2022-07-07 14:57:43
‹‹ታዩት›› የሚል ከሌለ ፍዳችንን እናያለን!
(አሌክስ አብርሃም)
በትውልድ ኢራናው የሆነ ቦስተን ዩኒቨርስቲ የሚያስተምር Nassir Ghaemi የሚባል የሳይካትሪስት ፕሮፌሰር አለ! በተለይ በአዕምሮ ህመምና ኪያል (ኪያል ያልኩት mood disorders የሚሉትን ነው! ወሎ አካባቢ አንድ ሰው ባህሪው ከኖርማሉ በተለያየ ምክንያት ወጣ ሲል… በስጨት ሲል ሙዱ ሲቀየር ከየል አለበት ይባላል እንደዛ ነው) እና ፕሮፌሰሩ ብዙ ፅሁፎች ፅፏል! በርካታ መፅሐፎችም አሉት ! ታዲያ የሆነ ጊዜ
Uncovering the Links Between Leadership and Mental Illness በሚል ርእስ የፃፈው መፅሐፍ አነጋጋሪ ሁኖ ነበር፡፡ እንደውም በኒዎርክ ታይምስ ቤስት ሴለር የተባለለት መፅሐፍም ነው፡፡ እንደሱ አባባል ከሆነ ከታላቁ የአሜሪካ ፕሬዝደንት አብርሃም ሊንከን ጀምሮ እስከታላቁ የጥቁሮች መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ፣ ባህር ተሻግሮ ከህንዱ ጋንዲ እስከእንግሊዙ ዊንሰተን ቸርቼር ዝቅ ሲል ከአዕምሮ ጤና ጋር የተያያዘ ከባድ ድብርት፣ ከፍ ሲል የለየለት የአዕምሮ ህመም በየጊዜው አጋጥሟቸው ነበር፡፡ ግን አለ …የአዕምሮ ህመም ሁልጊዜ መጥፎ አይደለም፣ አንዳንዴ የአእምሮ ህመም ለተሻለ አመራር ለታላላቅ ውሳኔዎች ይረዳል …በሌላ አባባል ወፈፍ የሚያደርገው አእምሮ አንዳንዴ ከጤነኛውም በላይ አሪፍ ውሳኔ ሊወስን ይችላል እንደማለት ነው፤ የአገሬ ተራች ‹‹የቸገረው ርጉዝ ያገባል›› እንዲል መሪህ ወፈፍ ቢያደርገው ‹‹ለበጎ ነው›› ብሎ ማለፍም ተለማመድ ጎን ለጎንም ዋ ለራሴ እያልክ እንዳይብስበት ፀልይ እንደማለት!
ነገሩ ቀልድ አይደለም ጓዶች ! ይሄ ሁሉ በሁለት እጅ የማይነሳ መኳንነትና መሳፍንት ለምን ወፈፈ ብለህ ከጠየክ ሰው ናቸዋ አንተ አንዲት ሴት አፈቀርኩ ብለህ ገጀራ ከመዘዝክ እነሱ ነካ ሲያደርጋቸው የኒውክሌር ቁልፍ ቢጫኑስ …ሰው ባለው ነው የሚወፍፈው! እነዚህ ታላለቅ ሰዎች አንድም በስራ ጫና ረፍት እንቅልፍ ከማጣት ፣ ሁለትም መሪዎቹ ከቀደመ መንፈሳዊም ይሁን ዓለማዊ እምነታቸው ጋር የሚጋጭ ውሳኔ ጋር ሲፋጠጡ ከሚያድርባቸው ከፍተኛ ጭንቀት ሊመነጭ ይችላል፡፡ ዝንብ ገሎ የማያውቅ ሰው በሚመራት አገር የሽዎች ደም ሲጎርፍ መወፈፍ ይነሰው! ሌላው ምክንያት ደግሞ አቅምና ሐላፊነት አለመጣጠን የሚያመጣው ጣጣ ነው፡፡ የሆነ ሁኖ መሪዎች መሪ ሆኑ ማለት ህመምም ጭንቀትም የማይነካካቸው ‹ሱፐር ናቹራል› ፍጥረቶች አይደሉምና ‹‹በአካልም በአዕምሮም ወጣ ያለ ነገር ሲታይባቸው የቅርብ ዘመድ ወዳጅ ‹እስቲ ታዩት› ማለት አለበት፡፡
