Get Mystery Box with random crypto!

✢✢✢ በተረጋጋ መንፈስ፤ በንጹሕ አእምሮ ስለቅዱሳን ማሰብ ስንጀምር ወንጌል ምን ማለት እንደሆነ እ | 💠አምደ ሐይማኖት💠ዘ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ⛪️

✢✢✢
በተረጋጋ መንፈስ፤ በንጹሕ አእምሮ ስለቅዱሳን ማሰብ ስንጀምር ወንጌል ምን ማለት እንደሆነ እንገነዘባለን። ቅዱሳን ወንጌልን በጸሎታቸውም በሕይወታቸውም ያለማቋረጥ ይደግሙታል። ሐዋርያት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተምረው ክርስቶስን እንደመሰሉ በእግረ ሐዋርያት የተተኩም ቅዱሳን ከሐዋርያት ተምረው ሐዋርያትን መሰሉ።
"እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ"እንዳለ 1ኛቆሮ 11÷1።

ሐዋርያት ዓለምን ዞረው እንዳስተማሩ እነሱም ይህንን አደረጉ። በዐቢይ ተጋድሎ ተጠመዱ በመጋዝ ተተረተሩ፣ በመስቀል ተሰቀሉ፣ በሰይፍ ተቆረጡ፣ እንደበግ ታረዱ፣ እንደ ሽንኩርት ተቀረደዱ እንደ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንጽሕና ኑረው በሐሰት ተከሰው በጭካኔ ተገድለዋል። እንደ አምላካችን ክርስቶስም ይነሣሉ።
"ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን" እንዲል ሮሜ 6÷5።

እርሱ ያከበራቸውን ማንም አያዋርዳቸውምና ፤ጆሮቹም ሁልጊዜ ወደእነርሱ ነውና ቅዱሳንን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን እንዲለምኑልን እንለምናቸዋለን። ስለእነሱም ብሎ ይቅር እንዲለን
በእንተ እግዝእትነ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ
በእንተ መላእክት መሐረነ ክርስቶስ
በእንተ ቅዱሳን መሐረነ ክርስቶስ እንለዋለን።
ሰው በወዳጁ ሲማጸኑት ልቡ እንዲራራ አምላካችን እግዚአብሔርም ስለወዳጆቹ ራርቶ ይቅር ይለናል። እንጂማ እኛ እንኳን ጸሎታችን ኃይል ኖሮት(በንጹሕ ሕሊና ፣በአንቃዕድዎ ልቡና፣ በጽኑዕ ፍቅር አንጸልይምና )ሊሰማ በቅጡ መች እንጸልያለን።

እግዚአብሔር ያከበራችሁ ቅዱሳን ሆይ እግዚአብሔር ራሱ እንዳከበራችሁ መጠን ምስጋና ይድረሳችሁ።

እኛ ደካሞች በኃጢአት ሀሳብ፣በኃጢአት ንግግር፣በኃጢአት ተግባር የዛልን ነንና ረዳትነታችሁ ከእኛ አይለየን።

አሜን

ዲ/ን ሳሙኤል በላቸው