Get Mystery Box with random crypto!

'ናፊባ' ክፍል ~ ሠማንያ ሥምንት በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888 'እነዚህን ሰነዶች በጥንቃቄ | የዮቶር ልጅ - አምባዬ ጌታነህ

"ናፊባ"
ክፍል ~ ሠማንያ ሥምንት
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"እነዚህን ሰነዶች በጥንቃቄ እንያዝና ለማምለጥ የተቻለንን እናድርግ!"አለ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው "አይ ኢንስፔክተር በዚህ ስዐትም ስለዚህ መረጃ ታስባለህ? መጀመሪያ የእኛ መኖርና አለመኖር በምን ተረጋገጠና"አለ ተሕሚድ በሸዋንግዛው ንግግር እንደመሳቅ እያለ " እዚህ ላይ አንድ ነገር ዘንገት ብለሀል። የሰው ልጅ የሚሞተው ተስፋ ማድረግ ሲያቆም ነው። ተስፋ ብቸኛ የሕይወታችን ማስቀጠያ መንገዳችን ነው። እኔ በዚህ ሁኔታ እንኳ ሆኜ የማስበው ስለቀጣይ እጣፈንታችን ነው። በሕይወት እስካለሁ ድረስ ፕላን ማድረጌን እቀጥላለሁ። ማድረግ ያለብኝን ነገር ሁሉ እያደረኩ እቀጥላለሁ። አንድ አባት አትክልት እየኮተኮቱ ድንገት የሞት መላዕክት ይመጡና "ለመሞት ሶስት ስአት ነው የቀረዎት ቢባሉ ምን ያደርጋሉ?" ብሎ ሲጠይቃቸው እሳቸውም ፈገግ ብለው "ኩትኮታዬን እቀጥላለሁ"አሉ ይባላል።እስከመጨረሻዋ የእንባ ጠብታ መዋደቅ ያስፈልጋል። በሕይወት እስካለሁ።የነዛን ምስኪን ዜጎች ገዳይ ለፍርድ ማቅረብና የወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንባ ማበስ ቀዳሚው ስራዬ ሆኖ ይቀጥላል! ስለዚህ አንተም እንደዛ ሆነህ የተነሳህበትን አላማ ለማሳካት መጣር አለብህ። ለአላማህ አንተ እንጅ የምትሞተው አላማህ ለአንተ አይሞትም" አለና የሚያስፈልጉትን መረጃዎች መሰብሰቡን ቀጠለ። ተሕሚድ ሸዋንግዛው የተናገረው ሜታፎርና ታሪክ ውስጡ ላይ እንደ አለት ድንጋይ የተቀመጠ ይመስላል።አንዳንዶቻችን የሆነ ነገር ሲጋረጥብን ቢቀርስ ሌላ ነገር ብንፈጥርስ ብለን የምናቆመው ነገር አለ። የምንሰራው ስራና ራዕያችን ከተዛመደ እንቅፋቶች ይበዙብናል።ብዙ ጊዜ ሞቲቬሽናል ስፒከሮች ስለ ስኬት ሲያነሱ ቀዳሚ ምሳሌያቸው የሚሆነው ቶማስ ኤዲሰን ነው። ይህ ሰው እንግዲህ የአለማችንን ገፅታ በብርሃን አጎናፅፎ የራሱን ታሪክ የቀለበሰ ነው። ስለዚህ ሰው ስኬት ማውራቱ አይጠቅምም የሚጠቅመው ስኬት ላይ የደረሰበትን ስቃይ መከራና መገለልን በመማር የራስን ስኬት መስራት በመቻል ነው። ስልክ ያለቻርጅ አይሰራም ቻርጅ የሚደረገው ደግሞ ከመብራት በሚሰበሰብ ሀይል ነው። አጠቃላይ ግዙፍ የሚባሉ ፋብሪካዎች ምኖች በመብራት ላይ ጥገኞች ናቸው ማለት ነው። ቶማስ ኤዲሰን ሁሉም ደደብ ተማሪ ብለው አንቅረው የተፉት ነገር ግን እናቱ ያን አስተያየታቸውን ለልጇ በበጎ ነገር በመቀየር ለአሁኗ አለም ነፀብራቅን አብቅተዋል። አሁን ሀሳቤ የቶማስን የሕይወት ታሪክ መተንተን አይደለም።