Get Mystery Box with random crypto!

የአህያው ታሪክ….! ….ከእለታት አንድ ቀን ንጉስ አንበሳ ቀበሮን ይጠራውና > ይለዋል። ቀበሮም | ዘሪሁን ገሠሠ

የአህያው ታሪክ….!

….ከእለታት አንድ ቀን ንጉስ አንበሳ ቀበሮን ይጠራውና << እጅግ በጣም እርቦኛል ፤ በአስቸኳይ የምበላው ካላመጣህልኝ ፥ አንተን ነው ቀረጣጥፌ የምበላህ! >> ይለዋል። ቀበሮም ተደናግጦ ለአንበሳው ምግብ ፍለጋ ሲሄድ ከአህያ ጋር ይገናኛል፡፡

ይሄኔ አህያን የጦስ ዶሮ ለማድረግ የማታለያ ሀሳብ የመጣለት ቀበሮ ፥ << አያ አህያ! ስፈልግህ አገኘሁህ፡፡ ንጉሳችን አንበሳ አንተን ንጉስ ሊያደርግህ ይፈልጋልና በአስቸኳይ እንሂድ ! >> ብሎ በማሳመን አስከትሎት ይሄዳል፡፡

የተራበው አንበሳ አህያው ከአጠገቡ ሲደርስ ፥ ጊዜ ሳያጠፋ ተንደርድሮ ጆሮውን ግሽልጥ አድርጎ ይበላዋል፡፡ ይሄኔ አህያ ደሙን እያዘራ ሲሮጥ ከቀበሮ ጋር ይገናኛሉ፡፡

<< አታለልከኝ አይደል ! ልታስበላኝ ነበር የጠራኸኝ ! >> ይለዋል፡፡

<< ኧረ በፍፁም አላታለልኩህም አያ አህያ ፤ ጆሮህን የበላህኮ ስትነግስ ዘውዱን ለመድፋት አንዳያስቸግርህ ብሎ ነው ! በል አሁን እንመለስ በቶሎ ..>> ይልና አሳምኖ ይመልሰዋል፡፡

ድጋሜ አህያው ከአንበሳው ፊት ሲደርስ ተንደርድሮ ጭራውን ቆርጦ ይበላዋል፡፡ አሁንም አህያው ደሙን እያዘራ ሲሄድ ከደላላው ቀበሮ ጋር ይገናኛሉ፡፡

<< አያ ቀበሮ ምን በድዬህ ነው ግን ፥ ያታለልከኝ ? አሁንም ጭራዬን በላኝኮ!>> ! >> ይለዋል፡፡

<< ኧረ በፍፁም አላታለልኩህም፡፡ ምነው አያ አህያ ? ለአንተው በደከምኩ ፤ አያ አንበሳ ጭራህን የቆረጠውኮ ፥ ከነገስክ በኃላ ዙፋኑ ላይ ስትቀመጥ እንዳያስቸግርህ አስቦ ነው፡፡ በል አሁን እንመለስ ..! >> ይልና በድጋሜ አሳምኖ ይወስደዋል፡፡

ይሄኔ አንበሳው አህያውን ደቋቁሶ ገደለው፡፡ ወደቀበሮውም ዘወር ብሎ << አህያውን አሳምነህ በማምጣትህ ጥሩ ሰርተሃል፡፡ በል አሁን ደግሞ አህያውን ገነጣጥለህ ቆዳውን ፥ ጭንቅላቱን ፣ ልቡን ፤ ሳንባውና ጉበቱን ብቻ ለይተህ አምጣልኝ! >> ሲል አዘዘው፡፡

ቀበሮ የታዘዘውን ፈፅሞ ለአንበሳው ይዞ ቀረበ፡፡ ነገርግን ይዞ ከመጣው ስጋ ውስጥ ጭንቅላቱን ስለበላው ሊገኝ አልቻለም፡፡ ይሄኔ አንበሳው በንዴት ጦፈ፡፡ << ጭንቅላቱን የት አባክ አስገብተኸው ነው ? >> ሲልም አፈጠጠበት፡፡

ቀበሮም የዋዛ አልነበረም << ጌታዬ! ጭንቅላት እኮ ቀድሞውኑ አልነበረውም፡፡ ጭንቅላት ቢኖረውማ ፥ ጆሮና ጅራቱን ከቆረጥከው በኃላ ዳግም ተመልሶ ወደአንተ ጋር ይመጣ ነበርን ? >> ብሎ በብልሃት በማሳመን ራሱን ከሞት አዳነ ይባላል፡፡

የሠው ልጅም ህይወት ለአንድና ለሁለት ጊዜ ሲሳሳት እንዲታረም ከሰጠችው እድል መማር ካልቻለ ፥ ከውድቀቱ በኃላ የመማር እድሉ ጠባብና ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ሊሆን ይችላል!