባት ያ ሰው ዜማውን የሰማው የቅድስት ሶፍያ ቤተ ክርስቲያንን እየዞረ ሲዘምር ከነበረው ከቅዱስ ያሬድ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡ Ancient and medival Ethiopian History/
ቅዱስ ያሬድ ማትያስና ዮሴፍ በተባሉ የአቡነ አረጋዊ ደቀ መዛሙርት መሪነት ወደ ደብረ ዳሞ ተራራ ላይ ወጥቶ ከጻድቁ ጋር በመገናኘትና የቤተ ክርስቲያኑን ሥራ እያደነቀ ዙሪያውን ከዞረ በኋላ «ዖድክዋ ወርኢኩ ሥነ ሕንፃሃ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን» ሲል ዘመረ፡፡ በዚያም ለአንድ ሳምንት ሰንብቶ ሄዷል፡፡
ቅዱስ ያሬድ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ጋር በመሆን በወሎ፣ በጎንደር፣ በሸዋ እና እስከ ጋሞጎፋ ብርብር ማርያም ድረስ በመሄድ አስተምሯል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የዐርባ ምንጭን ታሪክ ከቅዱስ ያሬድ፣ ከአቡነ አረጋዊ እና ከዐፄ ገብረ መስቀል ታሪክ ጋር ያያይዙታል፡፡
ሦስቱም ብርብር ማርያምን ለማየት ሄደው በነበረ ጊዜ በዛሬው ዐርባ ምንሥ አካባቢ ሠፍረው ነበር፡፡ በዚያ ቦታ ለወታደሩ የሚበቃ የሚጠጣ ውኃ በመጥፋቱ አቡነ አረጋዊ ጸልየው መሬቱን በመስቀል ቢመቱት ዐርባ ውሃዎች ፈለቁ ይባላል፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል የጣና ቂርቆስን ቤተ ክርስቲያንን በሚያሠራ ጊዜ በዚያ ቦታ ለሁለት ዓመት ተቀምጦ ድጓውን በማስተማሩ ምልክት የሌለው ድጓው እስከ ዛሬ በገዳሙ ይገኛል፡፡
35 views11:24