Get Mystery Box with random crypto!

''በኦነግ ሸኔ ታግተው ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ለተጠየቁ ሹፌሮች ገንዘብ እየተሰበሰበ ነው'' ተባ | ዘሪሁን ገሠሠ

''በኦነግ ሸኔ ታግተው ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ለተጠየቁ ሹፌሮች ገንዘብ እየተሰበሰበ ነው'' ተባለ!

ከአምስት ቀን በፊት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገርበ ጉራቻ ከተማ አካባቢ ለታገቱ ከ50 በላይ ሹፌሮች ፣ እገታውን የፈጸሙት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የጠየቁትን ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ህዝቡ እየሰበሰበ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የሥራ ኃላፊዎች ሰምታለች።

በዚህም በደብረ ማርቆስ እና ደንበጫ መካከል አማኑኤል ከተማ ላይ የታገቱ ሹፌሮች ይለቀቁልን በሚል ለሦስት ቀናት ያህል መንገድ ተዘግቶ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን ፤ መፍትሔ ባለመገኘቱ የታጋቾቹ ቤተሰቦች በየቦታው ጨርቅ አንጠፈው የተጠየቁትን ገንዘብ በመለመን ላይ ናቸው ተብሏል።

"እኛም ግራ ገብቶናል" ያሉ አንድ የሥራ ኃላፊ ፤ "አብዛኛው ሹፌሮች የታገቱት ከዚህ አካባቢ ስለሆነ ሕዝቡ ልጆቻችን ይፈቱልን በማለት መንገድ ተዘግቶ ነበር።" ካሉ በኋላ ፣ "ሕግ እና መንግሥት ባለበት አገር ሰው ታግቶ በሚሊየን ክፈሉ እየተባለ ነው፣ አጣርታችሁ ለመንግሥት ይፋ አድርጉ የሚሰማ ካለ።" ሲሉ ተደምጠዋል።

አክለውም፤ "ከታገቱት ውስጥ ዕድል ቀንቶት ለአንድ ሰው አንድ ሚሊየን ከፍሎ የሚለቀቅ አለ። አልፎ አልፎ እየከፈሉ እየተለቀቁ ነው፣ ክፍሎ ያልተለቀቀም አለ" ብለዋል።

የሥራ ኃላፊው "ገርበ ጉራቻ አሊዶሮ አካባቢ ያለው የመንግሥት አካል በዚህ ጉዳይ ለምንድነው ማብራሪያ የማይሰጠው?" ሲሉ ጠይቀው፤ "የፀጥታ ኃይል፣ መንግሥትና ህግ ባለበት አገር በተደጋጋሚ ድርጊቱ መፈፀሙ ያሳዝናል።" ብለዋል።

ከ50 በላይ ሹፌሮች ታግተው ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ነው የተጠየቀው ያሉት የሥራ ኃላፊው፤ "በዚህ ኑሮ ውድነት ምንም የሌለው ድሃ ልጆቹን ለማትረፍ በየቦታው ጨርቅ አንጥፎ እየለመነ ነው። የሚመለከተው አመራር ማብራሪያ ይስጥ።" ሲሉ አሳስበዋል።

ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው እና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ ተብሎ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሰዎችን ከመግደልና ከማፈናቀል ባለፈ ንጹሃን ዜጎችን በማገት ከፍተኛ ገንዘብ እየጠየቀ ይገኛል።

አዲስ ማለዳ ባለፈው ሰኔ 10/2015 በሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አቅራቢያ ከ50 በላይ የከባድ መኪና እና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎች ሹፌሮች ፣ እረዳቶችና ተሳፍሪዎች መታገታቸውን መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን፤ ድርጊቱ ሲፈጸም በቅርብ እርቀት የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ አካላት "ከበላይ አካል ትዕዛዝ አልተሰጠንም" በማለት የታገቱ ዜጎችን ሊታደጉ አለመቻላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች መግለጻቸው አይዘነጋም።

//ዘገባው ፦ የአዲስ ማለዳ ነው//