እንግዲህ በዚሁ መፅሐፍ እንደተጠቀሰው አንዳንድ መሪዎች (መሪ ስላችሁ የአገር ብቻ ላይሆን ይችላል) አእምሯቸው ወሰድ ሲያደርገው ልብሳቸውን ጥለው ድንጋይ አይወረውሩም ...የሚታይባቸው ምልክት ወይም የአዕምሮ ህመሙ አይነት positive illusion የሚባለው ዓይነት ነው ይለናል ፀሐፊው! ይሄን ሰርቸው ነው ፣ያንን አድርጌው ነው ፣…እንደኔ ታታሪ የለም ነው …እንደኔ አገር ታላቅ የትም የለም ነው…በአመራሬ አለም ተደነቀ ነው ፣ ሰዎች ቀኑብን ነው፣ …አገራት በእድገታችን ጉድ አሉ ነው …ታሪክ ላስተምራችሁ ነው …ጅኦግራፊ ከኔ ወዲያ ነው …የጦር ጥበብ ጥርሴን የሸረፍኩበት ነው ነው …ኢኮኖሚክስ ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ነው ነው …በቃ!
አፍንጫቸው ስር የሚፈጠረው ዓለም የሚያየው የብቃት ማነስም ሆነ የህዝብ ችግርና መከራ አይታያቸውም …ከታያቸውም ችግሩን የፈጠረው ሌላ አካል ነው ! መነፅራቸው ደግ ደጉን ብቻ ያሳያቸዋል ፣ጆሯቸውም ካለምስጋና አይሰማም! በዛ ላይ አድር ባይ አማካሪ ከከበባቸው ቻው ! መጀመሪያ እውነተኛ ችግራቸውን ስትነግራቸው አይሰሙህም፣ ጨለምተኛ በጎ ስራቸው የማይታይህ ነህ ! እምቢ ስሙኝ ብለህ ችግራቸውን ከነገርካቸው ግን የስልጣን ይሁን የቁጣ ሰይፋቸውን ይመዙታል …ያኔ አንተን አያድርገኝ!
ጥሎብኝ ስፅፍ ቀልድ ስለሚመስልብኝ እንጅ ይሄ ባህሪ በወጉ መስመር ካልያዘ እጅግ ዘግናኝ ወደሆነ ውሳኔ ሊደርስም ይችላል፡፡ ብዙ የአሜሪካ የአፍሪካ የመካከለኛው ምስራቅና የአውሮ መሪዎች ላይ ጭምር ተከስቶ ዘግናኝ እልቂት የፈጠረ አገርንም ህዝብም ጉድ የሰራ ‹‹ህመም›› ነው፡፡ እደግመዋለሁ ባህሪ አይደለም ‹‹ህመም›› ነው! የቁጣቸው ክፋት ደግሞ አጨበጨብክም አላጨበጨብክም ሁሉንም አይምሩም !! የቅርብ የለ የሩቅ ሰደድ እሳት በለው! ሳጠቃልለው.... ምንም እንኳን በግሌ የሙያው ባለቤት ባልሆንም (የሙያው ባለቤቶች የበለጠ እንደሚያብራሩልን በማመን) ጠ/ሚንስትራችን በርካታ በጎ ነገሮች እየሰሩ ነው ….ግን በተለይ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው ላይ ያየሁባቸው ባህሪ positive illusion ነው …ለስለስ ላድረገው እንደፀሐፊው mild posetive illusion! ይሄን ነገር ‹‹ታዩት›› ካላልን እንደ አገር ፍዳችንን ልናይ እንችላለን! ክቡር ጠ/ሚንስትር ከተቀየሙብኝም ይቀየሙብኝ እንጅ እንደአንድ አገሩን የሚወድ ዜጋ የምለው ‹‹ይሄን ነገር በጊዜ ታዩት›› ነው!
#Share
#AlexAbreham
JOIN
@AlexAbreham
2.9K viewsedited 11:57