Get Mystery Box with random crypto!

#ስለማስመሰል_ርኅራኄው_ሰይጣንን_ተጠንቀቀው ,,,, የቀጠለ ሐ/ #ዓለማዊ_አስተሳሰቦችን_መ | 💠አምደ ሐይማኖት💠ዘ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ⛪️

#ስለማስመሰል_ርኅራኄው_ሰይጣንን_ተጠንቀቀው
,,,, የቀጠለ

ሐ/ #ዓለማዊ_አስተሳሰቦችን_መንፈሳዊ_በማስመሰል

በተለይ ዛሬ ላይ የዲያብሎስ ዋናው ማታለያው በመንፈሳዊነትና በዓለማዊነት መካከል ያለውን ድንበር በማጥፋት ለዓለማዊ አስተሳሰቦች መንፈሳዊ ሽፋን መስጠት ነው፡፡ በተደጋጋሚ የምንሰማቸው የድኅረ ዘመናዊነት፣ የባህል እና የሃይማኖት ብዝኃነት፣ የሉላዊነት እና የዓለማዊነት እይታዎች በግለሰቦች ነፃነት ስም ሃይማኖት የሰዎችን ነፃነት እንደሚገድብ አድርጎ በማቅረብና ሃይማኖተኛ መሆንን እንደጽንፈኛ አድርጎና አስመስሎ ያቀርባል፡፡ ሰዎችንም ሳያውቁት በእነዚህ አስተሳሰቦች ተጽዕኖ ከሃይማኖታቸው ወጥተው ሃይማኖት የለሽ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡

#ከዲያብሎስ_የማስመሰል_ርህራሔው_እንዴት እንጠንቀቅ?

ሀ #ሕሊናችንን_በመርመር

ዘወትር በሕሊናችን የሚመላለሱትን ሀሳቦች በጥንቃቄ ልንመረምራቸው፣ ወደ ውሳኔ ከመድረሳችንም አስቀድመን ‹‹ለምን?፣ እንዴት?፣ ከዚያስ?›› ብለን መጠየቅ ይጠበቅብናል፡፡ ባለን ዕውቀትም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኘው ትምህርት ጋር በማጣቀስ መረዳት መቻል አለብን፡፡ ‹‹የቀደመ የሕይወት ተሞክሮዬ ምን አስተምሮኛል?›› ብለንም ልንመረምረው ያስፈልጋል፡፡ ‹‹አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ እርሱ ነውና››፤ (ምሳ. ፬፥፳፫) ቅዱስ ጴጥሮስ በዲያብሎስ የማስመሰል ርኅራኄው ወጥመድ እንዳንያዝ በንቃት እንድንኖር ያስገነዝበናል፡፡ ‹‹በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› እንዲል፡፡ (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፰)

ለ #በትሕትና

ሰይጣን በማስመሰል ርኅራኄው በመቅረብ የበቃውንም ሰው በትዕቢት በከንቱ ውዳሴ ለመጣል የተንኮል ወጥመዱን ይዘረጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ›› (፩ቆሮ. ፲፥፲፪) እንዳለ ጠላት ቀርቦ በትዕቢት እንዳይጥለን ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ‹‹ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል›› ተብሎም ተጽፏልና፡፡ (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፭)

ሐ #በጸሎት_በመትጋት

ጸሎት ከዲያብሎስ የሚላኩብንን የጥፋት ፍላጻዎች ጋሻ ሆኖ የሚመክት መሣሪያችን ነው፡፡ ስለዚህ ዘወትር ሳናቋርጥ በጸሎታችን እግዚአብሔርን በማመስገን፣ ልዕልናውን፣ ቸርነቱንና አዳኝነቱን በማሰብ፣ በፍጹም ልባችን ሆነን ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ፤ ‹‹ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤›› (ማቴ. ፳፮፥፵፩) ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ስለሆነም የዲያብሎስን ፈተና ልንቋቋም ከምንችልባቸው መንፈሳውያት ኃይሎቻችን መካከል ጸሎት ዋነኛው መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል፡፡

መ #ሕዋሶቻችን_ከክፉ_ሥራ_በመጠበቅ

ዲያብሎስ እኛን ለማሳት የሚጠቀመው የገዛ ሕዋሶቻችን ነው፡፡ እነርሱን መቆጣጠር ከቻልን በዲያብሎስ የማስመሰል ርኅራኄ አንታለልም፡፡ ዓይናችን የሚያየውን ክፉና በጎ ነገር፣ ጆሮዋችን የሚሰማውን ሐሰትና እውነቱን ነገር መምረጥ ስንችል፣ አንደበታችን እውነትን ሲናገር፣ እግሮቻችን ወደተቀደሱ ሥፍራዎች ሲያዘወትር ዲያብሎስ በቀላሉ ቀርቦ አያስተንም፡፡ በአጠቃላይ ሕዋሶቻችን ከኃጢአት ሥራ ተለይተው በጎ ነገርን መሥራት ሲጀምሩ በጎን ከክፉ ስለምንለይ በዲያብሎስ የማስመሰል ርኅራኄው ወጥመድ በቀላሉ አንወድቀወም፡፡

ሠ #የእግዚአብሔርን_ዕቃ_ጦር_ሁሉ_በመልበስ

ክርስቲያን ዘወትር በንቃት በመዘጋጀት ሕይወቱን ይመራል እንጂ በዘፈቀደ አይመራም፡፡ ‹‹ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን›› (ሉቃ.፲፪፥፴፭) ተብሎ በወንጌል እንደተጻፈው፤ ቅዱስ ጳውሎስ የዲያብሎስን ውጊያዎች በድል አድራጊነት ለመወጣት ምን ማድረግ እንዳለብን ሲያጠይቅ ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ›› ብሎናል፡፡ (ኤፌ ፮፥፲፩) የጦር ዕቃ የተባሉትን ጾም ጸሎትና መንፈሳዊ ተጋድሎን ጋሻና ጦር አድርገን ከዲያብሎስ የማስመሰል ርኅራኄው ወጥመድ ማምለጥ ይቻላል፡፡

ረ #በረድኤተ_እግዚአብሔር_በማመን

ዲያብሎስ በማስመሰል ርኅራኄው ለፈተና ወደ በሕይወታቸን ሲመጣ ‹‹ለምን ወይም እንዴት›› አንበል፤ ይልቅስ በእግዚአብሔር ረድኤት ማመን ይገባናል፤ እግዚአብሔር ማንንም በክፉ አይፈትንምና፡፡ ‹‹ማንም ሲፈተን በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና››፡፡ (ያዕ. ፩፥፲፫) ይልቅስ እንኳን እኛ ጌታችንም ተፈትኗል፤ ‹‹እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና›› (ዕብ. ፪፥፲፰) ተብሎ የተጻፈልን በፈተናችን ሁሉ መጽናኛ ይሆነን ዘንድ ነው፡፡ ስንፈተን ልንጨነቅ አይገባም፤ ጌታችንም ተፈትኗልና፤ ድል አድርጎም ድል የምናደርግበትን ኃይል ሰጥቶናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› (ፊል. ፬፥፲፫) ብሎ እንዳስተማረን ኃይልን የሚሰጠን አምላክ እንዳለ አምነን ዲያብሎስ በማስመሰል ርኅራኄው የሚያመጣብንን ሥውር ፈተናን በማለፍ ድል ማድረግ እንችላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፤ ከ‹‹መንፈሳዊ ውጊያዎች›› ፪ኛ መጽሐፍ፤ በብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