Get Mystery Box with random crypto!

አሁንም ' ሳይቃጠል በቅጠል!' እላለሁ! ተከታዩ ፅሁፍ ከአመት በፊት በዚሁ መንደር ያጋራሁት ቢሆ | ዘሪሁን ገሠሠ

አሁንም " ሳይቃጠል በቅጠል!" እላለሁ!

ተከታዩ ፅሁፍ ከአመት በፊት በዚሁ መንደር ያጋራሁት ቢሆንም ፣ ከሰሞኑ የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የአማርኛና የታሪክ ትምህርት ክፍሎችን መዝጋቱን ተከትሎ ለማስታወስ ያህል በድጋሜ ልለጥፈው ወደድኩ!



አሁንም " ሳይቃጠል በቅጠል!" እላለሁ!

" ..የታሪክ ሽሚያ - የራሱን ታሪክ መፃፍ የማይችል የመከነ ትውልድ መገለጫ ነው!"

ታሪክ ጥሩም ሆነ መጥፎ በታሪክነቱ ተከትቦ ትውልድ ከመልካሙ ታሪክ እንዲማርበትና እንዲያስቀጥለው ፥ እኩይ የሆነውን ታሪክ ደግሞ ዳግም እንዳይከሰት ተግቶ የሚሰራበት ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ቀዲም አሻራ ነው፡፡

የአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅበት ከትናንት ተምሮ ፥ በጎ ታሪኮችን አስቀጥሎ ነገን የመስራትና የራሱን ታሪክ ፅፎ ፥ ለተተኪው ትውልድ አውርሶ ማለፍ ነው፡፡

ያለፈ ታሪክ ዛሬውንም ሆነ ነገውን እንዲያበላሽ የሚፈቅድና የትናንቱን የቀድምት አባቶቹን አኩሪ ታሪክ ከመድገም ይልቅ ወደሽሚያ ውስጥ የሚገባ እርሱ ታሪክ መስራት የማይችል የመከነ ትውልድ ነው፡፡

አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ ከመጣ ጀምሮ የታሪክ ትምህርት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ከሀምሳ በላይ ዩኒቨርስቲዎች መሠጠት አቁሟል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ " ቀደምት የነበረው የኢትዮጵያ ታሪክ የእኛ ታሪክ አይደለም!" ብለው የሚያምኑና ለታሪክ ሽሚያ ያሰፈሰፉ ነውረኛ የፖለቲካ ሀይሎች ፥ የሀገረ መንግስቱን ስልጣን በመያዛቸው ነው፡፡ እነዚህ ሀይሎች የቀደምት አባቶቻችንን አኩሪ ታሪክ በብሄር ሚዛን ላይ አስቀምጠው ለቅርጫ የተቀመጡ ብሎም የተፈፀመውንም ሆነ በትርክት የወለዱትን በጎ ያልሆነ ታሪክ ፥ ህዝብን እርስበርሱ በማባላት በደም የጨቀየ አሁናዊው የፖለቲካ ስልጣን ረሀባቸውን ለማስታገስ የሚጠቀሙ ከንቱዎች መሆናቸው የሚታመን ነው፡፡

የዛሬ ሁለት አመት ገደማ የኦሮሞ የፖለቲካ ኤሊት ከሚባሉት አብዛኛዎቹ በተገኙበት መድረክ ላይ የመታደም እድሉን አግኝቼ በውይይታችን ካነሳሁት ጭብጥ መካከል ፦

<< ..ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክን አንሻፎ የሚተረጉም ፥ በክፉም ሆነ በበጎ የነበረውን ታሪክ ያለፈ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው ብሎ የማያምን ፥ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶቻችን ስለሀገር ብለው ሰርተው ያለፉትን ታሪክ በብሔር ቅርጫ ላይ አስቀምጦ ለመከፋፈልና ለመነጣጠቅ የሚተጋ ብሎም "ኢትዮጵያ" በምትባለው ሀገር ላይ በጋራ የሚያግባባ ተመሳሳይ ሀገራዊ ብያኔ የሌለው እንዲሁም ስያሜዋን ሁሉ የማይቀበል በፅንፈኝነትና በጥላቻ የሠከረ የፖለቲካ ኤሊት ባለበት ሀገር ፥ ማንኛውን ዘላቂ ሰላምና አብሮት ለማምጣት ነው ለውይይት የተቀመጥነው? ስለየቱ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ነው የምናወራው? ግጭትና እልቂትን እየደገሰ ያሐ የፖለቲካ ኢሊት ስለሰላምና ህዝባዊ አንድነት ለመስበክ መነሳቱ አሽሙር አይሆንምን ? ….. >> የሚል ሀሳብ አንስቼ ተከራክረን ሳንግባባ መለያየታችንን አስታውሳለሁ፡፡

በነገራችን ላይ ከኢህአዴግ/ህወሓት በፊት በነገስታቶችና በህዝቦች መካከል የነበረው ጥሩም ሆነ መጥፎ ታሪክ የተሰራው በሀገራዊ (ኢትዮጵያዊነት) ስሜት እንጂ በብሔር አጥር ስር አልነበረም፡፡ የሀገርን ሉአላዊነት ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው ከውጭ ወራሪዎች ጋር ካደረጓቸው ጦርነቶችና ካስመዘገቧቸው አኩሪ ድሎች ባሻገር ፥ እርስበርስ ተደረጉ የሚባሉት ግጭቶች ለስልጣን ሽኩቻ (ንግስና) ካልሆነ በስተቀርም ለብሔር የበላይነት የተደረጉ አለመሆናቸውን በቀና ልቦና የኢትዮጵያን ታሪክ ለሚገነዘብ ሁሉ ግልፅ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡

እናም " ለምን?" ብሎ የማይጠይቅ አድርባይና አጎብዳጁ የፖለቲካ ሀይል ፥ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከመጡ በኃላ በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ እየተሰራ ያለውን ሀገር አፍራሽና ለማንም የማይጠቅም የታሪክ ሽሚያ ማስቆምና መታገል አለመቻሉ ፥ በጥላቻ የሠከረው ፣ ፅንፈኛውና ታሪክ ለመስራት ያልተፈጠረው ይህ የፖለቲካ ቡድን ፥ ከዩኒቨርስቲ የታሪክ ዲፓርትመንት መዝጋት አልፎ ፥ መጪው ትውልድ የሚታነፅበትን ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተዘረጋ የትምህርት ስርአት ውስጥ የተንሻፈፈ ፣ የተፋለሰ ብሎም ለራስ ፖለቲካዊ ፍጆታ ማሳኪያነት ብቻ የሚውል ትርክት ተቀርፆ በማስተማሪያነት ሊመጣ ችሏል፡፡

ከዚህ በመነሳት ነገ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ማጥ መውጣት ቀርቶ ወደከፋ የእልቂት ጎዳና እየተንደረደረች እንደምትገኝ ፥ የተሟላ ጤንነት ያለው ሙሉ ሠው ሁሉ ፣ በቀላሉ የሚረዳው ሀቅ ነው!

ሠላም!