መብራትን ለመፍጠር አንድ ሺህ ጊዜ ተሳስቷል።ብዙዎችም ለምን አርፈህ አትቀመጥም።አይሆንም አይሳካም ይህ በአንተ አቅም የሚሆን አይደለም ብለውታል።ነገር ግን ቶማስ ሙከራውን አላቆመም።ሙከራህን ቀጠለ ምንም አይነት ተስፋ በማያሰጥበት ሁኔታ ላይ ብትሆንም የየዝከውን ነገር አትልቀቅ። ቃልኪዳን ትልቅ ማሰሪያ ገመድ ነው። ቶማስ ከአንድ ሺህ ሙከራዎቹ የተማረው ነገር ቢኖር መብራት የማይሰሩበትን መንገድ ነው። ስለዚህ በማንኛውም ቦታና ሁኔታ ሆነህ አላማህን ለማሳካት ጣር።
ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ድምፅ ይሰማ ጀመር። "በቃ ተጀመረ ማለት ነው።"አለ ተሕሚድ "ግን ከማን ጋር ነው የሚታኮሱት? ከተማ ላይስ ተኩስ መክፈት አግባብ ነዎይ?ይሄ እኮ ትልቅ የጦር ወንጀል ነው! ሌሎች እኔን የሚፈልጉኝ ሰዎችም አሉ ማለት ነው?"በርካታ ጥያቄዎችን ለተሕሚድ እየጠየቀ ግራ መጋባቱን ቀጠለ። "ምንአልባት ኮማንደር በርናባስ ይሆን እንዴ? ለማለፍ ሞክሮ እምቢ ሲሉት ይሆን?"አለ ተሕሚድ"ምን አልባት ልክ ልትሆን ትችላለህ ግምትህ ልክ መሆንና አለመሆኑን ልደውልለትና ቸክ እናድርግ" ብሎ ወደ በርናባስ ስልክ ደወለ።
በርናባስ ምንም አይነት ሀይል ይዞ እንዳልመጣና እሱን ለማድረግ ታማኝ ሰዎችን እያፈላለኩ ነው በማለት መፅናኛ ቃላት ሰጥቶት ወሪያቸውን ጨረሱ። ተሕሚድ የገመተው ግምት ልክ ባለመሆኑ እንደማፈር እያለ "ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል?" ይሄኔ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው አንድ ሀሳብ ወደ ምናቡ መጣለት። እንደተከበበ ለነገረው ሰው መደወል። "እየውልህ ማንነትህን አላውቅም።ከእኔ ምን እንደምትፈልግ አላውቅም።ለምን ያን ሁሉ ምስጢርም ስታስቀምጥልኝ እንደነበር አላውቅም። አሁንም ለምን እንደምትረዳኝ አላውቅም። ኢላማህ እኔ ልሁን አልሁንም አላውቅም።ግን አሁን ቢያንስ ልትጎዳኝ እንደማትፈልግ ተረድቻለሁ።ስለዚህ አንድ ነገር ብቻ ላስቸግርህ እኔ አንድ ነገር ብሆን ልጆቼን ለሚስቴ አደራ አስረክብልኝ። ይሄን ብቻ እንድትተባበረኝ ነው የምፈልገው!" አለ ሸዋንግዛው የመጨረሻ ንዝ በሚመስል አነጋገር "ኢንስፔክተር ምንም ችግር አይፈጠርም ተኩሱን የከፈቱት የእኔ ሰዎች ናቸው። ዋናው አላማችን አንተን ከመንግስት አፋኝነት ነፃ ማውጣት ነው። ስለዚህ አሁን እንደደረሰኝ መረጃ የበርህን አካባቢ የእኛ ሰዎች ተቆጣጥረውታል ስለዚህ ሌላ ሀይል ሳይመጣ በፍጥነት ከዛ አካባቢ እንድትወጡ ተዘጋጁ"አለ ሸዋንግዛውን ለረጅም ደቂቃ ካዳመጠው በኋላ። