Get Mystery Box with random crypto!

የደሀ ፖለቲካ ለምን ውሃ መውቀጥ ይሆንብናል ? ' አፍሪካውያን ለዘመናት ከድህነት መውጣት እን | ዘሪሁን ገሠሠ

የደሀ ፖለቲካ ለምን ውሃ መውቀጥ ይሆንብናል ?

" አፍሪካውያን ለዘመናት ከድህነት መውጣት እንዴት ተሰሳናቸው ? " ብትለኝ ፥ መልሴ የሚሆነው << የህዝቡ ድህነት ለአንባገነን መሪዎቻቸው በስልጣን ላይ የመቆያ መሳሪያ ሆኖ ስለሚያገለግላቸው ነው ! >> እልሀለሁ፡፡


<< ደሀ (ድህነት) >> የሚለውን ቃል ከኢኮኖሚያዊ ድህነት ባሻገር ፥ በተለያዩ አውዶች ልንጠቀመውና ብያኔ ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ሀብት ያላቸው ቢሊየነሮችም ፥ "ደሀ" የሚለውን ስም ሊጋሩ የሚችሉበትም በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ " Money makes the world go round, but greed turns it upside down. " እንዲሉት ስግብግብ ባለፀጋም ደሀ ነው ፤ የአስተሳሰብ ደሀም አለ ፤ ጓደኛና ወዳጅ የሌለው የሰው ደሀ ፥ የእውቀት ደሀ ፣ ...ወዘተ እያልን ልንዘረዝር እንችላለን፡፡ እኔ ያነሳሁት ግን ስለኢኮኖሚያዊ ድህነት ነው፡፡


እንግዲህ በአለም ላይ ለሚደረጉ ጦርነቶችና የእርስበርስ ፍጅቶች በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም ፥ ድህነትና ኢ-ፍትሃዊነት ( Poverty & Injustice ) ግን የመጀመሪያዎቹና አብዛኛዎቹ የጦርነትና የፍጅት መነሻዎች ናቸው፡፡


ደሀ ሰው ወይም ህዝብን ለመግለፅ ያህል ፥ ደሀ ህዝብ በፕሮግራም ወይም በጊዜ ሰሌዳ የሚመራ ህይወት የለውም፡፡ ሌላው ቀርቶ የሚመገበው ባገኘበት ሰአት በመሆኑ የተለየ የመመገቢያ ሰአት የለውም፡፡ ፕሮግራም "አለኝ!" ቢልም የሚመገበውን ካላገኘ ሊጠቀምበት አይችልም፡፡

" Where money talks, the poor have no voice. " እንደሚባለው ፥ ገንዘብ በሚናገርበት አለም ላይ ደሀ ድምፅ የለውም፡፡ ደሀ የመናገርና ሀሳብን የመግለጽ ነፃነቱን እንኳ ለመንግሥት ወይም ለናጠጡ ሀብታሞች አሳልፎ የሰጠ ነው፡፡ ደሀ በምኞትና በማይቀምሰው ፣ በማይዳስሰውና በማያጣጥመው ፍላጎት ውስጥ እየተበሳቆለ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ አለምን በሚታይ መልኩ ለሁለት የተለያዩ አለሞች የሰነጠቋትም ድህነትና ባለፀጋነት ናቸው፡፡

የደሀ ህዝብ ፖለቲካና ፖለቲከኞችም በአብዛኛው በአቢዮትና በጦርነት ካልሆነ በስተቀር ፥ ከማስመሰል ባሻገር ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ለመለማመድም ሆነ በዴሞክራሲያዊ መልኩ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ ፍላጎትና ዝግጅቱ የላቸውም፡፡ በተለይ በአብዛኛዎቹ የደሀ አፍሪካ ሀገራት አንባገነን መንግሥታት ድህነትን ከመዋጋት ይልቅ ደሀውን ህዝብና ድህነቱን ራሱ እንደመሳሪያ ተጠቅመው ፥ በተሻለ ሀሳብ የተገነባ ጠንካራ ትግል እንዳያደርግ ያሽመደምዱታል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ በአብዛኛው ሀገራት የዴሞክራሲያዊ ትግልና የምርጫ ፖለቲካ ከይስሙላነት በዘለለ ፍሬ ሲያፈሩ ወይም ለውጥ ሲያመጡ የማይስተዋለውም ለዚህ ነው፡፡


አዲስና የተሻለ ሀሳብ በጥቂቱ እንኳ ወደፖለቲካ ጠረጴዛ ሊመጣ የሚችለው በአንባገነኖች ችሮታ እንጂ በህዝብ ድምፅ የመሆን እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ደሀ ህዝብ በድህነቱ ምክንያት ነፃነትና መብቱን ጭምር በቀላሉ በመንግሥታዊ አንባገነኖች ስለሚነጠቅ ነው፡፡ ነጮቹ " The poor man has sold his freedom of expression to the state. " ማለታቸውም ለዚያ ነው፡፡

