Get Mystery Box with random crypto!

ክርክር ለማን በጀ ? በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ =>ቅድስት ቤተ ክ | 💠 ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው።

ክርክር ለማን በጀ ?

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እኛ #ልጆቿ በሁሉ ጎዳና ዝግጁ እንድንሆን ትፈልጋለች::
በሃይማኖት በምግባር
በጾም በጸሎት
በፍቅር በደግነት
በትህትና በትእግስት . . . ሁሉ ምሉዓን እንድንሆን ፈቃዷ ነው::

+በተረፈውም በቃለ እግዚአብሔር እንድንበረታና ለሚጠይቁን ተገቢውን ምላሽ የምንሰጥ እንድንሆንም ትመክረናለች:: (1ዼጥ3:15) ዛሬ ዛሬ ግን ብዙዎቻችን በጐ ምግባራትን ዘንግተን በመሰለን ጎዳና እንሔዳለን::

+በተለይ በዚህ የፌስ-ቡክ ገጽ ላይ ብዙ ነገሮችን (ያልተገቡትን ማለቴ ነው) ከክርስቲያኖች መመልከቱ ከመለመድ አልፎ አሰልቺ እየሆነ የመጣ ይመስላል::

እስኪ እነዚህን ጥያቄዎች ልብ በሏቸውና መልሱን ለራሳችሁ ስጡ:-

1.የፌስ ቡክ Account ለመክፈት ለምን አስፈለገን?

2.አሁን በየገጻችን ምን እየሰራን ነው?

3.በየጊዜው የምንጽፋቸውና የምንለጥፋቸው ነገሮች አላማቸው ምንድን ነው?

4.ፌስ ቡክ ውስጥ በመኖራችን ምን አተረፍን? ምንስ አጎደልን?

5.ፌስ ቡክ ይዘጋ (ይቅር) ቢባል ምን ይሰማናል?

6.በዚህ ገጽ ላይ እስከ መቼ ልንቀጥል አስበናል?

7.መጨረሻችን ምንድን ነው?

እስኪ እርሶ! እነዚህን ጥያቄዎች ለራስዎ ይመልሱና ራስዎን ይመርምሩ:: እኔ ግን በዚህ የማኅበረ-ሰብእ መገናኛ ገጽ ላይ ከተመለከትኩአቸውና መታረም ካለባቸው ነገሮች አንዱን ላንሳ::

(ከዓመታት በፊት የነበረው ችግር እጅጉን ገኖ፡ ከፍቶም በማየቴ ነው ጉዳዩን ዳግም ያነሳሁት)

☞ ብዙዎቻችን: በተለይ ሃይማኖትንና ሀገርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ክርክር ውስጥ ገብተናል::

+በተለይ ደግሞ በተለያየ ጊዜ ማን እንደከፈታቸው እንኩዋ ባልተረዳናቸው ቡድኖች (Groups) ከኢ-አማንያን ጋር ከመከራከር አልፎ መዘላለፍ ዘወትራዊ ሥራ ሆኗል:: አስቸጋሪው ነገር ደግሞ ወደ ቡድኖቹ ማን እንደ ጨመረን አናውቅም::

+የከፋው ግን #የፈጣሪያችን: #የእመቤታችንና #የቅዱሳኑ ስም በክፉና በከንቱ ይነሳል:: ሀገርም ትሰደባለች፡፡ ትናንታችን ይንቋሸሻል፡፡ አበውም ይዘለፋሉ፡፡ ምናልባት "በእነዚህ የቡድን ገጾች የሚለጠፈው ነገር አስተማሪ ነው:: ቡድኖችም የተመሠረቱት ለበጎ ውይይት ነው" ትሉኝ ይሆናል::

☞እንደምትሉት ቢሆንማ ሸጋ ነበር:: ግን አልሆነም::

+ቀላል ቁጥር የሌላቸው ባልንጀሮቻችን ከክርክር አልፈው ጸብ የሚመስል ነገር ውስጥ በመግባታቸው ከክርስቲያን በማይጠበቅ መንገድ ሌሎች እምነቶችን፡ አንዳንዴም ጎሳን ጨምረው ሲዘልፉ እያየን ነው::

☞ ወንጌልን በዚህ መንገድ (በክርክር: ሲከፋም በብሽሽቅ) የምናስፋፋ የመሰለን ሰዎች ካለን ተሳስተናል:: እንዲያውም በነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እየቀለልን ይመስላል::

+ሲጀመር #ክርስትና የክርክር ሃይማኖት አይደለም:: ሲቀጥል ጥራዝ ነጠቅ የሆነ እውቀት ይዞ እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ መግባቱ እጅጉን አደገኛ ነው:: ምክንያቱም ብዙዎቻችን የክርስትናን ስሙን ይዘናል እንጂ ጣዕሙ የገባን፡ ምስጢሩንም ያጣጣምን አይደለንም::

+እንዲያውም ፌስቡክ፡ ቴሌግራምና፡ ዋትሳፕ ላይ ባነበባትና ባደመጣት ትምህርት ራሱን እንደ አዋቂ ቆጥሮ የተማሩ ሰዎችን እንኳ የሚዘረጥጥ ሰው መመልከቱ አሁን አሁን ብርቅ አይደለም፡፡

+በዚያ ላይ አስፈላጊ ለሆኑ ጥያቄዎች በጊዜው መልስ ከመስጠት በቀር (ይሔውም በመምህራን ነው) እንድንከራከርም ሆነ መሰል ድርጊቶች ላይ እንድንሳተፍ እናት ቤተ ክርስቲያን ፈቃዷ አይደለም::

ምንተ ንግበር (ምን እናድርግ?) (ሐዋ. 2:37)

1.በልኩ እንማር!

