መፍትሔው ግራ አለመጋባትና በአማራነትህ ፀንቶ መቆም ነው! ልጅ እያለሁ ፤ በነጭ ወረቀት ላይ በስእል አሽሞንሙነው የገጠሟቸውን አጭሬ ግጥሞች ፥ ገበያ ላይ ወይም ሰው በሚበረክትበት ቦታ ይቀመጡና ፥ እያነበቡ በስሙኒ የሚሸጡ በርካታ ስራ ፈጣሪዎችን አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ ሻጩ በእጁ የያዛቸውን አጭሬ ግጥሞች እያነበበ ሲያስተዋውቅ ፥ ውስጥህ የገባውንና ስሜትህን የኮረኮረውን ግጥም "እሷን አምጣት!" ትልና በስሙኒ ሸምተህ ግድግዳህ ላይ ትለጥፋለህ፡፡ ታዲያ! በዚያ ዘመን ተገዝተው ከኛ ግድግዳ ላይ ከተለጠፉት አጭሬ ግጥሞች መካከል ፦ " ቢወፍሩ ዱባ ፤ ቢቀጥኑ ትንኝ" "ቢያወሩ አፈኛ ፤ ዝም ቢሉም ሞኝ" አምላክ ከዚህ ሁሉ አሟልተህ ስጠኝ!" . . የምትልን ግራ የተጋባ ሰው እንደገጠማት የምታሳብቅ ግጥም ፈፅሞ እስካሁን አልረሳትም፡፡ ጓዶች! የአማራ ህዝብም ላለፉት ሰላሳ አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ፥ የገጠመው እንደዚህ ግራ የተጋባ ነገር ነውኮ! የጥላቻ ትርክት ጡጦ ጠብተው ያደጉ ፅንፈኛ ብሄርተኞች ፥ በጠላትነት ፈርጀውትና የሀገረ-መንግስቱን ፖለቲካ ተቆጣጥረው ፍዳውን ሲያበሉት ፥ እንደህዝብ ማንነቱን ዋጋ ሰጥቶ ከመደራጀት ይልቅ "ዘር ለገበሬ ነው!" እያለ "ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ" በማለቱ " አሀዳዊ ፣ ደፍጣጭ ፥ ነፍጠኛ ፣ ትምክህተኛ ፣ ...ወዘተርፈ " የሚሉ ስሞች እየተሰጠው መከራውን ሲያይ ኖረ፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ለ27 አመታት የሀገረ-መንግስቱን ስልጣን ይዘው የኖሩት የትግራይ ፅንፈኛ የብሄር ሀይሎች ፥ በህዝብ ትግል ከማዕከላዊ መንግሥት ስልጣን ተገፍተው ቢሰነብቱም ፥ "ፍጥጥ" ያሉት የከፉ ፅንፈኞች ተተክተው ፥ የፍረጃ ስያሜዎቹንም ለማጥቂያነት እየተጠቀሙ አባብሰው ቀጠሉ እንጂ የተለየ ነገር አልተፈጠረም! ታዲያ! ከዚህ ሁሉ መከራ በኃላ የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትንና ፥ ከጊዜ ወደጊዜ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ብሎም ጥቅምና ፍላጎቱን ለማስከበር " እንደህዝብ ተደራጅቼ የሀገረ-መንግስቱን የፖለቲካ አሰላለፍ ልመሳሰል!" በማለት " አማራ ነኝ!" ብሎ ሲነሳ ደግሞ ፤ የራሳቸውን ዘመን ተሻጋሪ የግብር መጠሪያ አውልቀው " የአማራ ፅንፈኞች" የሚል ካባ ደረቡለትና ፥ ይኸው ለጅምላ እልቂትና ሰቆቃ በይፋ መጠቀም ጀምረው አረፉት! ገጣሚው "ቢወፍሩ ዱባ ፤ ቢቀጥኑ ትንኝ " ያለውም እንዲህ ግራ ቢገባው ነውኮ! ለዚህ መፍትሔው " ትንኝም ፥ ዱባም ፥ ..!" ለሚሉት መስሚያህን "ጥጥ" አድርገህ ፥ ፍፁም ጠንካራ በሆነ ህዝባዊ አደረጃጀትና ትግል ፥ ለዘመናት የገነቡትን የትርክትና የጥላቻ ግንብ በመናድ ራስህን የአላፊ አግዳሚው መፈንጫ ከመሆን መዳን ብቻ ነው! ይኸው ነው! 6.2K views16:34