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውጰበሰውዬው አነጋገርና ፍፁም የሆነ እርጋታ እየተገረመ የሚለውን ከመተግበር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ተረድቷል።
*****
" ልጆች ናቸው። እንዳይፈሩ ጥንቃቄ አድርጉ። ሲሀምንም ያለውን እውነት በመናገር እሷንም ከስጋት ነፃ እንድታደርጓት እፈልጋለሁ።የተወሰኑ አባላቶቻችንን ወደ ስፍራው በመላክም በአፋጣኝ እነ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን ወደዚህ የማምጣት ስራ መሠራት አለበት ሌላውን ስራ በሙሉ ተውትና አሁን ትኩረታችን ወደዚህ ነው መሆን ያለበት።የሸዋንግዛው መኖር ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነው ጠቃሚ ነው። አብዝሀኛውን ስራችንን የሚሰራልን እሱ መሆኑን እንዳትረሱ"በማለት ኮስተር ብሎ አዘዘ። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ለተሕሚድ ሙሉ ሽፋን በመስጠት የተወሰኑ ለምርመራ ይጠቅሙኛል ያላቸውን መረጃዎችና ላፕቶፕ ይዞ በመውጣት በተነገረው መሠረት በሩን ሲከፍት በርካታ ሲቢል ሰዎች ቆመዋል። ከዛ በቅርብ እርቀት ደግሞ የተኩስ ድምፅ ይሰማል።አካባቢው ሰላሙ ተረብሿል።በፍጥነት መሀል ላይ አስቀምጠዋቸው ይዘዋቸው ከአካባቢው ተሰወሩ። ሸዋንግዘው ወደየት እንደሚሄድም ማን እንደሚወስደውም ሳያውቅ ያለምንም ተቃርኖ ታግቶ ይሄድ ጀመር። በመጨረሻ በአንድ ቅንጡ ቪላ ቤት ውስጥ ገብተው የቤቱ ወለል ላይ የተነጠፈውን አረኔጓዴ ስጋጃ በመክፈት ጥቂት ቁጥሮችን በመጫን በሩ ተንሸራተተ። ጥቁር ሲሊንደር የሚመስል የሚያብረቀርቅ ነገር ላይ ሶስታቸው ከቆሙ በኋላ እነሱ ጋር ያልቆመው ልጅ ከቆሙባት አጠገብ የሆነች የአረንጓዴ በትን ሲጫን በእርጋት ይዟቸው ወደታች ይሰምጥ ጀመር።ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውና ተሕሚድ እርሰበእርስ ተያዩ። ወደታች በወረዱ ቁጥር በጨለማ የተዋጠው ክፍላቸው በብርሃን እየተተካ በግምት ወደሶስት ደቂቃ የሚሆን ጉዞ ከጨረሱ በኋላ የቆሙበት ሊፍት ደወል ሲያሰማ በፍጥነት እግራቸውን እንዲያወርዱ ካሳወቃቸው በኋላ ቀጥታ ተከተሉኝ በማለት ወደ አንድ ክፍል ይዟቸው ይሄድ ጀመር። ግራ ቀኝ ያሉት መብራቶች የምድሩን አለም የሰማይ ከዋክብት አስመስለው በብርሃን አንቆጥቁጠውታል። "ምንድን ነው የማየው? አለ ተሕሚድ።

@amba88
@amba88