=>እንኩዋን ለሌላ ለማስረዳት: ለራስ ለመዳንም በልኩ መማር ያስፈልጋል:: ጥቂት ነገርን ብቻ ይዞ የፌስ-ቡክ አርበኛ ለመሆን መሞከሩ አይረባንምና እንማር::

+ለዚህ ደግሞ ተመራጩ መንገድ . . . ከአበው: ከመምሕራን: ከጉባኤያት ተገኝቶ ከምንጩ መጠጣት ይገባል:: እድሉ የሌለን: በሰው ሃገር ያለን ደግሞ ከመልካም ድረ ገጾች አስፈላጊውን ትምህርት በጥሞና እንውሰድ::

+ያልገባን ነገር ካለም ማኅበረ ቅዱሳንን ለመሰሉ አገልጋዮች ልከን ማብራሪያዎችን ማግኘት እንችላለን::

2. ዓላማ ይኑረን!

=>የምናደርገው እያንዳንዱ ነገር ሁሉ እኛን ጠቅሞ ለሌሎቹ እንደሚተርፍ ካላመንበት ይቅር:: መጻፋችንም: መለጠፋችንም ለዓላማ ይሁን::

3.የከንፈር ምስክርነት ይብቃን!

=>ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ያጣችው በከንፈሩ የሚደልላት አይደለም:: ክርስትና የገባው: ሕይወተ አበውን የሚኖር ምዕመን ያስፈልጋል:: ስለ ተናገርን: ወይ ስለጻፍን መሰከርን ማለት አይደለም::

መመስከር ማለት እንዲህ ነው:-
ሀ..በሕይወት (አብነት በመሆን)
ለ..በአንደበት (ፊት ለፊት ሔዶ ዋጋ በመክፈል)
ሐ..በጽሑፍ (ይህ ግን ጾምና ጸሎት ትሩፋትም ካልተጨመረበት ፍሬ አይኖረውም)

4.በፍቅር ማስረዳት!

=>አንድን ኢ-አማኒ እምነቱን ስለ ሰደብክ አትመልሰውም:: የሚፈለገው በፍቅር: በማስተዋልና በጥልቀት ማስረዳቱ ነው:: ስብከት በፍቅር እንጂ በእልክ አይሆንምና:: (አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለመገሰጽና የተሳሳተ መንገዳቸውን ለመግለጥ ጊዜ ምረጥ)

+ስለ ሃይማኖታችን የማይገባ ነገር ሲባልም ከቻልን በማስተዋል መመለስ: ካልሆነልን ነገሩን ከመምህራን ማድረስ ይገባል:: ዓላማችን የእኛና የሰው ሁሉ መዳን ከሆነ የእኛን መሻት ትተን የጌታን ፈቃድ ልንከተል ግድ ይለናል::

+ክርስትና ጠላትንም የመውደድ ጥልቅ ምስጢር አለውና ኢ-አማንያንን "ንስጥሮስ ሆይ! አንተን እወድሃለሁ:: ትምህርትህን ግን እጠላዋለሁ" ብለን እንደ ታላቁ ሊቅ #ቅዱስ_ቄርሎስ ልንናገር ይገባል::

ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍም እንዲህ ይላል:-

" " ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ: ብትበላሉ: እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ::
ነገር ግን እላለሁ:: በመንፈስ ተመላለሱ:: የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ . . .

የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው:: እርሱም ዝሙት: ርኩሰት: መዳራት: ጣዖትን ማምለክ: ሟርት: ጥል: #ክርክር: ቅንዓት: ቁጣ: አድመኝነት: መለያየት: መናፍቅነት: ምቀኝነት: መግደል: ስካር: ዘፋኝነት: ይህንም የሚመስል ነው::
አስቀድሜ እንዳልሁ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም:: " " (ገላ. 5:15-21)

" " አንዳንንድ ተከራካሪዎችንም ውቀሱ:: " " (ይሁዳ. 1:22)

=>ለዚህ ደግሞ #የሥላሴ ቸርነት: የድንግል #እመ_ብርሃን አማላጅነት: #የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን::

ስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል!
ወለወላዲቱ ድንግል!
ወለመስቀሉ ክቡር፡ ዕጸ ሣሕል!
አሜን!

https://t.me/zikirekdusn