ከደሀው ህዝብ አብራክ ወጥተው ፥ ደሀው ህዝባቸውን በድህነቱ ዙፋናቸውን ለማስጠበቅ የሚታትሩት እኚህ ጨካኝ አንባገነኖች ፥ እግሩን ለቆረጡት ህዝብ ዊልቸር ገዝተውለት እንዲያመሠግናቸው ይፈልጋሉ ፤ ለረሀብ ዳርገውት በኩርማን እንጀራ ወይም በጥቂት ፍርፋሪ የዜግነት ነፃነቱንና ሰዋዊ ክብሩን ሁሉ አሳልፎ እንዲሰጣቸው ይሞክራሉ ፥ ያደርጉታልም፡፡ የእለት የእለቱን ፥ የፊት የፊቱን የሚኖረው ደሀው ህዝብ ደግሞ ፥ መሻታቸውን እንዲቀበል ድህነቱ ጠፍንጎ ያስገድደዋል፡፡፡ ፖለቲካዊ ትግልም ስልጣን በያዙ አንባገነኖች በቀላሉ ይጨናገፋል ፣ ይከፋፈላል ፣ ይገዛል፡፡

ከዚያ አለፍ ሲልም ትልቅ አቅምና ሀሳብ ይዞ ፥ ምንም ማድረግ ወዳለመቻል መስመር ይጓዛል፡፡ ትግል በገንዘብ አቅም ሲደገፍ ግን ላለማድረግህ የምትደረድረው ሰበብ ይቀንሳል ፤ ለህዝብህ በአፈሙዝ መታገል ከፈለክ መሳሪያ ገዝተህ ፍላጎትህን ታሳካለህ እንጂ ትጥቅ " የሚሠጠኝ አጣሁ!" ብለህ ሀሳብ ብቻ ይዘህ አትቀመጥም፡፡ ከብሶት ይልቅ መፍትሄ በእጅህ ይሆናል፡፡ አቅደህ በሰአቱ ትፈፅማለህ፡፡ ትግልህ በፕሮግራምና በእቅድ ተሟልቶ ይመራል፡፡ ከወደረኞችህ ጋር መገዳደር ፣ ተፅዕኖ መፍጠርና ለውጥ ማምጣትንም ትችላለህ፡፡ በገንዘብ የምትገዛው እንጂ በድህነት የምታጣው ተፈላጊ ነገር አይኖርም፡፡ ከሌለህስ ? በቃ! የለህማ!

በደሀዋ ሀገራችን እንኳ በአንፃራዊነት ፥ መስኖ የሚያለሙ ፥ የተሻለ የሚያመርቱ ፥ ኢኮኖሚያቸው ከሌላው የሚሻል ዜጎች ባሉበት አካባቢ ፥ የተሻለ ማህበረሰባዊ ንቃት ፥ ብዙ ታጋይና አርበኞች ብሎም የነፃነት ትግል ጅማሮዎች ጎላ ብለው የመታየታቸውን ምስጢር ለማጤን ሞክራችኃልን ?

እናማ በደሀ ሀገራት ጦርነትና ሽኩቻ መለያና መገለጫ ሁነው ይቀጥላሉ፡፡ አምባገነኖችም በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ያቃተው ሀህዝባቸውን ፥ ጥይት በዶላር ገዝተው ያዘንቡበታል ፥ አንገት አስደፍተውም ከፋፍለው ይገዙታል ፤ ተስፋም ያስቆርጡታል ፤ በድህነቱ የተሻለ ህልሙን እንዲረግም ያደርጉታል ፤ ድምፁን በቁራሽ ዳቦ ይለውጡታል፡፡

በመጨረሻም ተስፋ የቆረጠው ህዝብ ከሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ የሀሳብ ፖለቲካ ይልቅ አቢዮት (አመፅን) ብቸኛ አማራጩ ያደርጋል፡፡ በአመፅና በአቢዎትም በሰአታት ወይም በጥቂት ቀናት ውስጥ አንባገነኖችን ጠራርጎ ያባርራል፡፡

የሚያሳዝነው ግን ከዚያ በኃላም የሚቀጥለው ተመሳሳይ አዙሪት መሆኑና በተመሳሳይ የጭካኔ ፖለቲካ ዲስኮርስ የታነፀ ስርአት የመሆን እድሉ ሠፊ መሆኑ ነው፡፡ አንባገነኖችና፡ በጥላቻ ትርክት የሰከሩ የፖለቲካ ሀይሎች የሚያበላሹብን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነጋችንንም የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡

በመሆኑም አንድም ፥ በገዛ ህዝቡ ድህነትና ብስቁልና ዙፋኑን የሚያፀናው ጨካኝ የፖለቲካ ልሂቅ ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ ፥ የህዝቡን ድህነት ታግሎ ማሸኘፍ ወደሚቻልበት መንገድ ካልመጣ ፤ ሁለትም ህዝቡ በብሶት የወለዳቸው ፥ የተሻለ አማራጭ ሀሳብ ያነገቡ መሪዎችን አምጦ በመውለድ የተደራጀ ሁለንተናዊ ትግል አድርጎ ስርነቀል ለውጥ ካላመጣ ፤ አቢዮትና አመፁም ቢሆን ፖለቲካዊ ግብ ተኮርና ዛሬውን የማይደግም እንዲሆን አድርጎ ማስኬድ ካልቻለ ፥ የደሀ የምርጫ ፖለቲካ በአንባገነኖች መዳፍ ስር የሚጥመሰመስ ፍሬአልባ ችግኝ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ህዝቡም በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ መከራና ግፉ እንደበረዶ እየዘነበበት መቀጠሉ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ሠላም!