Get Mystery Box with random crypto!

#ግንቦት_1 #ልደታ_ለማርያም በግንቦት አንድ በዚህችም ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስ | ቤተ_ዜማ

#ግንቦት_1

#ልደታ_ለማርያም

በግንቦት አንድ በዚህችም ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኀነት የሆነባት ናት። ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ሐና ይባላሉ። ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ በዚያ ወራት የመካኖችን መብዓ ካህናቱ አይቅበሉም ነበርና።

እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር። ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ኀሳባቸውን ተመለከተ።

ክቡር እያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኀነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው።

በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች። ከዚህም በኋላ ይቺን የከበረች ሕፃን ፀንሳ ወለደች ስሟንም ማርያም ብላ ሰየመቻት ትርጓሜውም እመቤት ነው ደግሞም ሀብትና ስጦታ ማለት ነው።

በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ናት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት)